ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ርኅራኄን በማሳየት ምሕረትን እንድናደርግ ተጠርተናል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በምትከተል ካቶሊካ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ እሑድ ኅዳር 16/2016 ዓ. ም. የተከበረውን የክርስቶስ ንጉሥ በዓል በማስታወስ፥ በዕለቱ ከመሩት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አስቀድመው ባቀረቡት ቃለ ምዕዳን፥ የተጠራነው ርኅራኄን፣ ምሕረትን እና ለጋስነትን እንድናሳይ ነው ብለው፥ እነዚህም የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን መመዘኛዎች ናቸው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በእነዚህ ቀናት ውስጥ በሮም በተከሰተው ከባድ ብርዱ ምክንያት በየእሑዱ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከሚሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የሚያቀርቡትን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት፥ ቅዱስነታቸው ኅዳር 16/2016 ዓ. ም. ከቅድስት ማርታ የጳጳሳት መኖሪያ ቤታቸው ሆነው መምራታቸው ታውቋል።

ለሳምንታዊው ጸሎት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት በርካታ ምዕመናን የቅዱስነታቸውን ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እና ተጨማሪ መልዕክት በንባብ ያሰሙት የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሞንሲኞር ፓውሎ ብራይዳን እንደነበሩ ታውቋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተሰበሰቡ መንፈሳዊ ነጋዲያን፣ የአገር ጎብኚዎች እና ምዕመናን በሙሉ ዝግጅቱን የተከታተሉት በሥፍራው በተዘጋጀላቸው ትላልቅ የቪዲዮ ስክሪኖች በኩል እንደ ነበር ተመልክቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጤናቸው ምክንያት ትናንት ሊያካሂዱ የታቀዱትን ዝግጅቶች መሰረዛቸው ታውቋል። ከሰዓት በኋላ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል ሄደው ባደረጉት የሳምባ ምርመራ የጎላ ችግር እንደሌለባቸው የተገኙት ውጤቶች ገልጸዋል።

የክርስቶስ ንጉሥ በዓል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ዓመታዊ በዓል ባዘጋጁት መልዕክት፥ ቅዱስ ወንጌል ስለ መጨረሻው የፍርድ ቀን ሲነግረን፥ “እርስ በርሳችን የምናደርገውን በጎ ተግባር እና ምሕረትን መሠረት ያደረገ ነው” በማለት ተናግረዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ በእግሩ ሥር በተሰበሰቡበት በአንድ ትልቅ አዳራሽ ውስጥ እንደሆነ ቅዱስ ወንጌል ላይ የተገለጸውን ትዕይንት በማስታወስ፥ ብጹዓኑ የንጉሡ ወዳጆች መሆናቸው ገልጸዋል። የተራቡትን የሚያበሉ፣ የታመሙትን እና የተቸገሩትን የሚንከባከቡ፣ እስረኞችን የሚጎበኙ እነርሱ ብጹዓን ናቸው ብለው፥ “ይህም ሃብትን፣ ዝናን፣ ምቀኝነትን በማሳደግ የግል ጥቅምን ለሚፈልጉ ሰዎች ከሚሰጣቸው ባዶ ዋጋ እና የዓለም መመዘኛዎች ፍጹም የተለየ ነው” በማለት አስረድተዋል።

ሌሎችን መርዳት

“የኢየሱስ ክርስቶስ መመዘኛዎች ችግረኞችን፣ አቅመ ደካሞችን እና ዕርዳታን የሚፈልጉትን ለሚያገለግሉት ሰዎች ትልቅ ሥፍራን ይሰጣል” ብለዋል። ይህም ድሆችን ‘ወንድሞች’ ብሎ የሚጠራ፣ የተራቡትን፣ የተጠሙትን፣ የታመሙትን፣ የታሰሩትን የሚያውቅ እና “ከእነዚህ ሁሉ መካከል ለአንዱ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው” የሚል ፍጹም የተለየ ንጉሥ ነው ብለዋል። “ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተራቡትን፣ ቤት የሌላቸውን፣ የታመሙትን እና የታሰሩትን ያሳስባል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እነዚህ ማኅበራዊ ችግሮች በሙሉ የዛሬዎቹ እውነታዎች ናቸው ብለዋል።

ርህራሄ እና ምህረት

“ ‘ብፁዓን’ የሚባሉት ዕርዳታችንን እና አጋርነታችንን የሚሹ ሰዎችን በማገልገል ፍቅርን እና ምሕረትን የሚያሳዩ እንደሆኑ ቅዱስ ወንጌሉ አጽንኦት ይሰጣል። እነዚህን ሰዎች ችላ ማለት ወይም ማግለል ሳይሆን ምግብን፣ ውሃን፣ ልብስን፣ መጠለያን በመስጠት አብሮአቸው የሚሆኑት የንጉሡ ወዳጆች ናቸው። ምክንያቱም የእርሱን ምሳሌ በመከተል ምህረትን፣ ርህራሄን እና ለጋስነትን በተግባር በመግለጽ እራሳቸውን ይለያሉ” ብለዋል።

“ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ራሱን የሰው ልጅ ብሎ የሚጠራው፥ በሚወዳቸው እህቶች፣ ወንድሞች እና አቅመ ደካማ በሆኑ ሰዎች መካከለ ስለሚገኝ ነው። የእርሱ ንጉሣዊ ፍርድ ቤት የሚገኘውም የሚሠቃዩት እና እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ባሉበት ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከማቴ. 25:31-46 ተወስዶ በተነበበው በዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ቃለ ምዕዳን፥ የራሳችንን ሕይወት እንድንመረምር፣ የምሕረትን ማዕከላዊነት መገንዘብ እንዳለብን እና እንድናምንበት አደራ ብለው፥ ፍቅር እና በጎነት ለአማኞች እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጽ የንጉሡ ወዳጅ ከሆንን፥ በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች ያለን ፍቅር ምን ያህል ነው?” ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል ብለዋል።

የሰማይ እና የምድር ንግሥት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፥ በሰዎች መካከል እራሱን ድሃ ያደረገው ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንወደው ትርዳን በማለት የዕለቱን ቃለ ምዕዳን ደምድመዋል።

27 Nov 2023, 16:41