ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የካኅናት ሕይወት ግልጽ እና ተአማኒ መሆን አለበት” ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ቅዳሜ ግንቦት 23/2017 ዓ. ም. ጠዋት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተፈጸመው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለበርካቶች የክኅነት ማዕረግ በሰጡበት ወቅት፥ በተልዕኳቸው እና በማንነታቸው ላይ በማስተንተን ስብከት አሰምተዋል።
ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባሰሙት ስብከት፥ በእግዚአብሔር ሕዝብ እና በካኅናት ማንነት መካከል ያለውን ግንኙነት በማስረዳት፥ የካኅናት ማንነት የተላኩበት ሕዝብ አካል በመሆን ከዕለት ተዕለት የሚያድግ መሆኑንም ተናግረዋል።
አዲስ የሚቀቡ ካህናት፥ የክኅነት ማንነታቸው ከዘላለማዊው እና ከሊቀ ካህናቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ዘወትር ሊያስታውሱት ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
የክኅነት ሹመት፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ፈጽሞ እንዳልተወ የሚያሳይ፥ ተስፋን እና አንድነትን ዘወትር የሚገነባ ነው” በማለት አስረድተዋል።
“የእግዚአብሔር ደስታ የተጋነነ ሳይሆን ታሪክን የሚለውጥ ከመሆኑ በተጨማሪ እርስ በርስ እንድንቀራረብ ያደርገናል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የሚያገለግሏቸው ሰዎች ከሥጋ እና ከደም የተፈጠሩ በመሆናቸው ሁሉም ካህናት ራሳቸውን ከገሃዱ ዓለም ጋር በማያያዝ በሕይወታቸው ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ እንዲሆኑ ጋብዘዋል።
“የተቀበልከውን ስጦታ ሳታስቀር፣ ሳትለይ ወይም ሳትለውጥ ለእነርሱ አገልግሎት ራስህን ቀድስ!” ሲሉ ተናግረው፥ “ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ራስ ወዳድነት የሚስዮናዊነት መንፈስ እሳትን ያጠፋል” በማለት ብዙ ጊዜ ያስጠነቀቁትን አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ቤተ ክርስቲያን በባህሪዋ ከራሷ ይልቅ ወደ ሌሎች የምትመለከት እንደሆነች ተናግረው፥ ስቃይ፣ ሞት እና ትንሳኤ በእውነት የታየበት የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ዘወትር በሚያቀርቧቸው በእያንዳንዱ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ውስጥ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
“የእግዚአብሔር መንግሥት፣ የግል ነፃነቶቻችሁን አንድ በማድረግ፥ ወደ ሌሎች ሰዎች ዘንድ እንድትሄዱ በማዘጋጀት፥ አእምሮአችሁን እና የወጣትነት ጉልበታችሁን በሙሉ ኢየሱስ ለቤተ ክርስቲያኑ በአደራ በሰጠው የኢዮቤልዩ ተልዕኮ ውስጥ እንድታስገቡ ያደርጋችኋል” ብለዋል።
የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አገልግሎት ስንመለከት፥ የክህነት ሕይወት የአገልግሎት እንጂ የበላይነት እንዳልሆነ፥ “ምክንያቱም ይህ አገልግሎት ማንም ሊተካው ያልተጠራበት የኢየሱስ ክርስቶስ ተልዕኮ ነው” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አስረድተዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው አማካይነት በፍቅሩ እንዳስደነቀን ገለጸው፥ ሰዎች የክኅነትን ምስጢር በሚቀበሉበት ወቅት ለምዕመናን እና ለፍጥረት በሙሉ ቦታ እንዲሰጡ የተጋበዙ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች፥ “ከእናንተ ጋር ሳለሁ እንዴት እንደኖርኩ ታውቃላችሁ” ሲል በተናገረው ላይም አጽንዖት ሰጥተዋል።
“የእኛ ሕይወት ግልጽ፣ የሚታይ እና ተአማኒነት ያለው እንዲሆን በማድረግ፥ ይህም በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ታማኝ ምስክሮች ሆነን ለመቆም ነው” ብለዋል።
“ክርስቲያኖች ወደ ቆሰሉት ሰዎች ዘንድ የተላከች የቆሰለች ቤተ ክርስቲያን ታማኒነት እንደገና መጠገን የሚችሉት በኅብረት ብቻ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ከሙታን የተነሳውን የኢየሱስ ክርስቶስን ቁስሎች ያመለከቱት ቅዱስነታቸው፥ የሰዎችን እምብተኝነት እና የእግዚአብሔርን ይቅርታ የሚገልጹ ሁለት የቤተ ክርስቲያን ሚስዮናዊ ስልጣን ምልክቶች እንደሆኑ አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስብከታቸው ማጠቃለያ፥ “የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ነጻ የሚያወጣ እንጂ ሌሎችን እንድንጨቁን የሚያደርግ አይደለም” ብለው፥ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት ወደ 55,000 የሚጠጉ ምዕመናን እነዚህን አዳዲስ ካህናትን በአገልግሎታቸው እንዲደግፏቸው አደራ ብለዋል።
“በአንድነት ሆነን ሰማይን እና ምድርን አንድ እናደርጋለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “የቤተ ክርስቲያን እናት በሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እገዛ የክኅነት ስልጣን ዘወትር የሚያበራ፥ ትሑታንን የሚያነሳ፣ ትውልድን የሚያገናኘት እና ብፁዓን እንድንባል የሚያበቃን እንዲሆን” በማለት ስብከታቸውን ደምድመዋል።
