ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ኢየሱስን በቅርብ የመከተል አስደናቂ ልማድን ማሳደግ እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለገዳማውያቱ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት በካስቴል ጋንዶልፎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ውስጥ ቅዳሜ ሐምሌ 5/2017 ዓ. ም. ጠዋት በተቀበሏቸው ጊዜ ነው።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በዚህ ወቅት ከሮም በስተደቡብ ምሥራቅ በምትገኘው የሐይቅ ዳር ከተማ ካስቴል ጋንዶልፎ የተወሰኑ እንግዶችን የሚቀበሉ ቢሆንም፥ በጠቅላላ ምዕራፍ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ወደ ሮም የመጡ የውጭ ሐዋርያዊ ተልዕኮዎች ጳሳሳዊ ተቋማት አባላትን በደስታ ተቀብለዋል። ገዳማውያን እና ገዳማውያቱ፥ ፊሊፒናዊ የሃይማኖት መምህራን፣ የቬኔሪኒ የሃይማኖት መምህራን፣ የቤተ ክርስቲያን እህቶች ማኅበር አባላት፣ በሳሌዢያን ማኅበር የቅዱስ ልብ እህቶች ማኅበር አባላት እና የቅድስት አንጀላ ፍራንችስካውያን እህቶች ማኅበት አባላት እንደሆኑ ታውቋል።
የማኅበራቱ አባላት በበርካታ የዓለም ክፍሎች በታማኝነት ላደረጉት ሥራ ምስጋናቸውን በማቅረብ ንግግራቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው፥ መሥራቾቻቸው በመንፈስ ቅዱስ ብርታት የፈጸሙት ተግባር የኢየሱስ ክርስቶስ አካል መገንባት እንዲችሉ በልዩ ልዩ ምግባራት እንዲሳተፉ ማድረጉን አስታውሰዋል።
ለሰው ልጆች ያላቸው የእግዚአብሔር ፍቅር
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “እያንዳንዱ ማኅበራት የእግዚአብሔርን ሕዝብ እና የሕይወት ተልዕኮን የሚያሟሉ ገጽታዎችን ያካተቱ ናቸው” ብለው በተለይም ራስን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕትነት ጋር በማቅረብን፣ ተልዕኮን፣ የቤተ ክርስቲያንን ፍቅር ጠብቆ በማቆየት ለሌሎች ማሳለፍን እና ወጣቶችን ማስተማር እና ማዘጋጀት ነው” ብለዋል።
እነዚህ አገልግሎቶች በሙሉ በአንድ ዘላለማዊ እውነታ ውስጥ የሚገኙ፥ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ባለው ፍቅር ላይ የተመሠረቱ ልዩ ልዩ መንገዶች ናቸው” ሲሉ አስረድተው፥ ማኅበራት የተቀበሉትን ትሩፋት በማደስ እና ይዘቱን ለዛሬው ዓለም ጠቃሚ ለማድረግ በጥልቅ በመጸለይ እና በመደማመጥ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጋብዘዋቸዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ማሳሰቢያ
የቀድሞው ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ በመጥቀስ፥ በሐዋርያዊ መጋቢዎች መሪነት ብዙ የክርስቲያን ማኅበረሰብ በጎ አድራጎት ወደ ሙሉ እውነት እንዲጓዝ የሚያግዘው መንፈስ መሆኑን አስታውሰው፥ በዚህ ዐውደ ውስጥ ትክክለኛውን የሚስዮናዊነት መንፈስ ማደስ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለውን ስሜት በመከተል፣ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን ተስፋ መሠረት በማድረግ፣ በልባቸው ውስጥ የመንፈስ ቅዱስን እሳት በማቀጣጠል፣ ሰላምን በማሳደግ እና በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሐዋርያዊ አገልግሎት ኃላፊነትን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።
ኢየሱስ ክርስቶስን በቅርበት የመከተል አስደናቂ ልማድን
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስን በቅርበት የመከተል አስደናቂ ልማድን ጎን ለጎን ማስቀመጥ እንደሚገባ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ይህም በተለይም እንደ ገዳማውያን እና ገዳማውያት ኢየሱስ ክርስቶስን በቅርብ የምንከተል መሆናችንን እንድንገነዘብ ይረዳናል” ብለዋል።
“ኢየሱስ ክርስቶስን በቅርብ መከተል በሁላችን ዘንድ ያለውን ቤተ ክርስቲያን የመሆን ግንዛቤን እና ደስታን እንዲያድስልን እና እንዲያጠናክልን” በማለት ምኞታቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በተለይም ገዳማውያን እና ገዳማውያት አንድ ላይ ሆነው በማስተዋል የሚያካሂዱት ጠቅላላ ጉባኤ ራሳቸውን በአገልግሎት ሚያሳትፍ ልዩ ዕቅድ አድርገው እንዲያስቡ ያበረታታቸዋል” ብለዋል ።
የእግዚአብሔር የማዳን እቅድ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መልዕክታቸውን በመቀጠል፥ “ያ ዕቅድ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በሙሉ እንደ አንድ ታላቅ ቤተሰብ ወደ ራሱ ለመመልስ የፈልገበት የመዳን ዕቅድ ነው” ብለው፥ “እንደ ትናንሽ መብራቶች በመሆን የማይጠፋውን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን በምድር ላይ እንዲሰራጭ እንዲያደርጉ አሳስበዋቸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለገዳማውያኑ እና ገዳማውያቱ ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ከመስጠታቸው በፊት፥ ሁሉንም ነገር የሚያስተምረውን የመንፈስ ቅዱስ ድምፅ ለመረዳት እግዚአብሔር እንዲረዳን እና ያለ መንፈስ ቅዱስ ዕርዳታ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅም” ብለው በሥፍራው የተገኙትን በጸሎታቸው እንዲተባበሩ ጋብዘዋቸዋል።
