ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ሊዮ 14ኛ በካስተል ጋንዳልፎ የመልአከ እግዚአብሕእር ጸሎት ሲያደርጉ ር.ሊ.ጳ ሊዮ 14ኛ በካስተል ጋንዳልፎ የመልአከ እግዚአብሕእር ጸሎት ሲያደርጉ   (ANSA)

ር.ሊ.ጳ ሊዮ በካስቴል ጋንዶልፎ ቅዳሴ ላይ፡ እንደ ደጉ ሳምራዊ ክርስቶስን መምሰል ይኖርብናል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እሁድ ሐምሌ 06/2017 ዓ.ም በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው በቅዱስ ቶማስ የቪላኖቫ ቁምስና መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እኛም እንደ ደጉ ሳምራዊ ወደ ጌታ መመልከት እንዳለብን ጠቁመዋል፣ እናም የእግዚአብሔርን ፍቅር እና ፈውስ ስናገኝ ለሚያጋጥሙን ሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ መጽናኛ መስጠት እንደምንችል አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

"በክርስቶስ ከተፈወስን እና ከተወደድን በኋላ፣ እኛም በዓለማችን የእርሱ ፍቅር እና ርህራሄ ምስክሮች መሆን እንችላለን" ያሉት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የደጉ ሳምራዊ ምሳሌ ላይ ባደረጉት አስተንትኖ ለክረምት የዕረፍት ጊዜያቸው በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው የቅዱስ ቶማስ ዘ ቪላኖቫ ጳጳስ ደብር በቅዳሴ ላይ ይህን አጽናኝ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህን መስዋዕተ ቅዳሴ አብረዋቸው በማክበራቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ በስፍራው ለተገኙት ሁሉ ሰላምታ በመስጠት ጀመሩ።

በመቀጠል ቅዱስ ሉቃስ እንደገለጸው በዚህ የእሁድ ወንጌል ውስጥ “ከኢየሱስ ድንቅ እና አንገብጋቢ ምሳሌዎች አንዱን እንሰማለን” የሚለውን የደጉ ሳምራዊ ምሳሌ “ስለ ራሳችን ሕይወት እንድናስብ ዘወትር ይፈታተነናል” “የተኛውን ወይም የተዘናጋ ሕሊናችንን እንደሚያስቸግር” እና “በሕግ መገዛትና በመፈጸም ረክተን፣ ነገር ግን የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት እንዘነጋለን፣ በምሕረት የተሞላ ርኅራኄ እንደ መሐሪው እግዚአብሔር ሊኖረን ይገባል ብለዋል።

ሌሎችን እንዴት መመልከት እንደሚኖርብን

የደጉ ሳምራዊ ምሳሌ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እናዳሉት ከሆነ በእውነት ስለ ርኅራኄ ኢየሱስ ለምእመናን ሲነግራቸው፣ “ሌሎችን እንዴት እንደምንመለከት ማወቅ አስፈላጊ ነው፣ ምክንያቱም በልባችን ውስጥ ያለውን ያሳያል” በማለት ተናግሯል።

“አይተን መራመድ እንችላለን ወይም አይተን በርኅራኄ ልንነካ እንችላለን” በማለት ምሳሌው በመጀመሪያ የሚናገረን አምላክ እኛን ስለሚያይበት መንገድ መሆኑን በማስታወስ፣ “እኛም በተራው በፍቅርና በርኅራኄ የተሞሉ ሁኔታዎችንና ሰዎችን በዓይን እንዴት ማየት እንደምንችል እንማር” ብሏል።

ደጉ ሳምራዊ፣ በእርግጥም የኢየሱስ ምሳሌ እንደሆነ ያስታውሱናል፣ “አብ ወደ ታሪካችን የላከው የዘላለም ልጅ የሆነው ኢየሱስ የሰውን ልጅ በርኅራኄ መመልከት ቀጥሏል፣ እኛም በስሙ የምንጠራ ክርስቲያኖች የእርሱን አብነት በመከተል መኖር ይኖርብናል ብለዋል።

“በወንጌል እንደተገለጸው ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ይወርድ እንደነበረው፣ የሰው ልጅም ወደ ጥልቅ ሞት ይወርድ ነበር” ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፣ “በራሳችንም ዘመን የክፋትን፣ የመከራን፣ የድህነትንና የሞት እንቆቅልሹን ጨለማ መጋፈጥ አለብን ብለዋል።

ቁስሎችን በፍቅሩ እና በምህረቱ ይፈውሳል

ነገር ግን፣ ቅዱስ አባታችን እንደ ተናገሩት “እግዚአብሔር በርኅራኄ አይቶናል፤ በመንገዳችን ሊሄድና በመካከላችን ሊወርድ ፈለገ። በደጉ ሳምራዊ በኩል ኢየሱስ ቁስላችንን ሊፈውስና የፍቅሩንና የምሕረቱን ቅባት በእኛ ላይ ሊያፈስስ መጣ” በማለት አረጋግጠዋል።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአንድ ወቅት ኢየሱስን “የአብ ለእኛ ያለው ርኅራኄ ምሳሌ” በማለት የጠሩ ሲሆን እግዚአብሔር ምሕረትና ርኅራኄ እንደሆነ ያስታወሱ ሲሆን ቅዱስ አውግስጢኖስም እኛን ለመርዳት እንደመጣ ደጉ ሳምራዊ ኢየሱስ “ባልንጀራችን ተብሎ ሊጠራ ፈልጎ ነበር፤ በእርግጥም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዘራፊዎች መንገድ ላይ ለተደበደበው ግማሽ አካሉ ሞቶ የነበረውን ሰው የተንከባከበው እርሱ መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል።

"ይህ ምሳሌ ለእያንዳንዳችን በጣም ፈታኝ የሆነው ለምን እንደሆነ መረዳት እንችላለን" ያሉት ቅዱስነታቸው "ክርስቶስ ርህሩህ የሆነውን የእግዚአብሔርን ፊት ካሳየን በእርሱ ማመን እና የእርሱ ደቀ መዛሙርት መሆን ማለት ራሳችንን ለመለወጥ እና የእሱን ተመሳሳይ ስሜቶች ለመውሰድ መፍቀድ ማለት ነው" ብለዋል።

የሚንቀሳቀስ ልብ ይኑረን

ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህ ማለት የሚንቀሳቀስ ልብ እንዲኖረን ልባችንን ማሰልጠን ማለት ነው፣ ከእውነታው ለመሸሽ ዞር ብሎ የማያይ ዓይን፣ ሌሎችን የሚረዳ እና ቁስላቸውን የሚያረጋጋ እጆች፣ የተቸገሩትን ሸክም የሚሸከም ትከሻ እንዲኖረን መማር ማለት ነው ያሉ ሲሆን "ደጉ ሳምራዊ የምያስተምረን ክርስቶስ እንደሚወደንና እንደሚያስብልን በጥልቀት ከተገነዘብን እኛም በተመሳሳይ መንገድ መውደድ እና እንደ እርሱ ርኅሩኆች እንሆናለን" ብሏል።

"በክርስቶስ ከተፈወስን እና ከተወደድን በኋላ" ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እንዳሉት ከሆነ "እኛም በዓለማችን የእርሱ ፍቅር እና ርህራሄ ምስክሮች መሆን እንችላለን" ብለዋል።

"የፍቅር አብዮት"

ይህን በማሰብ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፣ “ዛሬ ይህ ‘የፍቅር አብዮት’ ያስፈልገናል ያሉ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ዛሬ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ የሚወርደው መንገድ ወደ ኃጢአት፣ መከራና ድህነት የሚወርዱ ሁሉ የሚሄዱበት መንገድ እንደሆነ ጠቁመዋል።

“መንገዱ በችግር የተከበበ ወይም በህይወት የተጎዳ ሁሉ...፣” “የሚወድቁ፣ ከፍተኛ ሸክም ሲኖረን እና ድንጋጤ በሚመታን ጊዜ ሁሉ...”፣ “በተገፉት፣ በተዘረፉት፣ በአምባገነናዊ የፖለቲካ ስርአቶች ሰለባ የሆኑ ህዝቦች፣ ለድህነት የሚያስገድዳቸው ኢኮኖሚ፣ ህልማቸውንና ህይወታቸውን በሚገድሉ ጦርነቶች የተከበቡ ሰዎችን ሁሉ ማገዝ ይኖርብናል ብለዋል።

ምን እናድርግ?

ስለዚህም ቅዱስ አባታችን "ምን እናድርግ?" የሚለውን ጥያቄ ያነሱ ሲሆን "እያየን እንሄዳለን ወይስ እንደ ሳምራዊው ለሌሎች ልባችንን እንከፍታለን? አንዳንድ ጊዜ የምንረካው ግዴታችንን ለመወጣት ብቻ ነው ወይንስ የቡድናችን ክፍል የሆኑትን፣ እንደ እኛ የሚያስቡትን፣ አንድ ብሔር ወይም ሃይማኖት የሚጋሩትን ብቻ እንደ ባልንጀሮቻችን አድርገን የምንመለከተው?" ሲሉ ጥያቄ አንስተዋል።

በመቀጠልም “ኢየሱስ ይህን አስተሳሰቡን የገለበጠው ሳምራዊ፣ ባዕድ ወይም መናፍቅ ተብሎ በጊዜው ይቆጠር የነበረው ሰው፣ ለዚያ የቆሰለ ሰው ባልንጀራ አድርጎ ሲያቀርብልን ነው” ሲሉ አስታውሷል፣ “እንዲሁም እንድናደርግ ይጠይቀናል ሲሉም አክለው ገልጸዋል።

በመጨረሻ ፍቅር ያሸንፋል ከክፉም ከሞትም የበለጠ ኃይል ይኖረዋል ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ይህንን ግብዣ አቅርበዋል፡- “ወደ ደጉ ሳምራዊ ወደ ክርስቶስ እንመልከት፣ ዛሬ ደግሞ ድምፁን እንስማ፤ ለእያንዳንዳችን፡- 'ሂዱና እንዲሁ አድርጉ ይለናልና' ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን አጠቃለዋል።

 

14 Jul 2025, 11:22