ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ፓክስ ክሪስቲ” ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ጸረ-አመፅ ጥረቱን እንዲያስፋፋ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ አሜሪካ ውስጥ የሚገኘው ብሔራዊ የ “ፓክስ ክሪስቲ” እንቅስቃሴ ዓለማችን ለበርካታ ፈተናዎች ማለትም ለጦርነት፣ ለሕዝቦች መከፋፈል እና ለግዳጅ ስደት በተጋረጠበት ወቅት ሰላምን ለማስፋፋት የሚያደረገውን ጥረት ይበልጥ እንዲያጠናክር በማለት የጉባኤውን ተሳታፊዎች አሳስበዋል።
የአሜሪካ ካቶሊካዊ ዓለም አቀፍ የሰላም እንቅስቃሴ በዲትሮይት ሚቺጋን በሚገኝ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ውስጥ ከሐምሌ 18-20/2017 ዓ. ም. ድረስ ባካሄደው ጉባኤ፥ “በተሰበረ ዓለም ውስጥ አመጽን የማስቀረት ኃይል መልሶ ማግኘት” በሚል ርዕሥ ውይይት ማካሄዱ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ዓርብ ምሽት በተካሄደው የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ በተነበበው መልዕክታቸው፥ የስቅለቱ ዓመፅ ከተፈጸመ በኋላ ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት የተናገረው የመጀመሪያ ቃል “ሰላም” የሚል እንደ ነበር አስታውሰው፥ ይህ ሰላም የመሣሪያ ትጥቅ የሌለበት እና መሣሪያ የታጠቁትን የሚያስፈታ ትሑት እና የጸና ሰላም መሆኑን እንዲያስታውሱ ጋብዘዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሰላም ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ወደ ዓለም መላክ መቀጠሉን በመልዕክታቸው ገልጸው፥ “ማስታረቅን የምታውቅ ቤተ ክርስቲያን በቁምስናዎች፣ በአጎራባች አካባቢዎች፥ በተለይም በማኅበረሰብ ዙሪያ መኖር ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ቅዱስነታቸው ብሔራዊ ጉባኤው የ “ፓክስ ክሪስቲ” እንቅስቃሴ አባላት የአካባቢያቸው ማኅበረሰቦች “የሰላም ቤት” ለማድረግ እንደሚሠሩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ይህም አንድ ሰው በውይይት አማካይነት ጠላትነትን እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል የሚማርበት፣ ፍትህ የሚተገበርበት እና ይቅርታ የሚከበርበት ነው” ብለው፥ የእንቅስቃሴው አባላት ይህን በማድረጋችው፥ ብዙ ሰዎች ከወንድሞቻቸው እና ከእህቶቻቸው ጋር በሰላም እንዲኖሩ የቅዱስ ጳውሎስን ግብዣ እንዲቀበሉ ያደርጋሉ” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ጉባኤውን ለቤተ ክርስቲያን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በአደራ ሰጥተው፥ ለጉባኤው ተሳታፊዎችም ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን በመስጠት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።
