ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የኢዮቤልዩ በዓል ለማክበር ወደ ሮም ለመጡት ወጣቶች አቀባበል ሲያደርጉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የኢዮቤልዩ በዓል ለማክበር ወደ ሮም ለመጡት ወጣቶች አቀባበል ሲያደርጉ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ “የካቶሊክ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በጦርነት በተበታተነ ዓለም ውስጥ የኅብረት መልዕክተኞ ናቸው"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀላቸው የኢዮቤልዩ በዓል ላይ ለተገኙት በመቶዎች ለሚቆጠሩ የካቶሊክ ዲጂታል ሚሲዮናውያን እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል። በብፁዕ ካርዲናል ታግለ መሪነት የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ለተካፈሉት ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት፥ የካቶሊክ ዲጂታል ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በጦርነት በተበታተነው ዓለም ውስጥ የአንድነት መልዕክተኞች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ወጣቶች በሦስት ቋንቋዎች ሰላምታ ካቀረቡላቸው በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት ወጣት ወንዶች እና ሴቶች በመካከላቸው ያለውን የመገናኛ “ኔትወርክ” እንዲጠግኑ እና በጦርነት ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች ሰላምን እንዲያውጁ አሳስበው፥ የእውነትን ውበት መናገር የሐሰት ዜና አመክንዮዎችን ለማሸነፍ ያግዛል ብለዋል።

የመገናኛ መረቦቹን መጠገን

ለሐዋርያቱ የቀረበላቸው የመጀመርያው ጥሪ የተበጣጠሱ መረቦችን ለመጠገን እጆቻቸውን በትዕግስት ማዘጋጀት እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ከሁለት ሺህ ዓመታት በኋላ የተፈጠርይት የዛሬዎቹ የመገናኛ መረቦች ፈውስ እንደሚሻቸው፥ ድረ ገጽ፣ ደካማ የግንኙነት እና የድምጽ ማስተላለፊያ መንገድ ዘወትር በጠላትነት እና በጦርነት የተበታተነች ዓለም ታሪክ እንደሚናገር ተገልጿል። በጦርነት የተበታተነ ዓለምን መጠገን ማለት ሰላምን ማወጅ፣ የተሰበረውን የሰው ልጅ ልብ መጠገን ማለት ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የዘመናችን የካቶሊክ ዲጂታል ሚሲዮናውያን እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የሰላም እና የአንድነት መልዕክተኞች እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።

የካቶሊክ ዲጂታል ሚሲዮናውያን እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ
የካቶሊክ ዲጂታል ሚሲዮናውያን እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ   (@Vatican Media)

የቅዱስነታቸው መልዕክት ለካቶሊክ ተጽእኖ ፈጣሪዎች እና ዲጂታል ሚሲዮናውያን የደረሳቸው በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፥ የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓልን ምክንያት በማድረግ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥር ዓት ማጠቃለያ ላይ እንደ ነበር ታውቋል።

ሰላም በልብ እና በድርጊት ውስጥ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ ሆነው በተመረጡበት ዕለት ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሰገነት ላይ ሆነው በአደባባዩ ለተሰበሰቡት በሺዎች ለሚቆጠሩ ምዕመናን ባሰሙት የመጀመሪያው ሰላምታ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” ማለታቸው ይታወሳል።

“ሰላምን ለዓለም ማወጅ የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣ ሰላም ሞትን የሚያሸንፍ፣ ይቅርታን የሚያመጣ፣ ሕይወትን የሚሰጥ እና የፍቅር መንገድን የሚያሳይ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ተስፋን ማሳደግ

የተፅእኖ ፈጣሪዎች ተልዕኮ፥ “ማኅበራዊ አውታረ መረቦችን እና ዲጂታል መገናኛዎችን በክርስቲያናዊ ተስፋ መመገብ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ሰላምን በየቦታው መፈለግ፣ መመስከር፣ ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች እና በሕይወት የመኖር ትርጉም በጠፋባቸው ሰዎች ልብ ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለወጣቶች ሰላምታ ሲያቀርቡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለወጣቶች ሰላምታ ሲያቀርቡ   (@Vatican Media)

ተስፋን እስከ ዓለም ዳርቻ መመስከር

“ሚስዮናውያን ደቀ መዛሙርት ከምን ጊዜውም በላይ ዛሬ የኢየሱስ ክርስቶስን ሕያው ተስፋ እስከ ምድር ዳርቻ ማድረስ ያስፈልጋል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ተስፋ በድንበር ሳይገደብ ወደ ዓለም ዳርቻዎች በሙሉ መድረስ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ፈጠራ ችሎታን ማሳደግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የዲጂታል ሚስዮናውያን ሁለተኛው ፈታኝ ተግባር፥ የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ በባልጀራ ሰው ውስጥ መፈለግ እንደሆነ ተናግረው፥ በተጨማሪም ይህን የሰው ልጅ መከራ በጥልቅ ምልክት እና በቴክኖሎጂ በተገነባ የዛሬው ባሕል ውስጥ ማግኘት እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ሰላምታ ሲያቀርቡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ሰላምታ ሲያቀርቡ   (@Vatican Media)

ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በአኗኗራችን እና ከዓለም ጋር በሚኖረን ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ በራሳችን ላይ፣ ከሌሎች እና ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ አስረድተው፥ ተልዕኮአችን ክርስቲያናዊ ባሕልን በጋራ ማሳደግ እንደሆነ እና የ “ኔትወርክ” ውበትም ይህ እንደሆነ አስረድተዋል።

የዘመናችን ቋንቋ ማዳበር

“የሰውን ልጅ በታሪክ ውስጥ ጥልቅ የሆነ የባሕል ለውጥ ሲያጋጥመው ይህ የመጀመሪያው አይደለም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እንዲህ ዓይነት ሽግግር ሲያጋጥማት ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ ማስተዋል እና ብርሃንን ለማግኘት እንደምትጥር ገልጸው፥ በእነዚህ አዳዲስ ተግዳሮቶች መካከል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሠራሽ አስተውሎት አንዱ እንደሆነ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

“ጭምብሎችን” ማስወገድ

በበይነ-መረብ ላይ መገኘት የሚለካው በይዘት ማመንጨት ብቻ ሳይሆን ልብ ለልብ መገናኘትን ማሳደግ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ “በዚህ መንገድ ስቃይ ውስጥ የሚገኙትን እና እግዚአብሔርን ለማወቅ የሚፈልጉትን መርዳት እንችላለን፣ ቁስላቸው ሊድን ይችላል” ብለዋል።

በዚህ መንገድ ሁሉም ሰው በእግሩ ሊቆም እና የሕይወት ትርጉምን ማግኘት እንደሚችል፥ ነገር ግን ሁሉም ከጋራ ጥረት የሚመጣ፣ የራስን አቅመ ደካማነት ከመቀበል የሚጋርደንን እያንዳንዱን “ጭንብል” ከማስወገድ እና የወንጌልን ውስጣዊ ፍላጎት ከመገንዘብ የሚመጣ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ለካቶሊክ ዲጂታል ሚሲዮናውያን እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ሰላምታ ሲሰጡ
ለካቶሊክ ዲጂታል ሚሲዮናውያን እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ሰላምታ ሲሰጡ   (@Vatican Media)

ነጻ የሚያወጡ እና የሚያድኑ አውታረ መረቦች

ጓደኝነትን መፍጠር የሚቻልባቸው ትክክለኛ የእርስ በርስ መገናኛ፣ የፍቅር እና የነጻ መጋራት አውታረ መረቦች እንደሚያስፈልጉ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የተበላሹ ነገሮችን የምንጠግንባቸው፣ ከብቸኝነት የምንፈውስባቸው የተከታዮችን ብዛት በመቁጠር ሳይሆን በእያንዳንዱ ገጠመኝ ውስጥ የማያልቅ የፍቅር ታላቅነትን የሚለማመዱባቸው፣ ከራስ ይልቅ ለሌሎች ቦታ የሚሰጡ እያንዳንዱ የጋራ መልካም ታሪክ የሚነገርባቸው፣ እውነት የሚመሰከርባቸው የእግዚአብሔር አውታረ መረቦች እንደሚያስፈልጉ አስረድተዋል።

በዲጂታል ጎዳናዎች ላይ መጓዝ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የካቶሊክ ዲጂታል ሚሲዮናውያን እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የኅብረት መልዕክተኞች እንዲሆኑ በጥብቅ በማሳሰብ፥ ከግለኝነት እና ከራስ ወዳድነት ይልቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማትኮር ዓለምን እና የውሸት ዜና አመክኖን በማሸነፍ ለኢየሱስ ክርስቶስ እና ለቤተ ክርስቲያን ላሳዩት ፍቅር፣ የተሰቃዩት በመርዳት ላደረጉት የዲጂታል ጉዞ  እና ህልም በማመስገን መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከፊሊፒን ለመጡት ወጣቶች ሰላምታ ሲሰጡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከፊሊፒን ለመጡት ወጣቶች ሰላምታ ሲሰጡ   (@Vatican Media)

 

30 Jul 2025, 16:28