ፈልግ

ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ አያቶች እና አረጋውያን የተስፋ ምስክሮች መሆናቸውን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለ5ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀንን ካስታወሱ በኋላ የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ለማክበር ወደ ሮም ለመጡ የተስፋ ነጋዲያን ወጣቶች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ እሁድ ሐምሌ 20/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአክ እግዚአብሔር ጸሎት አቅርበዋል።


ቅዱስነታቸው ከጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ በኋላ ለምዕመናኑ ባደረጉት ንግግር፥ “ተስፋን የማያጣ የተባረከ ነው” በሚል መሪ ርዕሥ፥ አምስተኛው ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን የሚከበር መሆኑን በማስታወስ የዘንድሮ መልዕክታቸውን አውጥተዋል።

ቅዱስነታቸው አምስተኛውን ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን በማስታወስ ይፋ ባደረጉት መልዕክት፥ “ለአዳዲስ ትውልዶች መንገድ እና ብርሃን መሆን የሚችሉ አያቶችን እና አረጋውያንን የተስፋ ምስክሮች አድርገን እንመልከታቸው” ብለው፥ “ብቻቸውን ሳንተዋቸው ነገር ግን በፍቅር እና በጸሎት ቃል ኪዳን እንቀላቅላቸው” ብለዋል።

የወጣቶች ኢዮቤልዩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በዓለም ዙሪያ በጦርነት በሚሰቃዩ አገራት ዘንድ ሰላም እንዲሰፍን ካቀረቡት ጸሎት በመቀጠል ከሰኞ ሐምሌ 21-25/2017 ዓ. ም. ድረስ የሚከበረውን የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ አገሮች ወደ ሮም ለመጡ ወጣቶች ሰላምታን በማቅረብ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ወጣቶች ባደረጉት ንግግር፥ ይህ አጋጣሚ እያንዳንዳችሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንድትገናኙ፣ በእርሱ ላይ ባላችሁ እምነት እንድትበረቱ እና ንጹሕ ሕይወት ለመከተል ባላችሁ ቁርጠኝነት እንድትበረቱ ዕድል እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

 

28 Jul 2025, 17:17