ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የጋዛ ንጹሃን ዜጎች ለረሃብ በመጋለጣቸው የተሰማቸውን ከፍተኛ ስጋት ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ልባቸው በጦርነት ምክንያት ለሚሰቃዩ ሰዎች ቅርብ እንደሆነ ገልጸው፥ በዓለማችን ውስጥ በግጭቶች እና በአመጾች ምክንያት የሚሰቃዩ በርካታ ሰዎችን በማስታወስ፥ የዓለም መሪዎች መከራው የሚወገድበትን መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በታይላንድ እና በካምቦዲያ ድንበር አካባቢ በተፈጠረው ግጭት ለተጎዱት በተለይም ለሕፃናት እና ተፈናቃይ ቤተሰቦች እንዲሁም በደቡብ ሶርያ ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት ሰለባ የሆኑትን በጸሎታቸው አስታውሰው፥ “የሰላም አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉም ሰው የውይይት እና የእርቅ ፍላጎት እንዲኖረው በማለት በጸሎት ጠይቀዋል።
ቅዱስነታቸው ለጋዛ ሕዝብ ያላቸው ጥልቅ ስጋት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ እሑድ ዕለት ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ የዓለም ሕዝብ የጋዛ ሆስፒታሎችን ያጠበቡ እና በረሃብ ምክንያት እጅግ የከሱ ሕጻናት ምስሎችን ባየበት ሳምንት ውስጥ እስራኤል የምግብ ዕርዳታ ጭነቶች ወደ ጋዛ እንዳይገባ በማድረጓ ብዙ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
ጋዛ ውስጥ ያለውን እጅግ አሰቃቂ ሰብዓዊ ቀውስን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ሲቪሎች በረሃብ እየተሰቃዩ ለጥቃት እና ለሞት መጋለጣቸውን እና በአካባቢው ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል።
የቅዱስነታቸው የሰላም ጥሪ
ቅዱስነታቸው ተኩስ እንዲቆም፣ ታጋቾች እንዲፈቱ እና ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግ ሙሉ በሙሉ እንዲከበር ልባዊ ጥሪ ማቅረባቸውን ተናግረው፥ “እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር በራሱ የተሰጠ ክብር አለው” ሲሉ አስረድተዋል።
“እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር የተሰጠው ውስጣዊ ክብር አለው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የፖለቲካ መሪዎች የሰላም ጥሪያቸውን እንዲቀበሉ አሳስበው፥ “በእያንዳንዱ ግጭት ውስጥ የተሰማሩ ወገኖች ይህንን ሰብዓዊ ክብር እንዲገነዘቡት እና ከክፉ ድርጊቶቻቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ለሕዝቦች ሰላምን በሚያመጡ ውይይቶች ላይ በማትኮር እና ይህን ጥረት የሚከለክል ማንኛውንም ሃሳብ መቀበል እንደማይገባ አሳስበው፥ የሰላም ንግሥት ወደ ሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባቀረቡት ጸሎት፥ “የግጭት ሰለባ የሆኑትን ንጹሐን ሰዎችን እና ጦርነትን ወደ ፍጻሜ ለማድረስ ኃይል ያላቸው መሪዎችን በአደራ እንድትቀበል ተማጽነዋል።
