ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ ከዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት መሪዎች እና ከቅዱስ ዛቪዬር ማኅበር ሚሲዮናውያን ጋር ር. ሊ. ጳ. ሊዮ ከዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት መሪዎች እና ከቅዱስ ዛቪዬር ማኅበር ሚሲዮናውያን ጋር  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ከኢየሱስ ጋር መወዳጀት ለክርስቲያናዊ ደስታ ቁልፍ እንደሆነ አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የዘርዓ ክኅነት መሪዎችን እና የቅዱስ ዛቪዬር ማኅበር ሚሲዮናውያንን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለእንግዶቹ ባሰሙት ንግግር፥ “ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለውን ወዳጅነት መንከባከብ፣ የእርሱን ቅርበት እና ፍቅር መለማመድ ለካኅናት እና ምዕመናን ደስታ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ይህን የተናገሩት፥ የዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት መሪዎችን እና የቅዱስ ዛቪዬር ማኅበር ሚሲዮናውያንን ዓርብ በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ እንደ ነበር ታውቋል።  

“ከኢየሱስ ጋር ያለውን ወዳጅነት መንከባከብ እጅግ አስፈላጊ ነው!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ይህን መልዕክት ያስተላለፉት፥ በሮም በሚገኝ የ“ሬጂና አፖስቶሎረም” ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተዘጋጀውን ስልጠና ተከታትለው ለፈጸሙት የዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት መሪዎች እና የማኅበራቸውን ጠቅላላ ጉባኤ በሮም ያካሄዱ የቅዱስ ዛቪዬር ማኅበር ሚሲዮናውያንን ዓርብ ሐምሌ 18/2017 ዓ. ም. በቫቲካን በተቀበሏቸው ወቅት ነው።

ለዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት መሪዎች የተዘጋጀው ስልጠና እና የቅዱስ ዛቪዬር ማኅበር ሚሲዮናውያን ጠቅላላ ጉባኤ ሁለት የተለያዩ ክስተቶች ናቸው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ነገር ግን አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ ተልዕኮ እንዳላቸው፥ “ይህም በተለያየ መንገድ ወደ ተልዕኮ እንዲገቡ እና የወንጌል ምስክርነት ጥሪን እንዲወጥ የተጠሩ በመሆናቸው ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚመሳሰል አስተሳሰብ መያዝ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ከሁላችን የሚፈለገው ይህ አስደናቂ ጥሪ፥ የተቀቡት አገልጋዮች ሆኑ ምዕመናን በልዩ ዕውቀት ብቻ ሳይደገቡ ነገር ግን ሰብዓዊነታችንን እና መንፈሳዊነታችንን በሚለውጥ ጽኑ ዓላማ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ተመሳሳይ አስተሳሰብ ይዘን በቅዱስ ወንጌል ላይ እንድናስተነትን የሚያደርገን ጥሪ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው በዚህ ጉዳይ ላይ ለማሰላሰል የሚያግዙ አንዳንድ ሃሳቦችን አቅርበው፥ ይህን ከመሰለ ተነሳሽነት ጋር በቅድስት መንበር የሀገረ ስብከት ካኅናት ጉዳይ የሚከታተል ጳጳሳዊ ምክር ቤት “ደስተኛ ካህናት” በሚል መሪ ርዕሥ በቅርቡ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ለካህናት ማዘጋጀቱን አስታውሰዋል።

“ይህን የወንጌል አገልግሎት አስደናቂ ጥሪ በወንጌል ደስታ ውስጥ ማካተት እንችላለን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “ይህ ጥሪ ለካህናት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው መሳተፍ የሚችልበት እንደሆነ ገልጸው፥ ይህን ከፈጸምን ስለ ደስተኛ ክርስቲያኖች፣ ስለ ደስተኛ ደቀ መዛሙርት እና ስለ ደስተኛ ሚስዮናውያን መናገር እንችላለን” ብለዋል።

የክርስቲያን ‘ቤት’ ‘በአለት’ ላይ መመስረት አለበት!

ይህ ተስፋ ከንቱ ሆኖ መቅረት ከሌለበት ወጣቶችን ለወንጌል አገልግሎት ማዘጋጀት ወይም ማነጽ አስፈላጊ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “በዚህም መሠረት የካኅናትን ሆነ የምዕመናንን ሕይወት በአለት ላይ የመመሥረት አስፈላጊነት በማብራራት፣ የክርስቲያኖች፣ የካኅናት እና የወንጌል ሰባኪዎች ሕይወት ከሰብዓዊ እና መንፈሳዊ ማዕበል ነፃ የሚሆንበት ጊዜ አለመኖሩን አስረድተዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስን ቅርብነት እና ፍቅር የመለማመድ አስፈላጊነት

“ቤታችንን በዓለት ላይ ለመገንባት” የሚያስችሉ ሦስት አጫጭር ምክሮችን የለገሡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የመጀመሪያው “ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወዳጅነትን መመሥረት፣ ይህም የ “ቤቱ” መሠረት ኢየሱስ  መሆን እንዳለበት፣ የእያንዳንዱ ጥሪ እና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መሠረት ኢየሱስ መሆን እንዳለበት አስታውሰዋል።

በግል የኢየሱስ ክርስቶስን ቅርብነት መለማመድ ይገባናል ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ መታየታችንን፣ መወደዳችንን እና መመረጣችንን የምናውቀው ለስጦታው ተገቢ ሆነን ሳይሆን በአገልግሎታችን ውስጥ በምናሳየው እና ከግል ተሞክሮአችን በላይ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ሌሎችን ለክኅነት ሕይወት ስናዘጋጅ እና እንደ ጥሪያችን በተላክንባቸው አገራት ወንጌልን ስንሰብክ በቅድሚያ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በግል ያለንን የወዳጅነት ልምዳችንን በአኗኗራችን፣ በአመለካከታችን፣ በሰውነታችን እና ጤናማ ግንኙነቶችን ለመምራት በምንችልበት መንገድ እናሳያለን” ብለዋል።

በራሳችን ላይ ያለማቋረጥ መሥራት አለብን!

ቅዱስነታቸው በዚህ መሠረት ወንጌልን መመስከር ቀዳሚ ምስክርነት እንደሆነ አስረድተው፥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በግል መገናኘት ቀጣይነት ያለው የለውጥ ጉዞ የሚያስፈልገው መሆኑን በማሳሰብ፥ “በራሳችን ላይ ዘወትር መሥራት አለብን” ብለዋል።

በላያችን ላይ ያለውን ጥላ እና ቁስል፣ ልባችንንም ለመመልከት የተቀናጀ ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፥ ከዚያም የሚጋርደንን “ጭምብል” አውልቀን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ድፍረት ሊኖረን ይገባል ብለው፥ በዚህ የወንጌል ሕይወት ተለውጠን እውነተኛ ወንጌላዊ መሆን እንችላለን ብለዋል።

ሁለተኛው ሃሳብ፥ “በመካከላችን ውጤታማ እና አፍቃሪ የወንድማማችነት ሕይወትን ማኖር ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በዚህ ረገድ ግለኝነትን እና ሌሎችን ለመጫን ያለንን ፍላጎት ማሸነፍ እንድንችል በራሳችን ላይ ጠንክረን መሥራት አለብን ብለው፥ ይልቁንም ጤናማ እና ወንድማማችነት ያለበት ሰብዓዊ እና መንፈሳዊ ግንኙነቶችን ቀስ በቀስ መገንባትን መማር እንደሚያስፈልግ ተናግረው፥ በመርህ ደረጃ በእውነታው ሁሉም ሰው የሚስማማ ቢሆንም ነገር ግን አሁንም ብዙ እንደሚቀረው ተገንዝበዋል።

ካህናት ብቻቸውን አይደሉም!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመጨረሻም፥ ሦስተኛው ገጽታ “የወንጌል ተልዕኮን ምስጢረ ጥምቀትን ከተቀበሉት ሁሉ ጋር መጋራ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጸው፥ “ካህናትም በዚህ መሰልጠን እንዳለባቸው እና “ራሳቸውን እንደ ብቸኛ መሪዎች አድርገው መቁጠር ወይም የተሾሙትን የክህነት ሥልጣንን በበላይነት መመልከት የለባቸውም” ሲሉ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “የምእመናንን የጥምቀት ጸጋ እና ከውስጡ የሚፈሱትን ተነሳሽነቶችን ማስተዋል እና ማድነቅ የሚችሉ ካህናት ያስፈልጉናል” ብለው፥ ለእነዚህ ሥጦታዎች ራሳቸውን እንዲከፍቱ፥ “ለቤተ ክርስቲያን እና ለኅብረተሰብ አገልግሎት ራሳቸውን ለመስጠት ድፍረት እና ጉጉት ያላቸው ካህናት ያስፈልጉናል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በተጨባጭ መንገድ እንዳብራሩት፥ “የወደፊቱ የካህናት ዝግጅት ከጊዜ ወደ ጊዜ በእግዚአብሔር ሕዝብ እውነታ ውስጥ የጠለቀ እና በአባላቶች ማለትም በካህናት፣ በምእመናን እና በገዳማውያን እና ገዳማውያት ዝግጅት መከናወን አለበት” ብለዋል።

መልዕክታቸውን ከማጠቃለያቸው በፊት እንደተናገሩትም፥ ለዚህ አብሮ የመሆን ዕድል፥ ከእርሳቸው በፊት የነበሩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን አመስግነው፥ “ከሁሉም በላይ በበርካታ አገሮች ውስጥ ለወንጌል ተስፋ ስትሉ በካኅናት ዝግጅት እና በወንጌል ምስክርነት ወቅት የተሰቃያችሁ እና የቆሰላችሁ ሚስዮናውያን በሙሉ ጉዟችሁን በድፍረት እንድትቀጥሉ” በማለት አበረታተዋቸዋል።

 

26 Jul 2025, 16:47