ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “የኢየሱስ ክርስቶስ ጥበብ ለተማሪዎች አቅጣጫ ጠቋሚ ሊሆን ይገባል” አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለዓለም አቀፍ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ፌዴሬሽን መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፥ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች የእውነተኛ ጥበብ ምንጭ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ጸንተው እንዲቆሙ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ሰኞ ሐምሌ 21/2017 ዓ. ም. በሜክሲኮ ጓዳላጃራ በተካሄደው 28ኛው ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ዩኒቨርስቲዎች ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለተገኙት ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች በዓለማችን ላይ ስላላቸው ሚና በማሰላሰል፥ የጥበብ እና የእውነት ምንጭ በሆነው በኢይሱስ ክርስቶስ ላይ ሥር እንዲሰድዱ አሳስበዋል።

ጉባኤው “የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች የእውቀት ጠንሳሾች” በሚል መሪ ሃሳብ በመካሄድ፥ የካቶሊክ ዩኒቨርስቲዎች ፌዴሬሽን ምሥረታ መቶኛ ዓመት ያከበረ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ይህን ጭብጥ በመጥቀስ፥ “ስምምነትን፣ አንድነትን፣ አዳዲስ ሃሳብን እና ደስታን የሚያመነጭ መልካም አገላለጽ ነው” ብለዋል።

ዩኒቨርስቲዎች ወደ እግዚአብሔር የሚወስዱ የአዕምሮ መንገዶች ናቸው

“የዘመኑ ባህል በአደጋ ማሳሰቢያ ዘፈኖች የተሞላ ነው” በማለት ያስጠነቀቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “የዘመኑ ባህል አዲስነቱን፣ ታዋቂነቱን ወይም ግልጽ በሆነ መንገድ የሚስቡ ሃሳቦችን የያዘ እንደሆነ ገልጸው፥ በአንጻሩ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች የቅዱስ ቦናቬንቸርን ሐሳብ በማስተጋባት አእምሮን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ለመውሰድ የተገነቡ መንገዶች ለመሆን ተጠርተዋል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ቅዱስ አጎስጢኖስን እና ቅዱስ ጳውሎስን ጨምሮ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባቶች በመጥቀስ፥ ካቶሊካዊ ተቋማት በመለኮታዊ እውነት ላይ እውቀትን በማስቀመጥ የሰውን መንፈስ ለማብራት ዘላቂ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ቅዱስ አጎስጢኖስን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ “በራሷ የተተወች ነፍስ ብርሃንም ሆነ ጥንካሬ የላትም” ብለው፥  “ከማይለወጥ የእውነት ምንጭ ስትርቅ ትጨልማለች፥ ስትርቀርብ ታበራለች” ብለዋል።

ከዚህ አንፃር የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በውይይት እና በዕውቀት ብዝሃነት ተለይቶ የሚታወቀው ለቤተ ክርስቲያን ካለው ተልዕኮ የራቀ አለመሆኑን እንደሆን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አረጋግጠዋል።

በተለያዩ ዕይታዎች ውስጥ ራስን ማሳተፍ

ከመጀመሪያዎቹ የስብከተ ወንጌል ጊዜያት ጀምሮ ክርስቲያኖች ከተለያዩ የዓለም አመለካከቶች ጋር የመሳተፍን አስፈላጊነት ተረድተዋል። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ የሮም ክርስቲያኖች የቀድሞ አኗኗራቸውን ፍሬ እንዲመረምሩ እንደመከራቸው አስታውሰው፥ የሰው ጥበብ ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሞት እንደሚመራ አስረድተዋል።

“ኢየሱስ ክርስቶስ ለምክንያታዊ ንግግሮች እንግዳ አይደለም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ይልቁንስ ሕይወትን ለማሻሻል እና ዓላማን ለማግኘት፣ ለሁሉም ሃሳቦቻችን፣ የተስፋዎቻችን እና የጥረቶቻችን ቅንጅት ትርጉም የሚሰጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቅዱስ ቶማስ አኳይነስ ሃሳብ ላይ በማሰላሰል እንደተናገሩት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ጥበብ የእምነት ማዕከል እና ለዓለም አቀፋዊ የሰው ልጅ አስተሳሰብ ተደራሽ መሆኑን አመላክተዋል።

“በዓረፍተ ነገሮች ላይ አስተያየት መስጠት” የሚለውን የቅዱስ ቶማስ አኳይነስ ሃሳብ በመጥቀስ፥ ጥበብ እንደ ተፈጥሮ ምሁራዊ አቅም ወይም እንደ መለኮታዊ ስጦታ የምትታይ፣ “ከሁሉም መለኮታዊ ጉዳዮች በላይ የምታስብ እና ከሁሉም ባሕሎች እና የአስተሳሰብ ትምህርት ቤቶች ጋር ለመነጋገር ጠንካራ መሰሠረት እንደምትሆን አጽንኦት ሰጥተዋል።

የክርስትና ማንነት ጥንካሬ

የካቶሊክ ዩኒቨርስቲዎች እራሳቸውን ከኢየሱስ ክርስቶስ ማራቅ ወይም በምሁራዊ ንግግር ስም ያለውን ልዩ ሚና ማነፃፀር እንደሌለባቸው አስረግጠው፥ ይልቁንም ከክርስቲያናዊ ማንነት ጥንካሬያቸው በመነሳት ሁሉንም የእውቀት ወጎች በአክብሮት እና ፍሬያማ በሆነ መንገድ መሳተፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ጥበብ፣ እውነት፣ ሰው እና መላውን ዓለም ወደ ራሱ የሚስብ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁሉም የካቶሊክ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አቅጣጫን የሚጠቁም መሪ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለው ፍቅር በካቶሊክ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ለወንጌል ምስክርነት አዲስ መነሳሳትን እንዲያመጣ” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በሜክሲኮ ጓዳላጃራ በተካሄደው 28ኛው ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ዩኒቨርስቲዎች ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለተገኙት እና ለሚወክሏቸው ተቋማት በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል።

 

29 Jul 2025, 17:26