ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ እግዚአብሔር ለቤተሰቦች ፍጹም አርአያ የሚሆን ቅዱስ ቤተሰብን እንደሰጠ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “እግዚአብሔር በችግር ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን ለመርዳት ብሎ ቅዱስ ቤተሰብን ፍጹም አርአያ አድርጎ አቅርቦላቸዋል” ሲሉ፥ በያዝነው የኢዮቤልዩ ዓመት የላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት (CELAM) የቤተሰብ የወደፊት ዕጣ ፈንታን በማስመልከት ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ የተገኙትን ዓርብ መስከረም 9/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ ተቀብለው ባደረጉት ንግግር ገልጸው፥ ንግግራቸውም ኢዮቤልዩ፣ ተስፋ እና ቤተሰብ በሚሉ ሦስት ቃላት ላይ ያተኮረ እንደ ነበረ ተመልክቷል።
የወላጆቻችን እና የአያቶቻችን እምነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ እንደተጠቀሰው፥ ኢዮቤልዩ “መመለስን” እንደሚያስታውሰን በመግለጽ፥ “እንደዚሁም ዛሬም ይህ ‘መመለስ’ የሕይወታችን ማዕከል ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር አብ፣ ወደ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እንድንመለስ የሚጋብዝ ጥሪ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ የተስፋ ኢዮቤልዩ ከእግዚአብሔር ርቀን ከምንገኝበት ቦታ ወደ መሠረቶቻችን እንድንመለስ የሚጋብዘን በመሆኑ፥ ማለትም ከወላጆቻችን ወደ ተቀበልነው እምነት፣ ሴት አያቶቻችን ሳያቋርጡ የመቁጠሪያ ጸሎትን በማቅረብ በርካታ ቤተሰቦችን እና ማኅበረሰቦችን ወደ ደገፉበት ቀላል፣ ትሁት እና ቅን ሕይወት እንድንመለስ የሚጋብዘን መሆኑን በመደነቅ ተናግረዋል።
እውነተኛ ደስታችንን የምናገኘው በኢየሱስ ነው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ እውነተኛ ደስታን እንደምናገኝ በድጋሚ በማረጋገጥ እርሱ መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት መሆኑን እንማራለን” ብለዋል። “በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ እውነተኛ ደስታን እናገኛለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ መሆን በምንፈልግበት ቤት መሆናችንን ስናውቅ ደስታን እናገኛለን” ሲሉ አስምረውበታል፣
የተስፋ ኢዮቤልዩ ከእውነት ጋር የምንገናኝበት ጉዞ እንደሆነ በማስታወስ እርሱም ራሱ እግዚአብሔር ነው” ሲሉ አስረድተው፥ “ሕይወታችንን በሰዎች ላይ እና ዓለማዊ በሆኑ ምኞቶች ላይ መገንባት አደጋ ላይ ይሚጥል ነው” በማለት አስጠንቅቀዋል።
በተጨማሪም ድህነት፣ ስደት እና ሁከትን ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ ቤተሰቦችን እያጋጠሙ ያሉትን እውነተኛ ተግዳሮቶች አስታውሰው፥ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ መንግሥታዊ ተቋማት የቤተሰብን ሕይወት እንዲደግፉ እና እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
ለቅዱስ ዮሴፍ እንዳደረገው ሁሉ...
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በዚህ ዐውድ ውስጥ ቤተሰብ ሁለቱንም ማለትም ስጦታ እና ሃላፊነት መሆናቸውን በመግለጽ፥ እግዚአብሔር ለቅዱስ ዮሴፍ እንዳደረገው ሁሉ፥ “በእያንዳንዱ ሕፃን፣ በእያንዳንዱ ባል ወይም ሚስት በኩል ልጁን ኢየሱስ ክርስሮስን እና እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን በአደራ ሰጠን” ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ለናዝሬት ምእመናን ያስተላለፉትን መልዕክት በማስታወስ፥ ምዕመናን በሙሉ የቅዱስ ቤተሰብን ምሳሌ እንዲከተሉ፣ እርስ በርስ በመደጋገፍ፣ በዝምታ፣ በሥራ እና በጸሎት፣ እግዚአብሔር ያዘጋጀላቸውን የፍቅር ዕቅድ በእያንዳንዱ ሰው እንዲፈጽምላቸው” በማለት አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመልዕክታቸው፥ “ይህ ፍቅር በጥምቀት ከእምነት በተወለደ ሕይወት ውስጥ ሥጋ የሚሆን እና ይህን የጸጋ ዓመት ለሰዎች ሁሉ ለማወጅ የተቀባ ነው” ብለዋል።
ቅዱስ ቤተሰብ እግዚአብሔር የሚሰጠን ፍጹም አብነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመጨረሻም፥ የስብሰባው ተሳታፊዎች ሐሳብን ለቅዱስ ቤተሰብ አማላጅነት በአደራ በመስጠት፥ የቅዱስ ቤተሰብ ፍጹም አብነት ስጦታ እግዚአብሔር ከቤተሰቦች ለሚሰነዘር ተስፋ አስቆራጭ ጩኸት የሚሰጠው ምላሽ እንደሆነ በማስረዳት፥ ይህን ስጦታ በመምሰል ቤቶቻችንም የእግዚአብሔር ብርሃን ሕያው ምስክሮች ይሆናሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
