ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ከአርሜኒያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ካሬኪን ጋር ሲገናኙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ከአርሜኒያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ካሬኪን ጋር ሲገናኙ  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ከአርሜኒያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ካሬኪን ጋር ተገናኙ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በቅድስት መንበር የአርሜኒያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ከብጹዕ ወቅዱስ ካሬኪን ዳግማዊ ጋር በካስቴል ጋንዶልፎ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የመላዋ አርመን ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ካሬኪን ዳግማዊን ማክሰኞ መስከረም 6/2018 ዓ. ም. ማለዳ ለመጀመሪያ ጊዜ በካስቴል ጋንዶልፎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ተቀብለዋል።

ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ዳግማዊ ለከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪነት ከተመረጡበት ከሃያ አምስት ዓመታት ወዲህ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ተገናኝተው እንደ ነበር ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እና ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ዳግማዊ የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች በማስመልከት ያደረጉት ውይይት፥ በወንድማማችነት እና በአክብሮት መንፈስ እንደ ነበር ታውቋል።

የአርመኒያው ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ካሬኪን ዳግማዊ በውይይታቸው፥ በአርሳክ ክፍለ ሀገር የሚገኙ አርሜኒያውያን ዕጣ ፈንታ ላይ አጽንኦት መስጠታቸውን በቅድስት መንበር የአርመን ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ካጃግ ባርሳምያን ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት የስልክ ቃለ ምልልስ አብራርተዋል።

ፓትርያርኩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ አርመንን እንዲጎበኙ ግብዣ ማቅረባቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባርሳሚያን ገልጸው፥ ሁለቱም የቤተ ክርስቲያን መሪያዎች በውይይታቸው የሰላምን አስፈላጊነት ያረጋግጡ ሲሆን፥ በፍትህ ላይ የተመሠረተ ሰላም እንደሚያስፈልግ ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ዳግማዊ አጽንዖት ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥  ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ጋር  ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ   (@Vatican Media)

ወደ ነፍስሔር ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ መካነ መቃብር የተደረገ ጉብኝት

ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ዳግማዊ ወደ ሮም ባደረጉት ጉብኝት አብረዋቸው የነበሩት የልዑካን ቡድን አባላትም የተገኙ ሲሆን፥ ወደ ቫቲካን አቅንተው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር ከተገኙት በኋላ ከከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት መሪዎች ጋርም ተገናኝተዋል።

በጉብኝታቸው ወቅት ከብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፥ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት እና ከብጹዕ ካርዲናል ቶሌንቲኖ ዴ ማንዶካ፥ በቅድስት መንበር የባሕል እና የትምህርት ጉዳዮች ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

በዕለቱ መርሐ ግብር መሠረት በሮም ውስጥ ወደሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካን የጎበኙ ሲሆን፥ ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ዳግማዊ ከእርሳቸው ጋር የውይይት እና የወዳጅነት መንገድ የፈጠሩትን ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በማስታወስ፥ በባዚሊካው ውስጥ ወደሚገኝ መካነ መቃብራቸው ፊት ቀርበው በጸሎት አስታውሰዋቸዋል።

ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ዳግማዊ በቅድስት ማርያም ባዚሊካ ውስጥ በሚገኝ የር ዕሠ ሊቅነ ጳጳሳት መካነ መቃብራቸው ፊት ቀርበው ሲጸልዩ
ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ዳግማዊ በቅድስት ማርያም ባዚሊካ ውስጥ በሚገኝ የር ዕሠ ሊቅነ ጳጳሳት መካነ መቃብራቸው ፊት ቀርበው ሲጸልዩ

ቀደም ሲል ወደ ቫቲካን ያደረጓቸው ጉብኝቶች

በቅድስት መንበር የአርሜኒያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ካሬኪን ዳግማዊ ሮምን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኙት እንደ ጎርጎርሳውያኑ ከህዳር 9-10/2000 ዓ. ም. እንደ ነበር ይታወሳል። ይህም የአርሜኒያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው በተመረጡበት እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2000 ዓ. ም. የኢዮቤልዩ በዓል እንግዳ አድርገው በጋበዟቸው ወቅት እንደ ነበር ይታወሳል።

በዚያ ጉብኝት ወቅት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት 12/1970 ዓ. ም. በቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እና በብፁዕ ወቅዱስ ቫስኬን ቀዳማዊ የተፈረመውን የጋራ መግለጫ ተከትሎ፥ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ሙሉ ህብረት ወደ ነበረበት ለመመለስ የተደረገው ስምምነት አሁንም የቀጠለ መሆኑ ታውቋል።የጋራ መግለጫው፥ “በቅድስት ሥላሴ እና የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ በሆነው እና እኛን ለማዳን ሰው በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን። በተጨማሪም በአንዲ፣ ካቶሊካዊት፣ ሐዋርያዊት እና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን። ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስ አካል እንደመሆኗ መጠን አንዲት እና ብቸኛ ናት። ይህ በሐዋርያት እና በቤተ ክርስቲያኑ አባቶች ትምህርት ላይ የተመሠረተ የጋራ እምነት ነው” ሲል ገልጿል። “በመካከላችን ሙሉ እና የሚታይ ኅብረት እንዲኖረን መጸለያችንን እንቀጥላለን” በማለት “የጋራ ተልዕኮአችን ሐዋርያዊ እምነትን ለማስተማር እና ለሰው ልጆች ሁሉ በተለይም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚኖሩት የክርስቶስን ፍቅር መመስከር” መሆኑን መግለጫው አረጋግጧል።

በዚያ ጉብኝት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ዳግማዊ የቅዱስ ጎርጎርዮስ አብርኆት ንዋያተ ቅድሳትን ማበርከታቸው ሲታወስ፥ ከአንድ ዓመት በኋላ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከመስከረም 25-27/2001 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በአርሜኒያ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት ተብሎ የተወጀበትን 1700ኛ ዓመት ለማክበር ወደ አርሜኒያ ሐዋርያዊ ጎብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በዚህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የአርሜኒያን መሬት የረገጡ የመጀመሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ነበሩ። የቅዱስ ጎርጎርዮስ ንዋያተ ቅድሳት ለአርሜኒያውያን የታላቁ የኪልቅያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አራም ቀዳማዊ እና በወቅቱ የአርሜኒያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ለነበሩት ለብፁዕ አቡነ ኔርሴስ ቤድሮስ ታርሞኒ 19ኛ ተበርክቶላቸዋል።

የስጦታ ልውውጥ ሥነ-ሥርዓት
የስጦታ ልውውጥ ሥነ-ሥርዓት   (ANSA)

ወደ ር. ሊ. ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛ እና ወደ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ያደረጓቸው ጉብኝቶች

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ በቀረበላቸው ግብዣ መሠረት ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከግንቦት 6-9/2008 ዓ. ም. ድረስ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ መሪነት በተካሄደው የክርስቲያኖች አንድነት በዓል ላይ ለመገኘት ወደ ቫቲካን መመለሳቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የአርሜኒያ ሰማዕታት መታሰቢያን በማስመልከት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሚያዝያ 12/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በቀረበው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የአርሜኒያ ቤተ ክርስቲያን መሪ ከጎናቸው እንዲሆኑ በፈለጉት መሠረት፥ ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ዳግማዊ እንደገና ወደ ቫቲካን መምጣታቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ የናሬኩ ቅዱስ  ጎርጎሪዎስ የመላዋ ቤተ ክርስቲያን ዶክተር ብለው ያወጁ ሲሆን፥ ይህም ለአርሜኒያ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ትርጉም ያለው እንደሆነ ተገልጿል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን ፈለግ በመከተል፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከሰኔ 24-26/2016 ዓ. ም. በአርሜኒያን ሐዋርያዊ ጎብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

“የመጀመሪያው የክርስቲያን አገር” የሚለውን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን መሪ ቃል በማስታወስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2018 ዓ. ም. በቫቲካን የአትክልት ሥፍራ የናሬክን ቅዱስ ጎርጎርዮስ ሐውልት ባስመረቁበት ዕለት ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ዳግማዊ እና  ከአርሜኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት አቶ ሰርዝ ሳርጊያን ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።

በዚያው ዓመት ጥቅምት ወር ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ዳግማዊ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በድጋሚ በመጎበኙበት ወቅት ከበርካታ የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች አባላት ጋር ተገናኝተዋል። በመስከረም 2020 ዓ. ም. ሌላ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን፥ በዚያን ጊዜ ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካሬኪን ዳግማዊ በአርሴክ ግዛት ላይ የተፈጸመውን ወታደራዊ ጥቃት ተከትሎ የተፈጠረውን ሁኔታ የሚያስረዳ መረጃን ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባደረሱ ጊዜ ግጭቱን ለማስቆም እና ሰላምን በማደስ ረገድ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥሪዎች አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥቷል።

17 Sep 2025, 16:17