ፈልግ

በሲሲሊ ደሴት ላምፔዱሳ ላይ ዕርዳታን የሚጠባበቁ ስደተኞች በሲሲሊ ደሴት ላምፔዱሳ ላይ ዕርዳታን የሚጠባበቁ ስደተኞች 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ያለ ርኅራኄ ፍትህ የለም” ሲሉ ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በደቡብ ጣሊያን ሲሲሊ ደሴት በምትገኝ ላምፔዱሳ በተካሄደው ዝግጅት ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ የደሴቷን የእንግዳ ተቀባይነት ታሪኳን በማስታወስ፥ ማኅበረሰቡ ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ ላሳየው የረጅም ጊዜ ምሥክርነት ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ይህ ተግባር የዕርቅ ባህል፣ የሰላም እና የወንድማማችነት ጎዳና እንዲሆን ተማጽነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በላምፔዱሳ በተካሄደው የ “እንግዳ ተቀባይነት” ዝግጅት ላይ ለተሳተፉት ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ ሁሉም ሰው የማስታረቅ ባህልን ሳይሆን አቅመ ደካማ ዓለም አቀፋዊነትን እንዲቃወም አሳስበዋል።

“የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ”

“የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ” በሚል ርዕሥ የቀረበው ዝግጅቱ፥ በደሴቲቱ የስደተኞች መዳረሻነት ልምድ ላይ ለማሰላሰል የአካባቢው ነዋሪዎችን፣ በጎ ፈቃደኞችን፣ የቤተ ክርስቲያን ተወካዮችን እና የአካባቢውን ባለስልጣናትን በማሰባሰብ የደሴቲቱ የእንግዳ ተቀባይነት ታሪኮችዋን በማጉላት በባሕር ላይ ሕይወታቸውን ያጡትን የሚያስታውስ እና በአውሮፓ የባሕር ዳርቻዎች ጥገኝነት ከሚጠይቁት ጋር አብሮ ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ መሆኑ ተመልክቷል።

ቅዱስነታቸው በአካባቢው ቋንቋ “ኦሻ!” ወይም “እስትንፋስ” ወይም “መንፈስ” በማለት ለጉባኤው ተሳታፊዎች የላኩትን ሰላምታ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ከሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም ጋር አያይዘው፥ “እንደ አማኞች የእግዚአብሔር እስትንፋስን የሆነው መንፈስ ቅዱስን እርስ በርሳችን እንካፈላለን” ብለዋል።

ወደ ደሴቲቱ ዳርቻ የሚደርሱ ስደተኞችን ለመርዳት የላምፔዱሳ እና በአቅራቢያው የሚኖር የሊኖሳ ሕዝብ ላደረገው አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ለአሥስርት ዓመታት ስደተኞችን ተቀብለው በማስተናገድ ለሰጡት ምስክርነት፥ ልዩ ልዩ ማኅበራትን፣ በጎ ፈቃደኞችን፣ የሲቪል ባለስልጣናትን፣ ቀሳውስትን፣ የሕክምና ባለሞያዎችን እና የጸጥታ ሃይሎችን  አመስግነዋል።

ያለ ርህራሄ ፍትህ የለም

“ያለ ርህራሄ ፍትህ የለም፤ ​​የሌሎችን ስቃይ ካላዳመጥን ሕጋዊነት የለም” ሲል የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በተጨማሪም፥ በባህር ላይ ሕይወታቸውን ያጡ እና በላምፔዱሳ ደሴት የተቀበሩትን በርካታ ስደተኞች በማስታወስ፥ ስደተኞቹን “አዲስ ዓለም የሚበቅልበት ዘር” በማለት ጠርተዋቸዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን በሕይወት የተረፉትን እና አሁን የተሻለ ሕይወት በመኖር ላይ የሚገኙትን በሺህዎች የሚቆጠሩትን በመጥቀስ ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ ራሳቸውን የፍትሕ እና የሰላም ሠራተኞች አድርገው እንደሚቆጥሩ በመግለጽ፥ “መልካምነት ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ዓለም አቀፍ ግድየለሽነትን መቃወም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሐምሌ ወር 2013 ዓ. ም. በላምፔዱሳ ካደረጉት የመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ጋር ቀጣይነት ባለው መልኩ በስደተኞች ላይ በሚደርሱ አደጋዎች ላይ የሚታየውን ዓለም አቀፍ ግድየለሽነትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አውግዘዋል።

ዛሬ በአካባቢው የሚታየው የአደጋ ዓይነት የተለየ ነው” ሲሉ ያስጠነቀቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥“ንጹሐን ግፍ እንደሚፈጸምባቸው እና ስቃይ እንደሚደርስባቸው እናውቃለን፤ ነገር ግን ምንም ማድረግ እንደማይቻል በማሰብ ዝም ብለን እናዝናለን” ብለዋል።

ታሪክ ስለ ኃያላን ሰዎች ብቻ የሚጻፍ ሳይሆን “በትሑታን፣ በጻድቃን፣ በሰማዕታት፣ ደግነት በሚበራባቸው፣ እውነተኛ ሰብዓዊነት በሚታደስባቸው ሰዎች ዘንድ አለ” ሲሉ አበክረው ተናግረዋል።

እርቅን ለማበረታታት የቀረበ ጥሪ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለእነዚህ ችግሮች እጅ ከመስጠት ይልቅ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ እርቅን ለመፍጠር ጥረት እንዲያደርጉ ተማጽነው፥ “በወንድሞች እና በእህቶች መካከል ጠላትነት ስለሌለ የእርቅ ምልክቶች እና ፖሊሲዎች ያስፈልጉናል” ብለው፥ ማኅበረሰቡ ቁስሎችን እንዲፈውስ፣ ጭፍን ጥላቻ እንዲያሸንፍ እና የጋራ ተስፋዎችን እንዲገነዘብ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በደቡብ ጣሊያን ደሴት ላምፔዱሳ የተካሄደውን ዝግጅት ለተሳተፉት ያስተላለፉትን የቪዲዮ መልዕክት ሲያጠቃልሉ፥ እርስ በርስ በመገናኘት እና በማስታረቅ ጎዳና ላይ በመጽናት፣ የመገናኛ ድልድዮችን በመገንባት ለሰው ልጆች እና ለፍጥረታት በሙሉ ሰላም እንዲደርስ የሚያደርጉ የሰላም ደሴቶች እንዲበዙ አበረታተዋል።

የባሕር ኮከብ የሆነች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በመለመን ከሠላምታ ጋር ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ልከዋል።

13 Sep 2025, 15:37