ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ በሮም ከሚኖር የኢንዶኔዥያ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ጋር ሲገናኙ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ በሮም ከሚኖር የኢንዶኔዥያ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ጋር ሲገናኙ  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ በሮም የሚኖሩ ኢንዶኔዥያውያን የውይይት ባሕልን እንዲያሳድጉ አበረታቱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በሮም ከሚኖር የኢንዶኔዥያ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ጋር ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በሮም ለሚኖሩ የኢንዶኔዥያ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ባስተላለፉት በመልዕክት፥ በመካከላቸው የውይይት፣ የመግባባት እና የወዳጅነት ትስስር እንዲገነቡ ጋብዘዋቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የቅድስት መንበር እና የኢንዶኔዥያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 75ኛ ዓመት እና ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዶኔዥያ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሮም ከሚኖሩ የኢንዶኔዢያ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ጋር ሰኞ መስከረም 12/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ተገናኝተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለእንግዶቹ ባደረጉት ንግግር፥ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገር ኢንዶኔዥያ ነፃነቷን ካገኘችበት ጊዜ ጀምሮ ከቅድስት መንበር ጋር መጓዟን አስታውሰው፥ በአገራቱ መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ግንኙነት በመከባበር፣ በውይይት፣ ለሰላም እና መግባባት በጋራ ባደረጉት ጥረት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጸዋል።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዶኔዥያ የደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አስታውሰው፥ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በሁለቱ አገራት መካከል ወዳጅነትን ያጠናከረ ልዩ ጉብኝት መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ  አስታውሰዋል።

ሟቹ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለይ የኢስቲቅላልን መስጊድ በጎበኙበት ወቅት ከታላቁ ኢማም ጋር በሰው ልጆች መካከል ያለውን አንድነትን ለማጎልበት ባላቸው ዓላማ በጋራ የተፈራረሙት ስምምነት በሃይማኖቶች መካከል ባለው የጋራ ውይይቶች መካከል ጎልቶ የታየ እንደ ነበር ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በሮም ከሚኖሩ የኢንዶኔዥያ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ጋር መገናኘታቸውም የእምነት እና የአንድነት መልካም ፍሬዎች ምልክት እንደሆነ ገልጸው፥ “በሮም የሚገኘው የኢንዶኔዥያ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ከአገሩ ርቆ የሚኖር ቢሆንም፥ እርስ በርስ የመደጋገፍ ንቁ ባሕሉን ጠብቆ የቆየ ነው” ሲሉ በአድናቆት ተናግረዋል።

ኢንዶኔዥያ በዓለም ላይ አብዛኛው የሙስሊም ማኅበረሰብ የሚገኝባት  አገር ተብላ የምትታወቅ ሲሆን፥ የካቶሊክ ምዕመናን ቁጥር ከጠቅላላው ሕዝብ 3 በመቶ እንደ ሆነ ይነገራል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የኢንዶኔዥያ ክርስቲያኖች እና ክርስቲያን ያልሆኑ ማኅበረሰቦች እርስ በርሳቸው የሚጋሩትን ጠንካራ ግንኙነት ገልጸው፥ ይህም የአገሪቱን “‘በብዝሃነት ውስጥ ያለ አንድነት’ የሚለውን መሪ ቃል ያካተተ ነው” ብለዋል።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኢንዶኔዥያን በጎበኟት ጊዜ በዋና ከተማዋ ጃካርታ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “የኢንዶኔዢያ ሕዝቦች ለጋራ ጥቅም በኅብረት ሲተሳሰሩ አንድ የሚያደርጋቸውን መንገድ ይመሠርታሉ” ብለው፥ “በእርግጥም በልዩነት መካከል ስምምነትን መጠበቅ ለሁሉም ሰው የተሰጠ የጥበብ ሥራ ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለእንግዶቹ ባደረጉት ንግግር፥ በውጭ አገር የሚኖር የኢንዶኔዥያ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ባሕሉን ከአካባቢው ማኅበረሰቦች ጋር በመጋራት፣ አዲስ ስደተኞችን በመቀበል መተባበርን ለመለማመድ ላሳየው ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸው፥ እርስ በርስ የመገናኘት ባሕል ምሳሌ እንደሚሆን ተናግረዋል።

“ብዙውን ጊዜ መለያየትን እና ቁጣን በሚቀሰቅስ ዓለም ውስጥ የኅብረት ነቢያት እንዲሆኑ አደራ” ብለው፥ “የውይይት እና የጓደኝነት መንገድ ፈታኝ ሊሆን ቢችልም ውድ የሆነውን የሰላም ፍሬን ያስገኛል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ በሮም የሚኖሩት ኢንዶኔዢያውያን ካቶሊክ ምዕመናን ኩሩ፣ ለወንጌል ያደሩና በኅብረተሰቡ መካከል ስምምነትን የሚፈጥሩ እንዲሆኑ ጋብዘዋል።

የምዕመናኑን አደራ የቤተ ክርስቲያን እናት ለሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰጥተው፥ “በሕዝቦች፣ በባሕሎች እና በእምነቶች መካከል የመገናኛ ድልድይ ገንቢዎች ሆነው እንዲቀጥሉ” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

 

23 Sep 2025, 17:14