ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “ሃይማኖቶች የፈውስ እንጂ የመለያየት ምንጭ አይደሉም” ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከዓለም ሃይማኖቶች እና ባሕላዊ እምነቶች የተወጣጡ መሪዎች ከመስከረም 7-8/2018 ዓ. ም. ድረስ በካዛኪስታን አስታና ከተማ በሚካሄደው 8ኛው ጉባኤ ላይ ተገኝተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ረቡዕ መስከረም 7/2018 ዓ. ም. ካስተላለፉት መልዕክት ጋር በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ሰላምታቸውን ልከዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመልዕክታቸው፥ “የሃይማኖት መሪዎቹ አመጽ እና ግጭት በሚታይበት በዚህ ወቅት ወዳጅነትን ለማደስ እና አዲስ ግንኙነቶችን ለመፍጠር፣ ለተሰበረው እና ለቆሰለው ዓለማችን ፈውስን ለማምጣት በጋራ ፍላጎታችን ላይ አንድነት ለመፍጠር ተሰብስበዋል” ሲሉ አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት ወደፊት ለሚመጣው አንድነት” በሚለው መሪ ሃሳብ ላይ በማሰላሰል፥ እያንዳንዱ ትክክለኛ ሃይማኖታዊ ስሜት ድንበርን ተሻግረው የሚገኙ ሰዎችን ባሉበት ቦታ አንድ ስለሚያደርጋቸው የጋራ ውይይትን እና ትብብርን ለመፍጠር እንደሚጥር ጠቁመዋል።
“በጋራ ተስማምቶ መሥራት ተግባራዊ ምርጫ ብቻ ሳይሆን የእውነት ጥልቅ ሥርዓት ነጸብራቅ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ “አብሮነት በተግባር ውስጥ የሚገኝ መተባበር እና ባልንጀራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ራስ የመውደድ ህያው ምስክርነት ነው” ብለዋል። “ልዩነቶችን ከማስወገድ በተጨማሪ በሃይማኖቶች መካከል ያለው ኅብረት ምእመናን ብዝሃነትን እንደ ሃብታቸው ምንጭ እንዲቀበሉት ይጋብዛል” ብለዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1965 ዓ. ም. የተካሄደው ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ “Nostra Aetate” ወይም “የእኛ ዘመን” ሐዋርያዊ ሠነድ መሠረት፥ “ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉትን እውነተኛ እና ቅዱስ ለሆኑት ነገሮች የምትሰጠውን እውቅና እና ክብር የሚደግፍ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስታውሰዋል።
“ቤተ ክርስቲያን እያንዳንዱ እምነት ለጋራ ጥቅም አገልግሎት ልዩ ጥበብ እና ርኅራኄን በሚያበረክትበት ወቅት የእያንዳንዱ ትውፊት ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ወደ ውይይት በማምጣት ትክክለኛ ውህደትን ለማዳበር ትፈልጋለች” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከሳቸው በፊት የነበሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ባለፈው መስከረም 2022 ዓ. ም. በአስታና በተካሄደው ጉባኤ ላይ የሃይማኖት መሪዎች ሁከትን በማውገዝ ስደተኞችን መንከባከብ እና ለሰላም መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ያረጋገጡበት ወቅት እንደ ነበር አስታውሰዋል።
የሁሉም ሃይማኖቶች መሪዎች እምነት “ከመለያየት ይልቅ አንድ የሚያደርገው” የሚለውን እውነት በመመስከር፥ የሰላም፣ የወንድማማችነት እና የአብሮነት ተስፋን ለመገንባት ቃል እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል። “አቅምን ማስተባበር ለሰው ልጆች ሁሉ ከፍተኛ የተስፋ ምልክት ይሆናል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ይህም በዋናነት ሃይማኖት የግጭት ምንጭ ሳይሆን የፈውስ እና የእርቅ ምንጭ መሆኑን ያሳያል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ የሃይማኖቶች ጉባኤ፥ ምእመናን ሰላምን ለመፍጠር ተስማምተው እንዲሠሩ የሚያበረታታ፣ የጦር መሣሪያ ትጥቅን የሚያስፈታ ትሑት እና ጽኑ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
