ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳሳሳት ሊዮ፥ ባለፈው ዓመት የተሰየሙ ብጹዓን ጳጳሳትን በቫቲካን ተቀበሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳሳሳት ሊዮ፥ ባለፈው ዓመት የተሰየሙ ብጹዓን ጳጳሳትን በቫቲካን ተቀበሉ  (@VATICAN MEDIA)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ ጳጳሳት የኢየሱስን አገልግሎት በትህትና እና በጸሎት ማካተት እንዳለባቸው አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛው ባለፈው ዓመት የተሾሙት አዲስ ጳጳሳት የሕዝቦቻቸው የእምነት አገልጋዮች እንዲሆኑ በመጋበዝ፥ ሐአዋርያዊ ጉዟቸውን ከሌሎች ጋር እንዲጋሩ፣ ተንከባካቢ እና ንቁ እረኞች እንዲሆኑ ቤተ ክርስቲያን የምትልካቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ባለፈው ዓመት የተሾሙት አዲስ ብጹዓን ጳጳሳት ከነሐሴ 28/2017 ዓ. ም. እስከ መስከረም 1/2018 ዓ. ም. ድረስ በሮም የተሰጠውን ስልጠና ሲከታተሉ ቆይተው ሐሙስ መስከረም 1/2018 ዓ. ም. ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር ከተገናኙ በኋላ አጠናቅቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለአዲሶቹ ጳጳሳት ባደረጉት ንግግር፥ ጳጳሳቱ የእምነት አገልጋዮች ሆነው የተመረጡ፣ ለአገልግሎት የተጠሩ እና የተላኩ መሆናቸውን እንዲያስታውሱ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለበጹዓን ጳጳሳት ባደረጉት ንግግር፥ “የተቀበላችሁት ስጦታ ለራሳችሁ ሳይሆን ለወንጌል አገልግሎት መሆኑን ላሳስባችሁ እወዳለሁ” ብለው፥ በአደራ በተሰጣቸው የአገልግሎት ተልዕኮ ላይ በማትኮር “አገልግሎታቸው ማንነታቸውን የሚነካ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

አገልግሎት ውጫዊ ባህሪ ወይም የተግባር ስብስብ ሳይሆን “ውስጣዊ ነፃነት፣ የመንፈስ ድህነት እና ከፍቅር የተወለደው የአገልግሎት ዝግጁነት፥ ይህም የኢየሱስ ክርስቶስን ምርጫ ለማካተት፣ እኛን ባለ ጠጎች ሊያደርገን ድሃ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ጥሪ ነው” ብለዋል።

“እግዚአብሔር ወደ እኛ ዘንድ የመጣው በስልጣን ሳይሆን በአብ ፍቅር ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው አክለውም፥ “እግዚአብሔር ከራሱ ጋር ኅብረት እንድንፈጥር ይጠራናል” ብለዋል።

ቅዱስ አጎስጢኖስ፥ “ጳጳሳት ሌሎችን የሚመሩ የብዙ ሰዎች አገልጋዮች መሆናቸውን ማወቅ አለባቸው” ማለቱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርን መፈለግ የጀመሩ ደቀ መዛሙርትን ማሳሰቡን ተናግረዋል።

“እንግዲህ ነቅታችሁ እንድትጠብቁ፣ በትህትና እና በጸሎት እንድትመላለሱ፣ ጌታ ወደ እነርሱ ለሚልካችሁ ሰዎች ራሳችሁን አገልጋዮች እንድታደርጉ ዘወትር እጠይቃችኋለሁ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ጳጳሳት መንጋቸውን እንዲቀርቡ” በማለት የጋበዙትን የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አስታውሰው፥ “ምክንያቱም የእነርሱ ወደ ሕዝባቸው መቅረብ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን አሳቢነት ይገልጻል” ብለዋል።

ጳጳሳት የሁሉም አገልጋዮች እንደመሆናቸው፥ አገልግሎታቸው ኢየሱስ ክርስቶስን እና የእርሱን አገልግሎት መልክ የሚይዝ መሆን እንዳለበት ሊገነዘቡ ይገባል ብለው፥ ሐዋርያዊነታቸው የአስተዳደር ዘዴን ጨምሮ የኢየሱስ ክርስቶስን አገልግሎት የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት ብለዋል።

“የእምነት እና እምነትን የማሰራጨት እንቅፋት፣ ከቤተ ክርስቲያን አባልነት እና ተግባር ጋር የተያያዙ ችግሮች በሙሉ ለአዲስ የወንጌል ምስክርነት ያለንን ፍቅር እና ድፍረት እንደገና እንድናገኝ ይጋብዙናል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከዚህም ጋር አያይዘው፥ “ጳጳሳት የቤተ ክርስቲያንን በሮች የሚያንኳኩትን እንዲቀበሉ በማሳሰብ፥ ጦርነት፣ ዓመፅ፣ የድሆች ስቃይ፣ የሥነ-ምግባር ፈተናዎችን ጨምሮ ሌሎች ባህላዊ እና ማኅበራዊ ተግዳሮቶች መቼም ሊዘነጉ እንደማይችሉ ተናግረው፥ በወንድማማችነት እና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ዓለም እንዲፈጠር መሻት አለባቸው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፣ “ጳጳሳት የሕዝቦቻቸው የእምነት አገልጋዮች እንዲሆኑ በመጋበዝ፥ ጉዟቸውን፣ ጥያቄዎቻቸውን እና ጭንቀቶቻቸውን ከሌሎች ጋር እንዲጋሩ፣ የሕዝቡን ተስፋ እንዴት መጋራት እንዳለባቸው የሚያውቁ፣ መሪ መሆን የሚፈልጉ እረኞች፣ ለካህናቶች፣ በእምነት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ለሆኑት አባቶች እና ወንድሞች እንዲሆኑ በማለት ቤተ ክርስቲያን ትልካቸዋለች” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ አዲሶቹ ጳጳሳት የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ እንዳይጎድላቸው እና የሹመታቸው ደስታ እንደ ጣፋጭ መዓዛ በሚያገለግሏቸው ሰዎች ላይ እንዲሰራጭ በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ባለፈው ዓመት ውስጥ በካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ለተሰየሙት ብጹዓን ጳጳሳት ከነሐሴ 28/2017 ዓ. ም. እስከ መስከረም 1/2018 ዓ. ም. ድረስ በሮም ሲሰጥ የቆየውን ስልጠና፥ ከኢትዮጵያ የመጡት ብጹዕ አቡነ ተስፋ ስላሴ ታደሰ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ይልማ የአዋሳ ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ ጌታሁን ፋንታ የነቀምት ሀገረ ስብከት ጳጳስ እና ብጹዕ አቡነ ደጀኔ ሂዶቶ የሶዶ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ተከታትለውታል።

 

11 Sep 2025, 22:52