ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ “ለፍልስጤም እውቅና መስጠቱ ጠቃሚ ቢሆንም ውይይቱ ተቋርጧል” ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ አንድ ቀን ካሳለፉ በኋላ ማክሰኞ መስከረም 13/2018 ዓ. ም. ምሽት ወደ ቫቲካን የተመለሱ ሲሆን፥ ከመመለሳቸው አስቀድሞ ስለ መካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የፍልስጤም እና የእስራኤል ግጭት በማስመልከት እንደተናገሩት፥ “ቅድስት መንበር የሁለት ሀገር መፍትሄን ለብዙ ዓመታት ደግፋለች” ብለው፥ እንዲሁም በዚያኑ ቀን በጋዛ ከሚገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቁምስና አባላት ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
ለፍልስጤም እንደ ሀገር እውቅናን ስለመስጠት በተመለከተ የተጠየቁት ቅዱስነታቸው ሲመልሱ፥ “ቅድስት መንበር የሁለት አገር መፍትሔን ከጊዜያት በፊት ማሳወቋን ገልጸው፥ ይህ ግልጽ ነው፤ ሁሉንም ሕዝቦች የሚያከብር መንገድ መፈለግ አለብን” ብለዋል።
እውቅናን በተመለከተ፥ “ይህ ሊረዳ የሚችል ቢሆንም አሁን ግን በሌላ ወገን ለመስማት ምንም ፍላጎት አልታየም፥ ውይይቱ ፈርሷል” ሲሉ ተናግረዋል።
የጋዛን ሁኔታ በተመለከተ ሲናገሩ፥ ምንም እንኳን ወረራዎቹ እየተቃረቡ ቢሄዱም፥ ቁምስናው ደህና በመሆኑ እግዚአብሔርን በማመስገን ከቁምስናው አባላት ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
ስለ ሩሲያ ወረራን በማስመልከት ከጋዜጠኞቹ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ “ሁኔታ የበለጠ አደገኛ እየሆነ መጥቷል፣ የጦር መሣሪያን አስቀምጦ፥ ወታደራዊ ግስጋሴዎችን አቁሞ ወደ ድርድር ጠረጴዛው መመለስ እንደሚያስፈልግ አጥብቄ መናገሬን ቀጥያለሁ” ብለዋል።
በዚያ አውድ ውስጥ፥ “አውሮፓ በእውነት አንድ ብትሆን ኖሮ ብዙ ልትሠራ እንደምትችል አምናለሁ” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።
የጦር መሣሪያን እንደገና ማስታጠቅ አስፈላጊ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ “እነዚህ ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንደሆኑ፥ በአውሮፓ ላይ የውጭ ተጽዕኖ የተደረገባቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ገልጸው፥ “በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት አለመስጠትን እመርጣለሁ” ሲሉ መልሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከዚህም በላይ በሚቀጥሉት ወራት ቅድስት መንበር ልታከናውናቸው የምትችላቸው ዲፕሎማሲያዊ ውጥኖች ካሉ ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ “ከአምባሳደሮች ጋር የማያቋርጥ ውይይት በማድረግ ላይ እንገኛለን” ብለው፥ “እንዲሁም የአገር መሪዎች ሲመጡ ሁልጊዜም መፍትሔ እየፈለግን ለመነጋገር እንጥራለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
