ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ ለሮም ሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ አገልጋዮች ንግግር ሲያደርጉ ንግግር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ ለሮም ሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ አገልጋዮች ንግግር ሲያደርጉ ንግግር   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ የሮም ሀገረ ስብከት ሁሉን ሰው የሚያስተናግድ አገልግሎት እንዲያስተዋውቅ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፣ በሮም በሚገኝ የቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ ተገኝተው ለሮም ሀገረ ስብከት ቤተ ክኅነት እና ምእመናንን ንግግር አድርገዋል። ቅዱነታቸው በባዚሊካው ለተገኙት ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሮም ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር በኅብረት እንድትጓዝ አደራ ብለው፥ የተቸገሩትን የሚረዳ፣ የሚራራ፣ አስተዋይ፣ ፍርድ የማይሰጥ እና ሁሉንም ሰው ተቀብሎ የሚያስተናግድ የእረኝነት አገልግሎት እንድታበረክት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ዓርብ ከሰዓት በኋላ በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ ለተሰበሰበው የሮም ሀገረ ስብከት ጉባኤ ንግግር ያደረጉት ሲሆን፥ በንግግራቸውም፣ በነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለተጀመረው ሲኖዶሳዊ ሂደት አጽንኦት ሰጥተው፥ ቤተ ክኅነት፥ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ምዕመናን በሲኖዶሳዊነት፣ በኅብረት፣ በአብሮነት እና በተልዕኮ ተባብረው እንዲጓዙ ጋብዘዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የሮም ሀገረ ስብከት ጳጳስ እንደመሆናቸው፥ ከሀገረ ስብከቱ ማኅበረሰብ ጋር በመገናኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም የሰበካው ተወካዮችን ላበረከቱት ሐዋርያዊ አገልግሎት እና ምስክርነት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው ለሀገር ስብከቱ ሐዋርያዊ አገልጋዮች ባደረጉት ንግግር፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሮም ሀገረ ስብከት ጳጳስ እስከሆኑ፥ ለእናንተም ጳጳስ ነኝ” ብለው፥ በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ ውስጥ መገናኘታቸው፥ “ጳጳሱ ከምዕመናኑ ጋር ያለውን ጥልቅ ግንኝነት የሚያመለክት ነው” በማለት ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፣ ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ ሲደርሱ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፣ ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ ሲደርሱ   (@Vatican Media)

ስለ እግዚአብሔር ስጦታ አስመልክቶ በዮሐ. 4:10 ላይ እንደተጻፈው፥ በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በተገናኘችው ሳምራዊት ሴት ታሪክ ላይ በማሰላሰል ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን፥ መንፈስ ቅዱስ እንደ የ “ሕይወት ውሃ” የሰውን ልጅ ጥማት የሚያረካ እና ቤተ ክርስቲያንን በተልዕኮዋ የሚደግፋት መሆኑን አስረድተዋል።

ደጋፊ እና እንግዳ ተቀባይ ቤተ ክርስቲያን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስቸኳይ የእረኝነት አገልግሎት አቀራረቦችን በተለይም ለቤተሰቦች እና ለወጣቶች የሚሰጥ ሐዋርያዊ አገልግሎት ማደስ እንደሚያስፈልግ ካሳሰቡ በኋላ፥ “እንደ ሁልጊዜው ተመሳሳይ ነገሮችን በመድገም መርካት ሳይሆን፥ ድጋፍ የሚሆን፣ ርኅሩኅ፣ አስተዋይ፣ የማይፈርድ እና ሁሉንም ሰው ተቀብሎ የሚያስተናግድ አስቸኳይ ሐዋርያዊ አገልግሎት ማመቻቸት ያስፈልጋል” ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከብፁዕ ካርዲናል ባልዳሳሬ ሬይና፣ የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ጋር ሲገናኙ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከብፁዕ ካርዲናል ባልዳሳሬ ሬይና፣ የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ጋር ሲገናኙ   (@Vatican Media)

ከቤተሰቦች እና ወጣቶች ጋር በኅብረት መጓዝ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ንግግራቸውን በመቀጠል፥ ብዙውን ጊዜ ቤተሰቦች በሚያጋጥማቸው የኑሮ ጫና ምክንያት እምነትን ለሌሎች ከማስተላለፍ ሚናቸው የመውጣት ፈተና ውስጥ ሊወድቁ እንደሚችሉ ገልጸው፥ “የቤተ ክርስቲያን ተግባር እነሱን መተካት ሳይሆን ከእነሱ ጋር አብሮ መጓዝ፣ የጉዞአቸው አጋር በመሆን እግዚአብሔርን ለመፈለግ የሚረዱ ዘዴዎችን እና መንገዶችን ማሳየት ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ወጣቶችን ባስታወሷቸው ንግግራቸው፥ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶችን በተሳትፎ እና በጥበብ ፍለጋ ላይ ማበረታታት እንደሚገባት በማሳሰብ፥ “ፍርድን ሳይሰጥ በጥሞና ማዳመጥ የሚችል የአገልግሎት መንገድ፥ ወጣቶች የሚፈልጉትን መመሪያ እና በምዕመናን ውስጥ ቦታን ሊሰጣቸው ይችላል” ብለዋል።

ሕንጸት እና ተልዕኮ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በአስቸኳይ ሊሰጥ የሚገባ ሐዋርያዊ ሕንጸት በማስመልከት ሲናገሩ፥ ቁምስናዎች እና ማኅበረሰቦች እምነትን የሚያዳብሩ እና ከቤተ ክርስቲያን ወደራቁት ዘንድ የሚሄዱ እንዲሆኑ በማሳሰብ፥ ማኅበረሰቡን እና ወጣቱን ትውልድ የሚነኩ ማኅበራዊ ፍትህን፣ ሰላምን፣ ስደትን፣ የፍጥረት እንክብካቤን፣ የአእምሮ ጤናን እና የሱስ ተግዳሮቶችን ከቁምስና ሕይወት ጋር የማካተት አስፈላጊነት አስምረውበታል።

“የሁሉ ነገር አዋቂዎች መሆን አንችልም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን በእነዚህ እውነታዎች ላይ በማሰላሰል ከተማችን የምትሰጠንን በርካታ እውቀቶች መጠቀም አለብን” ብለዋል።

በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ ውስጥ የተገኙት የስብሰባው ተሳታፊዎች
በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ ውስጥ የተገኙት የስብሰባው ተሳታፊዎች   (@Vatican Media)

በሲኖዶሳዊነት እና በኅብረት ማደግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ በሮም የምትገኘኝ ቤተ ክርስቲያን በሲኖዶሳዊነት እና በተልዕኮ መንፈስ በአንድነት እንድትጓዝ ጥሪ አቅርበው፥ ስለ ሳምራዊቷ ሴት የሚናገረውን የወንጌል ክፍል በመጥቀስ “እኛም ማሰሮቻችንን ትተን በምትኩ ጥማታቸውን ለዘላለም የሚያረካ የሕይወት ውኃን ለማድረስ ወደ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንሩጥ” ብለዋል።

በሮም የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን በሲኖዶሳዊነት፣ በኅብረት፣ በጋራ ኃላፊነት እና በተልዕኮ ማደጓን እንደምትቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ “የታማኝነት እና የተስፋ እናት፣ የሮም ከተማ ጠባቂ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጉዞአችንን እንድትጠብቅልን” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፣ በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ ውስጥ በተካሄደ ስብሰባ ላይ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፣ በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ ውስጥ በተካሄደ ስብሰባ ላይ   (@Vatican Media)
20 Sep 2025, 16:05