ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፡- ሰማዕታት የተለያየ አቋም ያላቸውን ክርስቲያኖች አንድ ማድረግ ይችላሉ አሉ።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
በሮም ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ በመስከረም 4/2018 ዓ.ም ምሽት የሰማዕታት እና የእምነት ምስክሮች መታሰቢያ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የልዩ ዝግጅት ሆኖ ቀርቧል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከተለያዩ የክርስቲያን ቤተ እምነቶች እና ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በመሆን ይህንን የመታሰቢያ በዓል መርተዋል።
ዝግጅቱ የእነዚህን ሰማዕታት ህይወት እና ለክርስቲያናዊ እሴቶች ያላቸውን ምስክርነት ለማጉላት በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 5 ላይ በተጠቀሰው "በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ መፅናናትን ያገኛሉና። የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ይጠግባሉና። ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና። ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና። ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። “ሲሰድቡአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና” በተሰኘው
"አንቀጸ ብፁዓን" ቅዱስነታቸው በዋቢነት አንስተዋል። የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እና ማህበረሰቦች አባላት እና ተወካዮች ጸሎቶችን በወቅቱ አቅርበዋል።
ፍቅር ከሞት ይበልጣል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በስብከታቸው መስከረም 04/2018 ዓ.ም ቀን የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የተከበረውን የመስቀል ክብር በዓል እና የመስቀሉ ምስል ከሥቃይ ምልክት ወደ “የመዳናችን መንገድ”፣ “የክርስቲያኖች ተስፋ” እና “የሰማዕታት ክብር” እንዴት እንደተቀየረ ጠቁመዋል።
ለኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት አባላት፣ ለጥንት ምስራቃዊ አብያተ ክርስቲያናት፣ የክርስቲያን ማህበረሰቦች እና የክርስቲያናዊ ሕብረት ድርጅት አባላት "የእንኳን ደህና መጣችሁ" መልእክት ያቀረቡት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በላቲን ቋንቋ " Ut Unum Sint" (አንድ ይሆኑ ዘንድ) ከተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክት በመጥቀስ “ሰማዕትነት እስከ ሞት ድረስ” “ደሙን ካፈሰሰው ከክርስቶስ ጋር የሚቻል እውነተኛ ኅብረት” ነው ብለዋል።
ዛሬም ቢሆን "ጥላቻ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ውስጥ የገባ ይመስላል"ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሆኖም ደፋር ወንዶችና ሴቶች “የወንጌል አገልጋዮችና የእምነት ሰማዕታት” ራሳቸውን ለእምነታቸው በመወሰናቸው ፍቅር ከሞት የበለጠ እንደሚበረታ አሳይተዋል" ብለዋል።
መስቀሉንም ተሸክመዋል
ለእምነታቸው ሲሉ የሞቱትን በማስታወስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ኢየሱስ "የእግዚአብሔርን እውነተኛ ፊት፣ ለሰው ልጅ ያለው ወሰን የሌለው ርኅራኄ የገለጠልን" ወደ መስቀል እንዲመለከቱ ሁሉም ሰው አሳስቧል። ኢየሱስ ከመስቀል ላይ ሲወርድ፣ የዓለምን ጥላቻ በራሱ ላይ እንደወሰደ ገልጿል፣ “ለተዋረዱትና ለተጨቆኑት ሁሉ እጣ ፈንታቸውን ከፍሎላቸዋል ብለዋል።
አሁን ባለንበት ዘመን፣ ብዙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ለእምነት በሚሰጡት ምስክርነት “በአስቸጋሪ ሁኔታዎች እና በጥላቻ አውድ ውስጥ፣ እንደ እርሱ ይሰደዳሉ፣ ይኮነናሉ፣ ይገደላሉ” በማለት ይህን መስቀል መሸከማቸውን ቀጥለዋል ያሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ "አንቀጸ ብፁዓን" የሰጣቸው እነዚህ ወንዶች እና ሴቶች ናቸው፣ ለወንጌል ታማኝነታቸው፣ ለፍትህ ቁርጠኝነት እና እጅግ በጣም ከተቸገሩት ጋር አንድነት ለማግኘት የሚከፍሉት ዋጋ ሕይወታቸው ነው ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ “በዓለም ደረጃዎች እንደተሸነፉ” ጠቁመዋል። የጥበብ መጽሐፍ ግን በተለየ መንገድ “ተስፋቸው የማይሞት ነው” ይላል ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
በኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት መካከል፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁሉም ሰው እነዚህን የእምነት ምስክሮች እንዲያከብሩ አበረታቷቸዋል። በሰማዕትነታቸው የወንጌል መልእክት መስፋፋቱን ቀጥሏል። "በማይሞት ህይወት የተሞላ ተስፋ ነው፣ ምክንያቱም ምንም እንኳን በሰውነት ውስጥ ቢገደሉም፣ ማንም ድምጻቸውን ማጥፋት ወይም ያሳዩትን ፍቅር ሊሰርዝ አይችልም" ምስክርነታቸው በክፋት ላይ ድል እንደሚቀዳጁ ትንቢት በማሳየት ይቀጥላል ብለዋል።
መሳርያ ያልታጠቀ ተስፋ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የእነዚህ ሰማዕታት ምስክርነት ከኃይል እና ከዓመፅ መሳሪያዎች ይልቅ የወንጌልን ኃይል በመምረጣቸው "ያልታጠቀ ተስፋ" እንደሆነ አስምረውበታል።
ከዚያም "በአማዞን ደኖች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች" ሕይወቷን የወሰነችው የእህት ዶሮቲ ስታንግ ምሳሌ ያዞሩት ቅዱስነታቸው አጥቂዎቿ መሣሪያዋን እንድትሰጣቸው ሲጠይቁ መጽሐፍ ቅዱሷን ብቻ "መሣሪዬ ይሄውና" ብላ አሳየቻቸው ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አባ ራጂድ ጋኒ—በኢራቅ ውስጥ በሞሱል ይኖሩ የነበሩ የከለዳውያን ቄስ—ለእውነተኛ ክርስቲያናዊ እሴቶች ለመመስከር በጦር መሣርያ በሚደርገው ፍልሚያ እንዲሳተፉ በተጠየቁ ጊዜ አሻፈረኝ በማለታቸው መገደላቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።
ሌላው ምሳሌ በሰለሞን ደሴቶች ሰላም እንዲሰፍን ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠው የአንግሊካን አባል እና የሜላኔዥያ ወንድማማችነት አባል የሆነው ወንድም ፍራንችስኮስ ቶፊ ነው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ “እስከ ዛሬ ድረስ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ስደት አላበቃም፤ ይልቁንም በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ጨምሯል” ሲሉ አበክረው ተናግረዋል።
መርሳት አንችልም
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መርሳት "እኛ አንችልም እና መርሳት አንፈልግም" ሲሉ አጽኖት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን "ማስታወስ እንፈልጋለን" ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና የክርስቲያን ቤተ እምነቶች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በመሆን፣ ምስክርነታቸውን እና ታሪኮቻቸውን በሕይወት ለማቆየት እንፈልጋለን ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
የእነዚህን ወንዶች እና ሴቶች ትውስታዎች ከሁሉም የክርስቲያን ወጎች ለመጠበቅ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቁርጠኝነትን አረጋግጠዋል - ይህ ተግባር በቫቲካን የቅዱሳን ጉዳዮች በሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት እና በቫቲካን ክርስቲያናዊ አንድነትን ለማስፋፋት በሚሰራው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት ጋር በመሆን መከናወን እንደሚቀጥል ቅዱስነታቸው አረጋግጠዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቅርቡ ለተካሄደው ሲኖዶስ የተላከውን መልእክት ደግመው ተናግረዋል፡- “የደም ጠባያት ‘ልዩ ልዩ እምነት ያላቸው ክርስቲያኖች በአንድነት ሕይወታቸውን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። የሰማዕትነታቸው ምስክርነት ከምንም በላይ አንደበተ ርቱዕ ነው፤ አንድነት የሚመጣው ከጌታ መስቀል ነው” ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ስብከታቸውን ከማብቃታቸው በፊት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ በደረሰ ጥቃት የተገደለውን ፓኪስታናዊውን አቢሽ ማሲህን አስታውሰዋል። ይህ ልጅ በማስታወሻው ደብተር ላይ “ዓለምን የተሻለ ቦታ ማድረግ” ሲል ጽፏል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁሉም ሰው የአቢሽ ህልም ለእምነት በድፍረት እንድንመሰክር እና በዚህም "ለሰላማዊ እና ወንድማማችነት ለሰው ልጅ እርሾ" እንድንሆን እንዲያነሳሳን አሳስበዋል።
