ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊሊጶ ያኖኔ፤ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊሊጶ ያኖኔ፤ 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቫቲካን ለብጹዓን ጳጳሳት ጽሕፈት ቤት አዲስ ዋና ጸሐፊን ሰየሙ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቫቲካን ለሚገኙ ጽሕፈት ቤቶች በሰጡት የመጀመሪያ ሹመት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊሊጶ ያኖኔን የጳጳሳት ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ አድርገው ሾመዋል። አቡነ ፊሊጶ ያኖኔ ከዚህ ቀደም የሕግ ነክ ጽሑፎች ጽሕፈት ቤት ዋና ሃላፊ ሆነው አገልግለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እርሳቸውን ተክተው እንዲያገለግሉ በማለት ለእምነት አስተምህሮ ጽሕፈት ቤት፥ ብጹዕ ካርዲናል ዊልያም ሌቫዳን እንደሰየሟቸው ሁሉ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛም እርሳቸው ተክተው የሚሠሩ የብጹዓን ጳጳሳት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሹመት ወደ ፊት ከሚሰጧቸው ሌሎች ሹመቶች መካከል የመጀመሪያው እንደሚሆን ተጠብቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለከፍተኛ ሐዋርያዊ ስልጣን ከመመረጣቸው በፊት በነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምርጫ ወደ ሮም ከተዛወሩበት ከጥር 2023 ዓ. ም. (እ.አ.አ) ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 2025 ዓ. ም. ድረስ የብጹዓን ጳጳሳት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።

የዋና ጸሐፊ እና ምክትል ጸሐፊ ሚና ተረጋግጧል

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊሊጶ ያኖኔ አዲሱን ሥራቸውን የሚጀምሩት መጭው ጥቅምት 5/2018 ዓ. ም. እንደ ሆነ የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል በዕለታዊ መጽሔቱ ላይ አስታውቋል። መግለጫ ክፍሉ እንደዚሁም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ብራዚላዊውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢልሰን ደ የሱስ ሞንታናሪን ለተጨማሪ አምስት ዓመታት የጽሕፈት ቤቱ ዋና ጸሐፊ አድርገው መሾማቸው እና ሞንሲኞር ኢቫን ኮቫቺን ለተጨማሪ አምስት ዓመታት በምክትል ጸሐፊነት መሾማቸውን አስታውቋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊሊጶ ያኖኔ ለብጹዓን ጳጳሳት ጽሕፈት ቤት መሾማቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት መሪነት የሰጡት የመጀመሪያው ሹመት መሆኑ ተነግሯል። ቅዱስነታቸው በቅድስት መንበር ከፍተኛ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ወይም ሮማን ኩሪያ ውስጥ ለከፍተኛ ሃላፊነት የሰጡት ብቸኛው ሹመት ግንቦት 14/2017 ዓ. ም. የተከናወነው ሲሆን ይህ ከሆነ ከጥቂት ቀናት በኋላ የድሆች እህቶች ፍራንችስካዊ ማኅበር አባል የሆኑትን እህት ቲዚያና ሜርሌቲን የምንኩስና ሕይወት እና ሐዋርያዊ ማኅበራት ተቋማት ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ አድረገው መሰየማቸው ይታወሳል።

የሕግ ባለሙያ እና የሕገ ቀኖና ዳኛ

በጣሊያን ኔፕልስ ግዛት የተወለዱት እና በመጭው ታኅሳስ 4/2018 ዓ. ም. 68 ዓመት የሚሞላቸው ቀርሜሎሳዊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊሊጶ ያኖኔ የሕግ ሊቅ እና የሕገ-ቀኖና ዳኛ ሲሆኑ ለቅድስት መንበር ፍርድ ቤት፣ ለጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች እና ለሀገረ ስብከቶች ባበረከቷቸው አገልግሎቶች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው መሆኑ ተነግሯል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊሊጶ ያኖኔ በቅድስት መንበር የሐዋርያዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አባልነት ጨምሮ ሮም ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ አገልግለዋል። የምንኩስና ሕይወት ተቋማት ጉባኤ አማካሪ፣ የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የሕግ ጉዳዮች ምክር ቤት አባል፣ የአምልኮ ቦታዎች ኮሚቴ ፕሬዝዳንት እና በላዚዮ ክፍለ ሀገር የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አባል በመሆንም አገልግለዋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2012 ዓ. ም. የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ አድርገው መሾማቸው ይታወሳል። በኋላም በ2017 ዓ. ም. ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ለሕግ ነክ ጽሑፎች ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ረዳት ጸሐፊነት ካዛወሯቸው በኋላ በቀጣዩ ዓመት ማለትም በሚያዝያ 7/2018 ዓ. ም. የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አድርገው ሾመዋቸዋል።

የዓለም ጳጳሳትን የመምረጥ ተግባር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲመሩ የነበትን ሥራዎች እንዲቀጥሉ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊሊጶ ያኖኔን መድበዋል። የብጹዓን ጳጳሳት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሚና እጅግ ረቂቅ ሲሆን፥ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች አደራን የሚሰጧቸው አባቶች ምርጫ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን መርዳት ነው። ለጳጳስነት የሚያቀርቡ ካህናትን ከለዩ በኋላ የመጨረሻው ውሳኔን የሚሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው።

ይህን ተልዕኮ እንዲረዱ በማለት ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያን በሐምሌ ወር 2022 ዓ. ም. ለጳጳሳት ጽሕፈት ቤት አባልነት ሦስት ሴቶችን የሾሙ ሲሆን፣ እነዚህም አሁን የቫቲካን ከተማ ጠቅላይ ግዛት ፕሬዝዳንት እህት ራፋኤላ ፔትሪኒ፣ የቀድሞው የእመቤታችን ማርያም የክርስቲያኖች ረዳት ማኅበር የበላይ አለቃ የበሩ ኢቮን ሪያንጎት እና የቀድሞው ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ሴቶች ማኅበር (WUFC) ፕሬዝደንት የነበሩ ማርያ ሊያ ዜርቪኖ መሆናቸው ይታወሳል።

 

27 Sep 2025, 13:45