ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ከፍጥረታት በሙሉ ጋር ስላለን ግንኙነት መጸለይ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሯቸው የወደዱትን የመስከረም ወር የጸሎት ሃሳብ ይፋ አድርገዋል። በዓለም አቀፉ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ በኩል ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ እግዚአብሔር ከሚወዳቸው ፍጥረታት በሙሉ ጋር ያለንን መደጋገፍ ለመለማመድ መጸለይ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመስከረም ወር የቪዲዮ መልዕክታቸው፥ የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ እንዳደረገው፥ ፍቅር እና ክብር ከሚገባቸው የእግዚአብሔር ፍጥረታት ጋር ያለንን መደጋገፍ ለመለማመድ መጸለይ እንደሚገባ አሳስበውናል።

ጸሎቱ እግዚአብሔር ለፍጥረታት ባለው ፍቅር ላይ አጽንዖት የሚሰጥ፥ ከእርሱ ርኅራኄው ውጭ ሌላ ምንም እንደሌለ፥ አጭር ዕድሜ ያላቸውን ጥቃቅን ፍጥረታትን ሳይቀር እንደሚንከባከባቸው መሆኑን የሚያስታውስ፥ የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ምክርን በመድገም እንደ አሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ እኛም ዛሬ “ጌታ ሆይ ተመስገን!” እንድንል የሚጋብዘን ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ስለ ፍጥረታት ውበት በመናገር ባቀረቡት ጸሎታቸው፥ እግዚአብሔር የመልካምነት ምንጭ እንደሆነ ገልጸው፥ ዓለም ሊፈታው ከሚችለው ችግር በላይ እግዚአብሔር ለፍጥረታቱ ያለውን ቅርበት ለመረዳት  ዓይኖቻችንን እንዲከፍትልን በጸሎት በመጠየቅ “በአመስጋኝነት መታሰብ ያለበት ምስጢር ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በጸሎታቸው ማጠቃለያ፥ “በፍጥረታት መካከል መገኘታችንን እንድናውቅ፣ ይህን ሙሉ በሙሉ እንድንገነዘብ፥ ሕይወትን እንድንንከባከብ፣ እንድናከብር እና እንድንጠብቅ ለሚጋብዘን ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ተጠያቂዎች እንድንሆን ዕርዳን” ብለዋል።

የምስጋና ጊዜን መኖር

የእያንዳንዱን ወር የጸሎት ሃሳብ የማዘጋጀት ኃላፊነት ያለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፉ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጸሎት ጋር በሰጠው መግለጫ፥ የቪዲዮው ቅንብሩ ይፋ የሆነው ፍጥረት በሚታወስበት እና የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ዓመታዊ በዓል በሚከበርበት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከመስከረም 1 እስከ ጥቅምት 4 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን፥ ይህ ጊዜ ከልዩ ልዩ ቤተ እምነቶች የተውጣጡ ክርስቲያኖች በመተባበር ለምድር እንክብካቤ ጸሎት የሚያቀርቡበት ወቅት መሆኑን አስታውቋል።

የዘንድሮው “የፍጥረት ሰሞን” የሚከበረው፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ስለ ፍጥረታቱ ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀረበበትን 800ኛ ዓመት ቤተ ክርስቲያን በምታከብርበት እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳን 10ኛ ዓመት በሚታሰብበት ወቅት ነው።

“‘የተስፋ ኢዮቤልዩ’ እና ‘ውዳሴ ላንተ ይሁን!’ ቃለ-ምዕዳን 10ኛ ዓመት ምስጋናን እንድናቀርብ እና የጋራ መኖሪያ ምድራችን በቁርጠኝነት እንድንንከባከብ ይጋብዙናል” ሲሉ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለመስከረም ወር ያቀረቡትን የጸሎት ሃስብ በመደገፍ፥ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ ገልጸዋል።

እርስ በርስ የተገናኘ ዓለም

በመስከረም ወር የጸሎት ሃሳብ ላይ አስተያየታቸውን ሰጡት፥ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር አባ ክሪስቶባል ፎንስ፥ የዚህ ወር የጸሎት ዓላማ፥ “ከዓለማችን ያር ምን ያህል ትስስር እንዳለን ያስታውሰናል” ብለው፥ ደህንነታችንን በምድር ላይ ከሚኖሩ ሌሎች ፍጥረታት ወይም ፕላኔታች የደኅንነት ሁኔታ መለየት አይቻልም” ብለዋል።

አባ ፎንስ በመቀጠልም፥ “በመስከረም ወር ውስጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ተግባራችን ምን ያህል ተፈጥሮን እንደሚነካ፣ የእግዚአብሔርን ሥራ እንድናሰላስል እንዲሁም በሰዎች እና በመኖሪያ አካባቢያቸው መካከል ያለውን የተፈጥሮ ሚዛን እና ስምምነት የሚያጎለብቱ የኑሮ መንገዶችን እንድንፈልግ ጋብዘውናል” ብለዋል።

አባ ፎንስ በመጨረሻም፥ “ፉክክር እና ውዥንብር በበዛበት ዓለም ውስጥ፣ በፍጆታ ቁጥጥር ሥር በሚገኝ ዓለም ውስጥ፣ የሰው ልጅ በተደላደለ ሁኔታ ለመኖር በሚፈልግበት ዘመን ተፈጥሮን በመንከባከብ ይበልጥ እንድንቀርበው፣ ትኩረታችንን ከራሳችን፣ ከእግዚአብሔር እና ከሌሎች ጋር በማድረግ እንድናሰላስል የሚፈቅድ የሕይወት ዘይቤን እንፈልግ” በማለት ጋብዘውናል።

 

 

11 Sep 2025, 19:57