ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ዕለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ዕለት   (@VATICAN MEDIA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ቤተ ክርስቲያን ፀረ-ሴማዊነትን የማትቀበል መሆኑን አስታወቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የእኛ ዘመን” የተሰኘ ሐዋርያዊ ሠነድ 60ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓልን ምክንያት በማድረግ ያዘጋጁትን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ረቡዕ ጥቅምት 19/2018 ዓ. ም. ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ባቀረቡት አስተምህሮ፥ “ቤተ ክርስቲያን ፀረ-ሴማዊነትን አትቀበልም” ሲሉ ተናግረዋል።

ክቡራት ክቡራን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን የዕለቱን አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን፥ አስተንትኖ ያደረጉበትን የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ እናነብላችኋለን፥

“ኢየሱስም እንዲህ አላት ‘አንቺ ሴት እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ለምናውቀው እንሰግዳለን። መዳን ከአይሁድ ነውና። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስ እና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። ይኸውም አሁንም ነው፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል” (ዮሐ. 4: 21-24)።

ክቡራት እና ክቡራን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ተወካዮች! በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይትን በሚመለከተው በዛሬው ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮዬ ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሳምራዊቷ ሴት የተናገራቸውን ቃላት የአስተንትኖዬ ዋና ማዕከል ማድረግ እፈልጋለሁ። ‘እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስ እና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል’ (ዮሐ. 4፡24)። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ይህ ግንኙነት በሃይማኖቶች መካከል የሚደረገውን የእውነተኛ ውይይት ፍሬ ነገር ያመለክታል። ሰዎች በቅንነት፣ በትኩረት በማዳመጥ እና በጋራ በማሳደግ እርስ በርስ ለመወያየት ዝግጁ መሆንን ያመልክታል። ይህ ውይይት ከከፍተኛ ፍላጎት የሚመነጭ ውይይት ነው። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ልብ ያለው ጥማት እና ሰው ለእግዚአብሔር ያለውን ጥማት ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በሲካር ጉድጓድ አጠገብ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር መገናኘቱ የባህል፣ የፆታ እና የሃይማኖት እንቅፋቶችን ያሸንፋል። ሳምራዊቷን ሴት ወደ አዲስ የአምልኮ ግንዛቤ ይጋብዛል። ይህም ግንኝነት በተራራማ ቦታ ወይም በኢየሩሳሌም ብቻ የተወሰነ አይደለም። ነገር ግን በመንፈስ እና በእውነት እውን የሆነ ግንኝነት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር መገናኘቱ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት ዋና አካል ይሆናል። የእግዚአብሔርን መገኘት ማወቅ ከሁሉም በላይ እሱን በአክብሮት እና በትህትና እንድንፈልግ ይጋብዛል።

ከስልሳ ዓመታት በፊት ማለትም ጥቅምት 28/1958 ዓ. ም. ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ‘Nostra Aetate’ ወይም ‘የእኛ ዘመን’ የተሰኘ ሐዋርያዊ ሠነድ ይፋ ባደረገበት ወቅት አዲስ እርስ በርስ የመገናኘት፣ የመከባበር እና የመንፈሳዊ መስተንግዶ አድማስን ከፍቷል። ይህ ብሩህ ሠነድ የሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮችን እንደ ባዕድ ሳይሆን እንደ የጉዞ አጋሮች በእውነት መንገድ ላይ እንድንገናኝ ያስተምረናል። የጋራ ሰብዕናችንን የሚያረጋግጡ ልዩነቶችን በማክበር በእያንዳንዱ ቅን ሃይማኖታዊ ፍለጋ ላይ ሁሉንም ፍጥረት የሚያቅፍ አንድ መለኮታዊ ምስጢር ነጸብራቅ መለየት አለብን።

በተለይ ‘የእኛ ዘመን’ የተሰኘ ሐዋርያዊ ሠነድ የመጀመሪያ ትኩረት ወደ አይሁድ ዓለም እንደ ነበር መዘንጋት የለበትም። ይህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የመጀመሪያውን ግንኙነት እንደገና ለመመሥረት በማሰባቸው ነበር። በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ አይሁድ የክርስትና ሥሮች የሚገልጽ አስተምህሮ መፃፍ ነበረባቸው። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ እና በሥነ-መለኮት ደረጃ ሊዘነጋ የማይገባ ነጥብን የያዘ ነው። ‘የአዲስ ኪዳን ሰዎችን ከአብርሃም ዘር ጋር በመንፈሳዊ መንገድ  የሚያስተሳስር ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር የማዳን እቅድ መሠረት በእምነቷ ጅማሬ እና ምርጫ አስቀድሞ በፓትርያርኮች፣ በሙሴ እና በነቢያት መካከል የምትገኝ መሆኗን ትገነዘባለች’ (የእኛ ዘመን ሐዋርያዊ ሠነድ ቁ. 4)። በዚህ መንገድ ቤተ ክርስቲያን ከአይሁዶች ጋር የምትጋራውን እና በፖለቲካዊ ምክንያቶች ሳይሆን በወንጌል መንፈሳዊ ፍቅር የምትንቀሳቀሰውን የትውልድ ሐረግ ስታስብ በማንኛውም ጊዜ በማንኛውም አይሁዳዊ ሰው ላይ የተሰነዘረውን ጥላቻ፣ ስደት እና ፀረ-ሴማዊነትን ትቃወማለች”። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ ሁሉም የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፀረ-ሴማዊነትን በግልጽ ቃል አውግዘዋል። ስለዚህ እኔም ቤተ ክርስቲያን ፀረ-ሴማዊነትን እንደማትታገስ እና በወንጌል በራሱ የምትዋጋው መሆኑን አረጋግጣለሁ።

ዛሬ በእነዚህ ስልሳ ዓመታት ውስጥ በአይሁድ እና ካቶሊክ እምነቶች መካከል በተካሄደው ውይይት የተገኘውን በሙሉ በአመስጋኝነት መመልከት እንችላለን። ይህ የሆነው በሰው ጥረት ብቻ ሳይሆን በክርስቲያናዊ እምነት መሠረት ራሱ የውይይት ምንጭ በሆነው በእግዚአብሔር ዕርዳታ ነው። በዚህ ዘመን የተሳሳቱ ግንዛቤዎች፣ ችግሮች እና ግጭቶች መኖራቸውን መካድ አንችልም። ነገር ግን እነዚህ ችግሮች ውይይቱ እንዳይቀጥል አግደውት አያውቁም። ዛሬም ቢሆን በተለይም እስካሁን ድረስ ብዙ ስኬቶችን ባገኘንበት ወቅት አንዳንድ የፖለቲካ ሁኔታዎች እና ኢ-ፍትሃዊነት ከወዳጅነት እንዲያግዱን መፍቀድ የለብንም።

‘የእኛ ዘመን’ የተሰኘ ሐዋርያዊ ሠነድ መንፈስ ለቤተ ክርስቲያን ብርሃን መሆኑን ቀጥሏል። ‘ሁሉም ሃይማኖቶች ለሁሉም ሰው የሚያበራ የእውነት ብርሃን እንዳላቸው ቤተ ክርስቲያን ትገነዘባለች’ (ቁ. 2)። ለሰው ልጅ ህልውና ታላላቅ ምስጢሮች መልስ ሊፈልጉ እንደሚችሉ ትገነዘባለች። ስለዚህ ውይይት በፍፁም ምሁራዊ ብቻ ሳይሆን ጥልቅ መንፈሳዊ ጥረት መሆን የለበትም። ሐዋርያዊ ሠነዱ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች በሙሉ፥ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካኅናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ምዕመናን በሙሉ ከሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮች ጋር በቅንነት በመወያየት እና በመተባበር፣ በባሕላቻቸው ውስጥ ያለውን መልካም፣ እውነት እና ቅዱስ የሆነውን ሁሉ እንዲያውቁ እና እንዲያስተዋውቁ ተጋብዘዋል። ይህ ዛሬ ሰዎች እንቅስቃሴ በሚያደርጉባቸው ሁሉም ከተሞች፣ በመንፈሳዊ እና ባህላዊ ልዩነቶች ውስጥ እርስ በርስ እንዲገናኙ እና በወንድማማችነት አብረው እንዲኖሩ በተጠሩበት ወቅት እጅግ አስፈላጊ ነው።

እውነተኛ ውይይት የሚመሠረተው በፍቅር ላይ መሆኑን ‘የእኛ ዘመን’ የተሰኘ ሐዋርያዊ ሠነድ ያስታውሰናል። ይህም የሰላም፣ የፍትህ እና የእርቅ ብቸኛው መሠረት ሲሆን፥ ማንኛውንም ዓይነት መድልዎ ወይም ስደት አጥብቆ በመቃወም የእያንዳንዱን ሰው እኩል ክብር ያረጋግጣል (ቁ. 5)።”

 

29 Oct 2025, 16:40