ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዕለት ከጥንዶች ጋር ሲገናኙ  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዕለት ከጥንዶች ጋር ሲገናኙ   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ቤተሰብን ለመታደግ የምንችለውን ማድረግ ይገባል” ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የጋብቻ እና የቤተሰብ ጥናት ሥነ-መለኮታዊ ተቋማት የመጡ መምህራንን እና ተማሪዎችን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለእንግዶቹ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “በሁሉም ቦታ እና ሁልጊዜ ቤተሰብን ለመደገፍ፣ ለመከላከል እና ለማሳደግ ተጠርተናል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ዓርብ ጥቅምት 14/2018 ዓ. ም. ጠዋት በቫቲካን ለተቀበሏቸው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የጋብቻ እና የቤተሰብ ጥናት ሥነ-መለኮታዊ ተቋም አባላት ባደረጉት ንግግር፥ “በየትኛውም ሥፍራ እና ጊዜ ቤተሰብን ለመደገፍ፣ ለመከላከል እና ለማሳደግ ተጠርተናል” ሲሉ  በድጋሚ አረጋግጠዋል።

ተግዳሮቶቹ በልዩ ልዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ሁኔታዎች ውስጥ የተለያዩ መሆናቸውን በማስገንዘብ፥ ምእመናን ከሁሉም በላይ ቤተሰብን ከወንጌል ጋር በተጣጣመ የአኗኗር ዘይቤ ዘወትር መደገፍ እንዳለባቸው አደራ ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ለእንግዶቹ ባደረጉት ንግግር፥ “ሕይወትን እና ማህበረሰብን የሚቀይር የወንጌል ምስክርነት ቤተሰብን ለመደገፍ የሚያስችሉ የተቀናጁ እርምጃዎን እንድንወስድ ያበረታታናል” ብለው፥ “የአንድ ሀገር ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወት ጥራት የሚለካው በተለይ ቤተሰቦች ጥሩ ኑሮ እንዲኖሩ፣ ለራሳቸው ጊዜ እንዲያገኙ እና አንድነታቸውን የሚያረጋግጡባቸው ትስስሮችን እንዲዳብሩ በሚያስችላቸው መንገድ ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

“ብዙውን ጊዜ የእርስ በርስ ግንኙነት ጠፍቶ ምርታማነትን እና ችኮላን ብቻ በሚመለከት ማኅበረሰብ ውስጥ ለቤተሰብ ፍቅር ቦታን መስጠት አጣዳፊ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።

አዲስ ሕይወት ወደ ዓለም በማምጣት የሚያስገኘውን ደስታ ከፍ ማድረግ

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ልጅ ለመውለድ በዝግጅት ላይ የሚገኙ ሴቶች አዲስ ሕይወት ወደ ዓለም ማምጣት የሚያስገኘውን ደስታ ማድነቅ ይገባቸዋል” ሲሉ መናገራቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስታውሰዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ “ቀላል እና ጥልቅ እውነትን ያካተተ በመሆኑ የሰው ልጅ ሕይወት ስጦታን ዘወትር በአክብሮት፣ በእንክብካቤ እና በምስጋና መቀበል ያስፈልጋል” ብለው፥ በብቸኝነት ወይም በመገለል ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ እርጉዝ እናቶች እውነታን በመጋፈጥ የእናትነትን ሙሉ ክብር መመለስ የሲቪል እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ቁርጠኝነት እና ግዴታ ነው”ሲሉ ተናግረዋል።

“ለዚህ ዓላማ ተጨባጭ የሆኑ ተነሳሽነቶች አስፈላጊ ናቸው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥  በተለይም በቂ የኑሮ እና የሥራ ሁኔታዎችን የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችን መቅረጽ፤ የመውለድ ውበት የሚገነዘቡ ልማዳዊ እና ባህላዊ ተነሳሽነቶችን በቅርበት መንከባከብ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበው፥ እናትነትን እና አባትነትን በዚህ መንገድ መጠበቅ በምንም መልኩ በማኅበረሰቡ ጫንቃ ላይ የሚወድቅ ሸክም ሳይሆን ነገር ግን የሚያጠናክር እና የሚያድስ ተስፋ ነው” ብለዋል።

የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቫቲካን የተሰበሰቡት ፕሮፌሰሮች እና ተማሪዎች በቤተሰብ እና በቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መካከል ያለውን ትስስር የማጠናከር ተግባርን በማስታውስ፥ ይህም በሁለት ተጓዳኝ አቅጣጫዎች ሊቀጥል እንደሚችል፥ እነርሱም “ስለ ቤተሰብ ማጥናት ቤተ ክርስቲያን ስለ ማኅበራዊ ሕይወት የምታቀርበው የአባትነት አስፈላጊ ጥበብ  እና ይህን አባትነት በቤተሰብ ልምዶች በማበልጸግ የቤተ ክርስቲያንን ማኅበራዊ አስተምህሮ መርሆዎች በተሻለ ሁኔታ መረዳት” መሆናቸውን አብራርተዋል።

“ይህ ትኩረት በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ የተጠቀሰውን እና በቀደሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በተደጋጋሚ የተገለጸውን፥ ቤተሰብ የመጀመሪያው የኅብረተሰብ ዋና ክፍል እና መሠረታዊ የሰው ልጅ ትምህርት ቤት ነው” የሚለውን አስተሳሰብ ለማዳበር የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

ኢየሱስ የወጣቶችን ልብ እያንኳኳ ይገኛል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሐዋርያዊ አስተሳሰባቸው፥ “በብዙ የዓለም ክፍሎች ጋብቻን አለማድነቅ ወይም አለመቀበል ዝንባሌን ችላ ማለት አንችልም” ብለው፥ የጋብቻ እና የቤተሰብ ጥናት ሥነ-መለኮታዊ ተቋማት መምህራን ይህን በማሰብ “በጋብቻ ምስጢር ዝግጅት ወቅት በእያንዳንዱ ወንድ እና ሴት ልብ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔር ጸጋ በትኩረት እንዲከታትሉ አደራ ብለዋል።

“ወጣቶችም ቤተ ክርስቲያን ከምታቀርብላቸው የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ጋር የማይጣጣሙ ምርጫዎችን ቢያደርጉም እግዚአብሔር የልባቸውን በር ማንኳኳቱን ቀጥሎ አዲስ የውስጥ ጥሪ እንዲቀበሉ ያዘጋጃቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ጸሎታችሁ የወጣቶችን ሕሊና ሊነካ ይችላል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለጋብቻ እና የቤተሰብ ጥናት ሥነ-መለኮታዊ ተቋማት መምህራን ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የምርምር ሥራችሁ ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት የተገናኘ ከሆነ የወጣቶችን ሕሊና በጥልቀት ሊነኩ የሚችሉ አዳዲስ ቃላትን የማግኘት ድፍረት ታገኛላችሁ” ብለው፥ “ጊዜያችን ልብን በሚያደናግሩ ውጥረቶች እና ርዕዮተ ዓለሞች ብቻ የተሞላ ሳይሆን በተለይም በወጣቶች መካከል መንፈሳዊነትን፣ እውነትን እና ፍትህን የመፈለግ ምልክት እያደገ ያለበት” ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።

ማዳመጥና ጸሎት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለጋብቻ እና የቤተሰብ ጥናት ሥነ-መለኮታዊ ተቋማት መምህራን ባስተላለፉት የማበረታቻ መልዕክት፥ የሲኖዶሳዊነት ጉዞን ዋና የትምህርታቸው አካል እንዲያደርጉት በማበረታታት፥ በተለይም በዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በትዳርና በቤተሰብ አገልግሎት አብሮ ማደግን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት መደማመጥን መለማመድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

እምነትን ለሌሎች ማስተላለፍን በተመለከተ ብዙ ሊማሩት የሚገቡ ነገሮች መኖራቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ የማዳመጥ እና የጸሎት ልምምድ፣ ስለ ፍቅር እና ስለ ሰላም ማስተማር፣ ከስደተኞች ጋር ወንማማችነትን መፍጠር እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤን ማድረግ እንደሚገባ በማሳሰብ፥ በተለይም የቤተሰብ ሕይወት እነዚህን በሙሉ በቆራጥነት እና በቅድስና ምስክርነት እንደሚያስተምራቸው አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመጨረሻም፣ ተማሪዎቹ እና መምህራኑ አዲሱን የትምህርት ዓመት በተስፋ እንዲጀምሩ በማሳሰብ፥ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ዘወትር በእውነት እና በሕይወት ጸጋ እንደሚደግፈን እርግጠኞች ነን” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

 

 

25 Oct 2025, 17:13