ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ሊዮ 14ኛ፥ የዓለም አቀፍ የሚስዮናውያን እና የስደተኞች ኢዮቤልዩ መስዋዕተ ቅዳሴን መርተዋል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ሊዮ 14ኛ፥ የዓለም አቀፍ የሚስዮናውያን እና የስደተኞች ኢዮቤልዩ መስዋዕተ ቅዳሴን መርተዋል  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የዓለም መሪዎች ለጋዛ የሰላም ስምምነት ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እሑድ መስከረም 25/2018 ዓ. ም. በመሩት ዓለም አቀፍ የሚስዮናውያን እና የስደተኞች ኢዮቤልዩ መስዋዕተ ቅዳሴ መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የጋዛ ሕዝብ ከፍተኛ ስቃይ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ የመጣውን የፀረ ሴማዊ ጥላቻን በማውገዝ፥ የእስራኤል እና የሐማስ የሰላም ስምምነት በተቻለ ፍጥነት ቶሎ እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት በርካታ ምዕመናን ባደረጉት ንግግር፥ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በሚደረግ የሰላም ድርድር ላይ የፖለቲካ መሪዎች የራሳቸውን ጥረት እንዲጨምሩ ጥሪ አቅርበው፥ “የሰላም ጥረቱ በቅርቡ ጉልህ ውጤት አሳይቷል” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የሰላም ስምምነቱ በተቻለ ፍጥነት እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ምዕመናን በሙሉ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲገኝ በጸሎት እንዲተባበሩ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ጋዛ ውስጥ በፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ ባለው ከፍተኛ ስቃይ ማዘናቸውን ገልጸው ከቤተልሔም ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ምዕመናን ሰላምታቸውን አቅርበዋል።

በተለይ በእንግሊዝ ማንቸስተር በሚገኝ ምኩራብ ላይ ሐሙስ መስከረም 22/2018 ዓ. ም. የተፈጸመውን ጥቃት በመጥቀስ፥ በዓለም ላይ የፀረ-ሴማዊ ጥላቻ መጨመር ያሳሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለመስዋዕተ ቅዳሴ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ሰላምታ ሲሰጡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለመስዋዕተ ቅዳሴ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ሰላምታ ሲሰጡ   (@Vatican Media)

ቤተ ክርስቲያን በፍፁም ሚስዮናዊት ናት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዓለም አቀፍ የሚስዮናውያን እና የስደተኞች ኢዮቤልዩ መስዋዕተ ቅዳሴ ማብቂያ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በዕለቱ በጣለው ቀላል ዝናብ ውስጥ በአደባባዩ የተገኙትን ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን አመስግነዋል።

“ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ሚስዮናዊ ናት” ሲሉ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “በዓለም ዙሪያ በወንጌል አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሚስዮናውያን፣ መከራን እና ስቃይን በመሸሽ አገራቸውን ጥለው የወጡ ስደተኛ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ይህንን ያስታውሱናል” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም፥ “ማንም ሰው መሰደድ የለበት፥ እንደ ባዕድ ወይም እንደ ችግረኛ መበዘበዝ ወይም መበደል የለበትም” ብለው፥ “ሰብዓዊ ክብር ዘወትር መቅደም አለበት” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመጨረሻም፥ ማክሰኞ መስከረም 20/2018 ዓ. ም. በፊሊፒንስ በሬክተር መለኪያ 6.9 በሚደርስ ርዕደ መሬት የተጎዱትን በጸሎታቸው ማስታወሳቸው ገልጸው፥

ከውድ የፊሊፒንስ ሕዝብ ጋራ ያላቸውን አጋርነት በማስታወስ፥ “በአደጋው የተጎዱት በኅብረት እንዲቆሙ እና ዕርዳታም እንዲደርሳቸው” በማለት አሳስበዋል።

 

06 Oct 2025, 17:13