ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ሊዮ ማርያም ወደ ልጇ ኢየሱስ ትመራን ዘንድ ልንጸልይ ይገባል ማለታቸው ተገለጸ!

እሁድ ጥቅምት 02/2018 ዓ.ም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ኢዮቤልዩ በተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ምእመናን በቅድስት እናት ወደ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት መዞር እና መከተል እንደሚችሉ የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ እንዲያዩ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እሁድ ጠዋት በቫቲካን በተካሄደው የማርያም መንፈሳዊ ኢዮቤልዩ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ “እምነታችንን የሚመግበው የማርያም መንፈሳዊነት ኢየሱስ ማእከል ነው” ሲሉ አሳስበዋል።

ቅዱስ አባታችን ባደረጉት ስብከት፣ ይህንን መንፈሳዊነት በማንፀባረቅ፣ “እንደ እሑድ በየሳምንቱ በትንሳኤ ሙታን እዲስ ሳምንት ይከፈታል” በማለት ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የማርያም መሰጠት ወንጌልን እንደሚያገለግል እና ምእመናን በተሟላ ሁኔታ እንዲኖሩት እንደሚረዳቸው አስረድተዋል።

"የማርያም መንፈሳዊነት በወንጌል አገልግሎት ላይ የተመሰረተ ነው፣ የዋዕነቱን ይገልጣል" ሲሉ ተናግሯል።

የማርያም መንፈሳዊነት

አክሎም “ለናዝሬቷ ማርያም ያለን ፍቅር ከእሷ ጋር የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንድንሆን ያደርገናል” ብሏል። "ወደ እርሱ እንድንመለስ ያስተምረናል፣ እናም በሕይወታችን ውስጥ ያጋጠሙንን ሁኔታዎች እንድናሰላስል እና ከሙታን የተነሣው አሁንም ወደ እኛ መጥቶ የሚጠራን በእርሷ በኩል ነው" ያሉት ቅዱስነታቸው ይህ መንፈሳዊነት ምእመናንን ወደ እግዚአብሔር የማዳን ሥራ ይስባቸዋል ብሏል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የማርያም መንፈሳዊነት ሰማይ በተከፈተበት ታሪክ ውስጥ ያስገባናል" ያሉ ሲሆን በመቀጠልም “ትዕቢተኞች በትምክህታቸው ሲበተኑ፣ ኃያላን ከዙፋናቸው ሲወርዱ፣ ባለጠጎችም ባዶ እጃቸውን ሲሰደዱ ማየት ይጠቅመናል፣ የተራበውን በበጎ ነገር እንድንሞላ፣ የተዋረዱትን እንድናነሳ፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት እንድናስታውስ እና በክንዱ ኃይል እንድንታመን ይገፋፋናል" ብለዋል።

የማርያም ውዳሴ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ማርያም የአምላክን ፈቃድ መቀበሏን በማሰላሰል “እነሆኝ” የሚለው ቃል የአንድ ጊዜ ድርጊት ሳይሆን የዕለት ተዕለት ቁርጠኝነት እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን “ኢየሱስ ማርያምን ‘እነሆኝ’ እንድትል እንደጠየቃት የመንግሥቱ አካል እንድንሆን ጋብዞናል፤ ይህም አንድ ጊዜ ከተሰጠ በየቀኑ ይታደሳል ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስለ አሥሩ የሥጋ ደዌ በሽተኞች በሚናገረው በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ታሪክ ላይ አስተንትኗቸውን ማድረግ ሲቀጥሉ ከእነዚህም መካከል ከተፈወሱት አሥሩ ሰዎች መካከል ለማመስገን ወደ ኋላ የተመለሰው አንዱ ብቻ እንደ ነበረ እና ዘጠኙ ለማመስገን አልተመለሱም ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

"ለማመስገን የማይመለሱ በወንጌል ውስጥ ያሉ ለምጻሞች እንደ እነርሱ እኛንም የእግዚአብሔር ጸጋ ሊነካን ይችላል፣ እኛ ግን ምንም ምላሽ እንዳልሰጠን ያስታውሰናል" ሲሉ ቅዱስነታቸው የተናገሩ ሲሆን " ሊፈውሰን ይችላል፣ ነገርግን አሁንም መቀበል ተስኖናል፤ ስለዚህ ኢየሱስን እንድንከተል በማይመራን መንገድ ወደ ቤተመቅደስ እንዳንወጣ እንጠንቀቅ" ሲሉ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ማስጠንቀቂያ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አማኞችን ከባልንጀሮቻቸው የሚነጥሉ ሃይማኖታዊ ድርጊቶችን አስጠንቅቀዋል።“አንዳንድ የአምልኮ ዓይነቶች ከሌሎች ጋር መግባባትን አያሳድጉምና ልባችንን ሊያደነዝዙ ይችላሉ” ብሏል። "በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ፣ እግዚአብሔር በህይወታችን ውስጥ ያስቀመጣቸውን ሰዎች ማግኘት ተስኖናል፣ ልክ እንደ ማርያም፣ አለምን ለመለወጥ እና በውዳሴ ደስታ ለመካፈል አስተዋፅዖ ማድረግ ተስኖናል" ያሉ ሲሆን አክሎም “የተለያዩትን ማለትም ብዙውን ጊዜ ድሆችን—የሚወገዱና የሚጣሉ ‘ለምጻሞች’ እንደሆኑ ለመፈረጅ ከሚያስችል ማንኛውም የእምነት መጠቀሚያ እንጠንቀቅ" ሲሉ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ክርስቶስን ከማርያም ጋር መከተል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የማርያም ጉዞ ሁልጊዜ ወደ ኢየሱስ እና ወደ ተቸገሩ ሰዎች እንደምያቀርብ ተናግረዋል።

"የማርያም መንገድ የኢየሱስን መንገድ ይከተላል፣ ይህም እያንዳንዱን ሰው፣ በተለይም ድሆችን፣ የቆሰሉትን እና ኃጢአተኞችን እንድንገናኝ ይመራናል" ብሏል።

የፍቅር እና የርህራሄ ምሳሌ

እውነተኛ የማርያምን መንፈሳዊነት የእግዚአብሔርን ርኅራኄ በቤተክርስቲያኗ ሕይወት ውስጥ እንደሚገልጥ አክለው የተናገሩት ቅዱስነታቸው "ትክክለኛው የማርያን መንፈሳዊነት የእግዚአብሔርን ርኅራኄ፣ 'እናት የመሆን' መንገድን፣ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ብርሃን ያመጣል" ሲሉ በአጽኖት ተናግረዋል።

በላቲን ቋንቋ "Evangelii Gaudium" (የወንጌል ደስታ) የተሰኘውን የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ በመጥቀስ “በማንኛውም ጊዜ ወደ ማርያም ስንመለከት፣ የፍቅር እና የርህራሄ አብዮታዊ ተፈጥሮን እንደገና እናምናለን በእሷ ውስጥ፣ ትሕትና እና ርኅራኄ የደካሞች መገለጫ ባዕሪያት ሳይሆኑ  ነገር ግን ለራሳቸው አስፈላጊ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ሌሎችን በቸልተኝነት መያዝ እንደ ማይገባ የሚገልጹ የጠንካሮች ባሕርያት መሆናቸውን እናያለን” ብሏል።

ወደ ማህበራዊ ለውጥ እና እድሳት መንገድ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለማርያም መሰጠት ርህራሄን ሳያጡ ወደ ተግባር እና ወደ ማህበራዊ ለውጥ ያመራሉ ብለዋል ።

“ማርያምን ስናሰላስል፣ ‘ኃያላንን ከዙፋናቸው ስላወረደ’ እና ‘ባለጠጎችን ባዶ እጃቸውን እንደ ሰደደ’ አምላክን ያመሰገነችው ፍትሕን ለማግኘት የምንፈልገውን የቤት ውስጥ ሙቀት የምታመጣልን እንደሆነች እንገነዘባለን ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል “ፍትሕና ሰላም በሚፈልግ ዓለም ውስጥ፣ የክርስቲያናዊ መንፈሳዊነትን እና ሕዝባዊ ቁርጠኝነትን እናነቃቃ፣ በአምላክ የተባረኩ ክስተቶች እና ቦታዎች የምድርን ገጽታ ለዘለዓለም እንቀይር፣ እነሱን ለመታደስና ለመለወጥ እንደ ኃይል እንጠቀምባቸው" ሲሉ ቅዱስነታቸው አክለው ተናግረዋል።

የኢዮቤልዩ ግብዣ በዓል ብቻ ሳይሆን የጥልቅ ተሃድሶ ጥሪ መሆኑንም አክለው ያመለከቱት ቅዱስነታቸው "በእርግጥም እያከበርን ያለነው ኢዮቤልዩ የመለወጥ እና የመልሶ ማቋቋም፣ የማሰላሰል እና የነጻነት ጊዜን ይጠይቃል" ብሏል።

እራሳችንን ለማርያም በአደራ እንስጥ

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ቤተክርስቲያንን ለቅድስት እናት ማርያም አደራ በመስጠት ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

“ተስፋችን እጅግ ቅድስት በሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማልጅነት ወደ የተሰቀለው ጌታ ወደ ኢየሱስም ትመራን ዘንድ ልንጸልይ የገባል” ካሉ በኋላ ስብከታቸውን ቅዱስነታቸው አጠናቀዋል።

 

13 Oct 2025, 15:45