ፈልግ

የእስራኤል ወታደሮች በከፊል መውጣታቸውን ተከትሎ በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ወደ ፈረሰባቸው ቤታቸው ሲመለሱ የእስራኤል ወታደሮች በከፊል መውጣታቸውን ተከትሎ በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ወደ ፈረሰባቸው ቤታቸው ሲመለሱ  (ANSA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የቅድስት ሀገር የሰላም ተስፋ ጭላንጭሎችን በማወደስ ለዩክሬን ጸለዩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ከእመቤታችን ማርያም መንፈሳዊ ማኅበርተኞች የኢዮቤልዩ በዓል መስዋዕተ ቅዳሴ በመቀጠል በፖለቲካ ውዥንብር እና አለመረጋጋት ምክንያት በቅድስት ሀገር፣ በዩክሬን እና በፔሩ የሚሰቃዩት ሕዝቦችን በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጥቅምት 2/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት የእመቤታችን ማርያም መንፈሳዊ ማኅበራት አባላት ጋር ባቀረቡት የኢዮቤልዩ መስዋዕተ ቅዳሴ ማጠቃለያ ላይ በግጭት፣ በፖለቲካ አለመረጋጋት እና በሌሎች የፍትህ እጦት ውጤቶች የሚሰቃዩትን በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

ሰላም በቅድስት ሀገር

በተለይም ከፍተኛ የሰው ሕይወት የጠፋበትን የቅድስት ሀገር ጦርነትን በማስታወስ ጸሎታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የሁለት ዓመታት ግጭት በሁሉም ቦታ ሞትን እና ውድመትን ማስከተሉን ጠቅሰው፥ በተለይ ልጆቻቸውን፣ ወላጆቻቸውን እና ጓደኞቻቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ በሞት ባጡ ሰዎች ልብ ውስጥ ሐዘን ማስከተሉን አስታውሰዋል።

ቤተ ክርስቲያን ከተጎዱት ጎን እንደምትገኝ ያረጋገጡት ቅዱስነታቸው፥ እግዚአብሔር ለሕዝቡ “እኔ ወደድኳችሁ”በማለት በጨለማ ጊዜም ቢሆን የማይናወጥ ብሮነት ያለው መሆኑን አስታውሰዋል።

እነዚህ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ንግግሮች በቅርቡ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተደረገው ስምምነት የሚያበረታታውን የተስፋ መልዕክት ተከትሎ ሲሆን፥ የሁለቱም ማለትም የእስራኤል እና የፍልስጤም ሕዝቦች ሕጋዊ ምኞቶችን ወደሚያከብር ወደ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም የሚወስደውን መንገድ በድፍረት እንዲቀጥሉ ሁሉም ተሳታፊ አካላትን አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የሰው ልጅ ሌላውን እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም የማየት ችሎታን እንደገና እንዲያገኝ በመጸለይ፥ ይቅርታን እና ዕርቅን ማድረግ የሚችል መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል።

በዩክሬን ሰላም እንዲወርድ!

በጦርነት ውስጥ የምትገኘውን ዩክሬን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ጦርነቱ በከተሞች እና በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ያደረሰውን ውድመት፣ ሕፃናትን ጨምሮ የበርካታ ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ያጠፋውን እና ለጨለማ እና ለብርድ የዳረጋቸውን አዲስ የዓመፅ እና የጥፋት ማዕበልን አስታውሰዋል።

“በስቃይ መካከል የሚገኘውን የዩክሬይን ሕዝብ በልቤ ውስጥ አስታውሳለሁ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በአገሪቱ ውስጥ አመጽ ቆሞ ውጤታማ ውይይት እንዲካሄድ ያቀረቡትን ጥሪ በድጋሚ አድሰዋል።

በፔሩ ውስጥ የሚታይ የፖለቲካ አለመረጋጋት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በፖለቲካ ሽግግር ወቅት ችግር እያጋጠመው ለሚገኘው የፔሩ ሕዝብ ያላቸውን ቅርበት ገልጸው፥ ከቅርብ ወራት ወዲህ በአገሪቱ ባለው አመራር ውጥረት ነግሶ የተሃድሶ ጥሪ እየቀረበ መሆኑ ታውቋል።

ለሀገር አንድነት ጸሎት ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፥ ፔሩ በእርቅ፣ በውይይት እና በብሔራዊ አንድነት ጎዳና እንድትቀጥል መጸለያቸውን ገልጸው፥ ጸሎታቸውን ያቀረቡትም ብዙ የፔሩ ነዋሪዎች በሰላማዊ መንገድ ለዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መረጋጋት እና አዲስ ቁርጠኝነት በሚፈልጉበት ወቅት እንደሆነ ታውቋል።

የሠራተኞች ድህንነት እንዲጠበቅ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመጨረሻም፥ ጣሊያን ውስጥ በሥራ ላይ አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች ባስታወሰችበት ብሔራዊ ቀን ለሞቱት ሰዎች ጸሎት በማድረግ ለሁሉም ሠራተኞች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

13 Oct 2025, 16:15