ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ከሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ስጦታ ሲበረከትላቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ከሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ስጦታ ሲበረከትላቸው   (@VATICAN MEDIA)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “የሃይማኖት ነፃነት እውነትን ለመፈለግ እና በተጨባጭ ለመኖር አስፈላጊ ነው" ሲሉ ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋት ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን አባላትን ዓርብ መስከረም 30/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፥ የሃይማኖት ነፃነትን አስፈላጊ የሰው ሕይወት አካል በማድረግ ላበረከቱት ተግባር አመስግነዋቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የሃይማኖት ነጻነት በማስመልከት በየዓመቱ የሚወጣው ዓለም አቀፍ ሪፖርት በጥቅምት 11/2018 ዓ. ም. ከመታተሙ በፊት ዕርዳታን ለሚያስፈልጋት ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ከሚያደርግ ከጳጳሳዊ ፋውንዴሽ አባላት ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በንግግራቸው፥ “የፋውንዴሽኑ አባላት የሮም ጉብኝት ክርስቲያኖችን ጨምሮ የልዩ ልዩ እምነቶች ተከታዮች ላይ ጠላትነት እና ብጥብጥ እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነው” ብለዋል።

አክለውም “የፋውንዴሽኑ ተልዕኮ ቤተ ክርስቲያን ከግፍ እና ከአመጽን በተቃራኒ የተሰደዱ ወንድሞችን እና እህቶችን እፈጽሞ እንደማትረሳቸው መናገር ነው” ሲሉ አስታውቀዋል።

“ማንኛውም ሰው የእምነት ነፃነትን የማግኘት መብቱ አማራጭ ሳይሆን አስፈላጊ ነው” በማለት የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እያንዳንዱ ሰው በልቡ እውነትን፣ ትርጉምን ለማወቅ፥ ከሌሎች ሰዎች እና ከእግዚአብሔር ጋር አንድነትን ለመፍጠር ጥልቅ ጉጉት አለው” ብለዋል።

“የሃይማኖት ነጻነት በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሰው ክብር ላይ የተከሠረተ፣  ግለሰቦች እና ማኅበረሰቦች በምክንያታዊነት እና በነፃ ምርጫ እውነትን እንዲፈልጉ፣ በነጻነት እንዲኖሩ እና ስለ እውነትም በግልፅ እንዲመሰክሩ ያስችላቸዋል” ብለዋል።

“በመሆኑም የሃይማኖት ነፃነት ሕሊናችንን የምናለማምድበት፣ የምንጠቀምበት እና የሞራል ምህዳርን የሚጠብቅ የሕብረተሰቡ የማዕዘን ድንጋይ ነው” ብለዋል።

“የሃይማኖት ነፃነት ከመንግሥት የተሰጠን ልዩ ሕጋዊ መብት ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ እርቅ እንዲፈጠር የሚያደርግ መሠረታዊ መንገድ ነው” ብለዋል።

የሃይማኖት ነፃነት ሲነፈግ በማኅበረሰቦች መካከል ያለው የሥነ ምግባር እና የመንፈሳዊነት ትስስር ቀስ በቀስ እንደሚፈርስ ሰዎች የሚመሰክሩት መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ተናግረዋል።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ “የሃይማኖት፣ የአስተሳሰብ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት እና የሌሎችን አመለካከት ካላከበሩ በቀር ሰላም ሊኖር አይችልም” ብለዋል።

ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ ሠነድ በማስታወስ እንደተናገሩትም፥ የሃይማኖት ነፃነት በእያንዳንዱ ሀገር እውቅና ሊሰጠው የሚገባ መብት እንደሆነ በማስረዳት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሁሉን ሰው የሃይማኖት ነፃነት ታከብራለች” ብለዋል።

ዕርዳታ ለሚያስፈልጋት ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1947 ዓ. ም መመስረቱን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፣ በጦርነት ምክንያት ለሚደርስ መከራ ምላሽ በመስጠት፣ ስቃይ ወይም እንግልት በሚያጋትማት ቦታ በሙሉ ድምፅ እየሰጠ የይቅርታ እና የእርቅ መንገድን ለማግኘት የሚጥር መሆኑን አስረድተዋል።

በየሁለት ዓመቱ የሚታተመውን የፋውንዴሽኑ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነጻነት ሪፖርት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ዓለም አቀፍ ሪፖርቱ ግንዛቤን ለማስጨበጥ እና የብዙዎችን ስውር ስቃይ ለማጋለጥ ጠቃሚ መሣሪያ በመሆኑን አወድሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በተጨማሪም፥ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ተቋማት ላደረገው የገንዘብ ድጋፍ አመስግነው በተለይም ለመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ለቡርኪናፋሶ እና ለሞዛምቢክ ያደረገውን ድጋፍ ጠቅሰዋል።

ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ ጸሎት ቤቶችን በሚገነባባቸው፣ ገዳማውያት እህቶችን በሚደግፍባቸው፣ ሬዲዮ ጣቢያን በሚያቋቋምባቸው ወይም መኪናን በሚለግስባቸው አገራት በሙሉ የቤተ ክርስቲያንን ሕይወት እንዲሁም የሕብረተሰቡን መንፈሳዊ እና ሥነ-ምግባራዊ መዋቅር ያጠናክራል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በንግግራቸው መደምደሚያ፥ በአገራት ውስጥ በቁጥር ዝቅተኛ ለሆኑ ክርስቲያኖች የሚደረግ ድጋፍ፥ በአገራቸው ሰላም ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጸው፥ “ይህም በኅብረተሰቡ መካከል የአንድነት እና የወንድማማችነት ሕያው ምልክት እንዲሆኑ በማድረግ ምቹ ዓለምን መፍጠር እንደሚቻል ለጎረቤቶቻቸው የሚያሳዩበት መንገድ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

11 Oct 2025, 15:19