ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል በማቅረብ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል በማቅረብ ላይ  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “እግዚአብሔር ይቅር ባይና ከውድቀታችንም የሚያነሳን ነው” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ረቡዕ መስከረም 21/2018 ዓ. ም. ለተሰበሰቡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዮሐ. 20: 19-23 በተጻፈው ላይ በማስተንተን ባቀረቡት አስተምህሮ፥ እግዚአብሔር መሐሪ እንደሆነ፣ በኀጢአት የወደቁትንም የሚያነሳ እና መተማመንን የሚያድስ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በዚያው ከሳምንቱ የመጀመሪያ በሆነው ቀን፥ በመሸ ጊዜ፥ ደቀመዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ በመካከላቸው ቆሞ ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። ይህንንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀመዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። ኢየሱስም ዳግመኛ ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ’ አላቸው። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኀጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል’ አላቸው” (ዮሐ. 20: 19-23)።

ክቡራን እና ክቡራት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፥

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የእምነታችን ማዕከል እና የተስፋችን ምንጭ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ላይ የጸና ነው። ወንጌላትን በጥሞና ስናነብ ይህ ምስጢር የሚያስደንቅን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ከሙታን በመነሳቱ ብቻ ሳይሆን ይህን ለማድረግ የወሰነበት መንገድም ጭምር እንደሆነ እንገነዘባለን። በእርግጥ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ትልቅ ድል ቢሆንም ነገር ግን በጠላቶቹ ላይ የተወሰደው የበቀል እርምጃ አይደለም። ፍቅር ከትልቅ ሽንፈት በኋላ እንደገና መነሳት እንደሚቻል እና ሳያቆም ጉዞውን የሚቀጥል መሆኑን የሚገልጽ አስደናቂ ምስክርነት ነው።

በሰዎች በኩል ከደረሰብን ጉዳት እንደገና ስናገግም ብዙውን ጊዜ የመጀመሪያው ምላሻችን ቁጣ እና ለደረሰብን ጉዳት ካሳ እንዲከፈለን የማድረግ ፍላጎት ነው። ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደዚህ አላደርገም። ኢየሱስ ከሞት ከተንሳ በኋላ አልተበቀለም። ኃይለኛነቱን ማሳየት አልፈለገም። ይልቁንም በየዋህነት ከማንኛውም ቁስል እና ክህደት የሚበልጥ የፍቅር ደስታን አሳየ።

ከሞት የተነሣው ኢየሱስ የበላይነቱን ለመድገም ወይም ለማረጋገጥ ምንም ፍላጎት የለውም። እርሱ ወዳጆቹ ለሆኑት ደቀመዛሙርቱ ተገለጠላቸው። ይህን ያደረገው እርሱን ለመቀበል ያላቸውን ችሎታ ሳያስገድድ በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው። የእሱ ብቸኛው ፍላጎት ደቀ መዛሙርቱ የጥፋተኝነት ስሜትን እንዲያሸንፉ በመርዳት ወደ መግባባት እንዲመለሱ ነው። ይህን በደንብ የምናየው በላይኛው ክፍል ውስጥ በፍርሃት ተውጠው ለሚገኙ ወዳጆቹ በተገለጠላቸው ጊዜ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ጨለማ ውስጥ የታሰሩትን ነጻ ለማውጣት ወደ ጥልቅ ሞት ከወረደ በኋላ በፍርሃት ተውጠው ለሚገኙ ሰዎች ማንም ሊጠብቀው የማይችለውን የሰላም ስጦታ አመጣላቸው። ይህም የኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ አስደናቂ ኃይል የተገለጠበት ጊዜ ነው።

እርሱ ያቀረበላቸው ሰላምታ ቀላል እና ተራ ሰላምታ ማለት ይቻላል። “ሰላም ለአንተ ይሁን!” (ዮሐ. 20:19) ነገር ግን በጣም በሚያስደስት ሁኔታ በእጅ ምልክት የታጀበ ከመሆኑ የተነሳ ግራ የሚያጋባ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ እጆቹን እና ጎኑን በስሜታዊነት ምልክቶች አሳያቸው። በእነዚያ አስከፊ ሰዓታት እርሱን ክደው ጥለውት ለነበሩት ቁስሎቹን ለምን አሳያቸው? የሕመም ምልክቶችን ለምን አልደበቀም? የኀፍረት ቁስሉን እንደገና ከመክፈት ለምን አልተቆጠበም?

ወንጌሉ እንደሚነግረን ደቀ መዛሙርቱ ጌታን ባዩት ጊዜ ደስ እንዳላቸው ይላል (ዮሐ. 20፡20)። ምክንያቱ ጥልቅ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከደረሰበት መከራ ሁሉ ጋር ሙሉ በሙሉ ታርቋል። የቂም እና የበቀል ሃሳብ የለም። ቁስሎቹ ጠላቶቹን ለመበቀል ሳይሆን ከማንኛውም ዓይነት ክህደት የበለጠ ጠንካራ ፍቅር እንዳለው ለማረጋገጥ ያገለግላሉ። በውድቀታችን ወቅት እንኳ ቢሆን እግዚአብሔር ከእኛ ዘንድ እንዳላፈገፈገ የሚያረጋግቱ ናቸው። እርሱ በእኛ ተስፋ አልቆረጠም።

በዚህ መንገድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን እንደ እርቃን መከላከያ የሌለው መሆኑን ያሳያል። እርሱ ከእኛ ምንም አይጠይቅም። ከእኛ ዘንድ ቤዛንም አልፈለገም። ፍቅሩ የማይዋረድ ነው። ለፍቅር የተሠቃየ ሰው ሰላም እና በመጨረሻ ዋጋ ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል።

ይልቁን እኛ ቁስላችንን የምንሸፍነው ከትዕቢት የተነሳ ወይም ደካሞች ልንመስል እንችላለን ብለን በመስጋት ነው። ‘ምንም ችግር የለውም፣ ሁሉም ያልፋል’ እንላለን። ነገር ግን እኛን ካቆሰሉን ነገሮች ጋር በእውነት ሰላም የለንም። አንዳንድ ጊዜ ለጥቃት መጋለጣችን እንዳንታይብን ይቅር ለማለት የምናደርገውን ጥረት መደበቅ እንመርጣለን። ኢየሱስ ግን እንዲህ አያደርግም። ቁስሉን የይቅርታ ዋስትና አድርጎ ያቀርባል። ትንሳኤውም ያለፈውን ለመደምሰስ ሳይሆን ወደ ምሕረት ተስፋ መቀየሩን የሚያሳይ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ በማለት ይደግማል፥ ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን!’፤ ‘አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ’ በማለት አክሎ ተናግሯል(ዮሐ. 20:21)። ኢየሱስ ክርስቶስ በእነዚህ ቃላት ሐዋርያትን ሃላፊነትን በኃይል ሳይሆን በዓለም ውስጥ የማስታረቅ መሣሪያዎች እንዲሆኑ አደራ አላቸው። “ውድቀት እና ይቅርታ ያጋጠማችሁ እናንተ ካልሆናችሁ በቀር  የእግዚአብሔርን መሐሪነት ሌላ ማን ሊያውጅ ይችላል?” እንደ ማለት አስረዳቸው።

ኢየሱስ እፍ አለባቸው፤ መንፈስ ቅዱስን ሰጣቸው (ዮሐ. 20:22)። ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባቱ በመታዘዝ እስከ መስቀል ሞት ድረስ በፍቅር የደገፈው ይህ መንፈስ ቅዱስ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሐዋርያት ስላዩት እና ስለሰሙት ነገር በሙሉ ዝም ማለት አልቻሉም። የእግዚአብሔርን ይቅር ባይ፣ ከሞት የሚያነሳ እና እምነትን የሚመልስ መሆኑን መሰከሩ።

የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ምንጭም ይህ ነው። በሌሎች ላይ ስልጣንን እንዲኖር ማድረግ ሳይሆን ለሚወዷቸው ሰዎች በማይገባቸው ጊዜ ደስታን በትክክል ማስተላለፍ ነው። ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ወንዶች እና ሴቶች ወደ ሕይወት ተመልሰው ለሌሎችም እንዲሰጥ የሚያስችላቸው ጥንካሬ ነው።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች እኛም ተልከናል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቁስሉን እያሳየን ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን’ ይላል። በምሕረት የተፈወሰውን ቁስላችንን ለሌሎች ለማሳየት አትፍሩ። በፍርሃት ወይም በጥፋተኝነት ወደ ታሰሩ ሰዎች ዘንድ ለመቅረብ አትፍሩ። የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ እኛንም የዚህ ሰላም እና ፍቅር ከየትኛውም ሽንፈት በላይ ብርቱ ምስክሮች ያድርገን።”

 

01 Oct 2025, 16:13