ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በቱርክ እና ሊባኖስ የሚያደርጉት ጉብኝት ዓርማ እና መሪ ቃል ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በቱርክ እና ሊባኖስ የሚያደርጉት ጉብኝት ዓርማ እና መሪ ቃል  

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በቱርክ እና ሊባኖስ የሚያደርጉት ጉብኝት ዓርማ እና መሪ ቃል ይፋ ሆነ

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ጽ/ቤት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቱርክ እና ሊባኖስ ከህዳር 18-23/2018 ዓ. ም. ድረስ የሚያደርጉት የሐዋርያዊ ጉብኝት ዓርማዎችን እና መሪ ቃላትን ሰኞ ጥቅምት 17/2018 ዓ. ም. ይፋ አድርጓል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር መግለጫ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቱርክ እና በሊባኖስ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓርማዎችን እና መሪ ቃላትን ይፋ አድርጎ፥ ይህም የቱርክ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ከህዳር 18-21 እና የሊባኖስ ጉብኝታቸው ከህዳር 21-23/2018 ዓ. ም. መሆኑን አስታውቋል።

የቱርክ ጉብኝት ዓርማ እና መሪ ቃል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅድሚያ ወደ ቱርክ በመጓዝ የኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል በማክበር ዋና ከተማዋ አንካራን፤ ኢስታንቡልን እና ጥንታዊቷ ኒቂያ ዛሬ ኢዝኒክ ተብላ የምትጠራ ከተማን እንደሚጎበኙ ታውቋል።

የቱርክ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓርማ በእውነቱ ይህንን አስፈላጊ መታሰቢያ በዓልን የሚያንፀባርቅ ሲሆን፥ የሁለቱ አኅጉራት ማለትም የእስያ እና የአውሮፓ ግንኙነትን የሚወክል እና ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር እና በሰው ልጅ መካከል እንደ ድልድይ ማገልገሉን የሚያመለክት ክብ ያለው እንደሆነ ተመልክቷል።

በድልድዩ ስር የሚታዩ ሞገዶች የጥምቀት ውሃን እና የኢዝኒክ ሐይቅን ያመላክታሉ ሲል የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል። በዓርማው በስተቀኝ የ2025 ኢዮቤልዩ መስቀል የሚታይ ሲሆን፥ በላይኛው ግራ በኩል የሚታዩ ሦስት የተጠላለፉ ቀለበቶች ቅድስት ሥላሴን የሚወክሉ መሆናቸው ተገልጿል።

ይህ ዓርማ “አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት እና አንድ ጥምቀት” የሚለውን የሐዋርያዊ ጉዞ መሪ ቃል የሚያንፀባርቅ እና ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች ከጻፈው መልዕክት ምዕ. 4፡5 የተወሰደ መሆኑ ታውቋል።

የእግዚአብሔርን አንድነት የሚያመላክት ክብ ምስል ድልድይን፣ ሰዎችን አንድ የሚያደርግ አንድ እምነትን እና ሞገዶችን ከመግለጽ በተጨማሪ ለእግዚአብሔር ልጆች አዲስ ሕይወት የሚሰጥ ጥምቀትን ያመለክታል” ሲል የቅድስት መንበር መግለጫ ገልጾ፥ “ይህም በምሥራቁ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል ወንድማማችነትን እና ውይይትን እንድናሳድግ ይጋብዘናል” ብሏል።

የቱርክ ጉብኝት ዓርማ እና መሪ ቃል
የቱርክ ጉብኝት ዓርማ እና መሪ ቃል

የሊባኖስ ጉብኝት ዓርማ እና መሪ ቃል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቱርክ ካደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ቀጥሎ ወደ ሊባኖስ የሚጓዙ ሲሆን፥ እዚያም ዋና ከተማዋ ቤሩትን ከጎበኟት በኋላ የአናያ፣ የሃሪሳ፣ የቤከርኬ እና የጃል ኤድ ዲብ ከተሞችን እንደሚጎበኙ ታውቋል።

የሊባኖስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓርማ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ቀኝ እጃቸውን ለቡራኬ ማንሳታቸው፣ ሰላምን የሚያመላክት የርግብ ምስል፣ የዝግባ ዛፍ እና የሊባኖስን የእምነት እና የሃይማኖቶች መስማማትን የሚወክል ጥልቅ ታሪክን ያሳያል። በምስሉ በስተቀኝ በኩል የሚታየው መስቀል ከ2025 ዓ. ም. የኢዮቤልዩ ዓርማ የተወሰደ ሲሆን ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባለ እምነት ላይ የተመሠረተ ጽኑ ተስፋን የሚያመላክት እንደሆነ ታውቋል።

“ጥልቅ ሰማያዊ፣ ለስላሳ ሮዝ፣ አረንጓዴ እና ቀላል ሰማያዊ ቀለሞች ጸጥታን የሚገልጹ ሲሆን፥ ከነጭ ቀለም ጋር ተዋሂደው የሊባኖስን የሰላም ናፍቆት ያንጸባርቃል” ሲል የቅድስት መንበር መግለጫ ገልጿል።

ከማቴዎስ ወንጌል ምዕ. 5:9 የተወሰደው እና “ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው” የሚለው መሪ ጥቅስ ቅዱስነታቸው በሊባኖስ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና መልዕክት የያዘ ሲሆን፥ ይህም የሊባኖስን ሕዝብ ለማጽናናት እና በሁሉም ማህበረሰቦች መካከል ውይይትን፣ እርቅን እና ስምምነትን ለማበረታታት ያለመ ነው” ሲል መግለጫው አስረድቷል።

የሊባኖስ ጉብኝት ዓርማ እና መሪ ቃል
የሊባኖስ ጉብኝት ዓርማ እና መሪ ቃል
28 Oct 2025, 15:33