ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከጋቦን ፕሬዝዳንት ጋር ተገናኙ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐሙስ ዕለት ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም ከጋቦን ፕሬዝዳንት ብሪስ ክሎቴየር ኦሊጉዊ ንጌማ ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐሙስ ጥቅምት 20 ቀን ከጋቦን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ብሪስ ክሎቴየር ኦሊጉዊ ንጌማ ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል ሲል የቅድስት መንበር የፕሬስ ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ፕሬዝዳንቱ ከዚያም ከቫቲካን ዋና ጸኃፊ ከሆኑት ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ጋር ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ በመቀጠል ቫቲካን ከተለያዩ አገራት እና ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የምታደርገውን ግንኙነት የሚቆጣጠረው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት ክፍል የባለብዙ ወገን ዘርፍ ምክትል ጸሐፊ ከሆኑት ከየእኔታ ዳንኤል ፓቾ ጋር ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በ"አብሮነት መንፈስ በተካሄደው ውይይት" ወቅት በቅድስት መንበር እና በጋቦን መካከል ያለው "ጥሩ ግንኙነት" ተስተውሏል ሲሉ የቅድስት መንበር የፕሬስ ጽ/ቤት መግለጫ አስታውቋል። "የአገሪቱን የፖለቲካ እና ማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የተለያዩ ገጽታዎች በተለይም ከአካባቢው ቤተክርስቲያን ጋር በጤና አጠባበቅ፣ በትምህርት እና በወጣቶች ሙያዊ ሥልጠና መስክ ስላላት ትብብር ተብራርተዋል" ሲል ጉዳዩን የተከታተለው የቅድስት መንበር የፕሬስ ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በውይይቱ ወቅትም “በክልላዊ እና በዓለም አቀፍ ተፈጥሮ ላይ በተነሱ ጭብጦች ላይ የሐሳብ ልውውጥ ተደርጓል፣ ይህም በሕዝቦች መካከል ውይይት እና እርቅን የማስፋፋት አስፈላጊነትን ያጎላል” ሲል መግለጫው አክሎ ገልጿል።
31 Oct 2025, 09:12
