ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሮም ኮሎሲየም በሚገኘው የሳንትኤጂዲዮ አመታዊ የሰላም ስብሰባ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሮም ኮሎሲየም በሚገኘው የሳንትኤጂዲዮ አመታዊ የሰላም ስብሰባ ላይ   (@Vatican Media)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ‘ሰላም ቅዱስ ነው፣ ጦርነት ደግሞ ክፉ ነው" ማለታቸው ተገለጸ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሮም ኮሎሲየም በሚገኘው የሳንትኤጂዲዮ አመታዊ የሰላም ስብሰባ ላይ ከተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች ጋር ተገናኝተው የተነጋገሩ ሲሆን ጦርነት እንዲቆም፣ ለእርቅ እና ለጸሎት አዲስ ቁርጠኝነት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በሳንትጂጊዲዮ ማህበር የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የሰላም ስብሰባ፡ ሃይማኖቶች እና ባህሎች በውይይት መዝጊያ ላይ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ማክሰኞ ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም ምሽት በሮም ኮሎሲየም የዓለም የተለያዩ  የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችን ለሰላም የጸሎት ዝግጅት ላይ ነበር ቅዱስነታቸው ይህንን የተናገሩት።

በክርስቲያን፣ በአይሁድ፣ በሙስሊም፣ በቡዲስት፣ በሂንዱ እና በሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ፊት ባቀረቡት ንግግር፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሁሉም ሕዝቦች መካከል የእርቅ፣ የውይይት እና የወንድማማችነት ጥሪ አቅረበዋል።

“እንደተለያዩ ሃይማኖታዊ ወጎቻችን መሰረት ለሰላም ጸልየናል” ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፣ “አሁንም የእርቅ መልእክት ለማወጅ ተሰብስበናል። ግጭቶች በሁሉም የሕይወት ክፍሎች ይገኛሉ፣ ነገር ግን ጦርነት እነሱን ለመቋቋም ወይም መፍትሄ ለማግኘት ምንም እገዛ የለውም። ሰላም የማያቋርጥ የእርቅ ጉዞ ነው” ሲሉ መናገራቸው ተገልጿል።

“ሰላምን የተጠማ” ዓለም

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጦርነትና በመፈናቀል በተበታተነ ዓለም ውስጥ የአንድነት አጣዳፊ አስፈላጊነትን በማስተጋባት፣ “የሥልጣን አላግባብ መጠቀምን፣ የኃይል መግለጫዎችን እና ለሕግ የበላይነት ግድየለሽነትን” አውግዘዋል፣ እና “እውነተኛ እና ጤናማ የእርቅ ዘመን” እንዲመጣ ጥሪ አቅርበዋል።

“ጦርነትን በቃ ልንል ይገባል"  ሲሉ በአጽኖት የተናገሩት ቅዱስነታቸው “በሞት፣ በመጥፋት እና በግዞት ምክንያት በሚደርሰው ሥቃይ ሁሉ! ዛሬ እዚህ ተሰብስበን ለሰላም ያለንን ጽኑ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ጸሎት ለእርቅ ኃይለኛ ኃይል መሆኑን ያለንን እምነትም ጭምር እንገልጻለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሃይማኖትን አላግባብ መጠቀምን በተመለከተ “ጸሎት ሳያደርጉ ሃይማኖትን የሚከተሉ ሰዎች እስከ መግደል ድረስ አላግባብ የመጠቀም አደጋ አለባቸው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። እውነተኛ ጸሎት “የልብ መክፈቻ ነው” ብለዋል፣ “የታሪክን መንገድ የሚቀይር” እና የአምልኮ ቦታዎችን ወደ “የመገናኛ ድንኳኖች፣ የእርቅ መቅደሶች እና የሰላም ምሽጎች” የሚቀይር እንቅስቃሴ ነው ብለዋል።

በአዚዚ መንፈስ

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.አ.አ በ1986 በአዚዚ ታሪካዊው በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መካከል የተደረገውን ስብሰባ ለአራት አስርት ዓመታት ያህል በማስታወስ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ “የአዚዚው መንፈስ” በአማኞች መካከል ውይይትንና ጓደኝነትን ማነሳሳቱን ቀጥሏል ብለዋል።

የቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበረሰብን እና “ይህንን መንፈስ ሕያው አድርገው፣ ከማዕበሉ ጋር እንኳን ሳይጋጩ በርካታ መልካም ተግባራትን የምያከናውኑ” ብዙ ድርጅቶች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፣ እናም ሁሉም ሃይማኖቶች “ለዘመናዊው የሰው ልጅ እጅግ ብዙ የጥንት መንፈሳዊ ሀብቶችን እንዲያቀርቡ” አሳስበዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በተጨማሪም ስብሰባው "ከኖስትራ አኤቴት" 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል ጋር የተገጣጠመ መሆኑን አስታውሰዋል፣ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ቤተክርስቲያን ከክርስቲያን ካልሆኑ ሃይማኖቶች ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ።

“ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን በአዚዚ መንፈስ የሚደረግ ጸሎት የተመሠረተው "በኖስትራ አኤቴት" ጠንካራ መሠረት ላይ ነው፣ የጉባኤው ጥሪ ቃላት በመጥቀስ፣ “ማንኛውንም ሰው እንደ እህቶችና ወንድሞች አድርገን ብናያቸው የሁሉ አባት ወደ ሆነው እግዚአብሔር በእውነት መጸለይ አንችልም፣ ምክንያቱም ሁሉም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ናቸው” ሲሉ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰንድ ጠቅሰዋል።

ሰላም ቅዱስ ነው

የቀድሞ ርዕሰ ሊቀ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በ2024 ዓ.ም በቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር የፓሪስ ስብሰባ ላይ የላኩትን መልእክት በማስታወስ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሃይማኖትን መሳሪያነት በመቃወም የቀደመውን አቤቱታ ደግመውታል፡-

“ጦርነት እየተባባሰ ይሄዳል። እግዚአብሔርን በጦርነት ውስጥ ወገንተኝነትን ለማስፋፋት ለሚሞክሩ ወዮላቸው” ሲሉ መናግራቸውን አስታውሰዋል።

“እነዚህን ቃላት የራሴ ማድረግ እፈልጋለሁ” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ተናግረዋል። “ጦርነት ፈጽሞ ቅዱስ ሊሆን በፍጹም አይችልም፣ ሰላም ብቻ ቅዱስ ነው፣ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚፈጸም ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በእግዚአብሔር ፊት የተሰጠ ግዴታ

የፖለቲካ መሪዎች ለሰላም ያላቸውን ኃላፊነት እንዲሸከሙ ጥሪ ሲያቀርቡ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “በእግዚአብሔር ፊት ከባድ ግዴታ ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

“ሰላም የሁሉም ፖለቲካ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። እግዚአብሔር ሰላምን ለመፈለግ ያልቻሉትን ወይም ውጥረትንና ግጭትን ያስነሱትን ሰዎች ተጠያቂ ያደርጋል። ለጦርነት ቀናት፣ ወራትና ዓመታት ተጠያቂ ያደርጋቸዋል” ሲሉ ተናግረዋ።

ሰላምን ለማረጋገጥ ድፍረት ያስፈልጋል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የሰላም ምስክር” ብለው የገለጿቸውን የተከበረውን ጆርጂዮ ላ ፒራ ቃላት በማስተጋባት፣ የሰው ልጅ “የድርድር ዘመንን፣ ጦርነት የሌለበት አዲስ ዓለም ዘመንን” እንዲቀበል አሳስበዋል።

 

የእያንዳንዱ እምነት ተከታዮች “የአቅም ማጣት ዓለም አቀፋዊነት” ብለው የጠሩትን ነገር በውይይት፣ በትብብር እና በጋራ ኃላፊነት እንዲያሸንፉ አበረታተዋል።

አክለውም “ዓለም ለዚህ ጥሪ ጆሮውን ቢያዞርም፣ እግዚአብሔር ጸሎታችንን እና የብዙዎችን መከራ የሚቀበሉትን ጩኸት እንደሚሰማ እርግጠኞች ነን። እግዚአብሔር ጦርነት የሌለበት ዓለም ይፈልጋል። ከክፋት ያወጣናልና” ሲሉ ከተናገሩ በኋላ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

29 Oct 2025, 09:39