ፈልግ

ቅዱስነታቸው ካካስቴል ጋንዶልፎ ወደ ቫቲካን ከመመለሳቸው በፊት ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርገዋል ቅዱስነታቸው ካካስቴል ጋንዶልፎ ወደ ቫቲካን ከመመለሳቸው በፊት ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርገዋል   (@VaticanNews)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ ትራምፕ ለጋዛ ሰላም ያቀረቡትን እቅድ ሐማስ እንደሚቀበል ያላቸውን ተስፋ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በጋዛ የሰላም እቅድ፣ ወደ ጋዛ የባሕር ዳርቻ እየተቃረበ በሚገኝ የዕርዳታ ቁሳቁስ፣ የአሜሪካ የኒውክሌር ውይይቶች አሳሳቢነት፣ በቅድስት መንበር የገንዘብ አያያዝ ላይ የቫቲካን ችሎት እና በካርዲናል ኩፒች ዙሪያ በተነሱ ውዝግቦች ላይ አጭር አስተያየት ሰጥተዋል። ቅዱስነታቸው አስተያየታቸውን በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሰጡት በካስቴል ጋንዶልፎ ከሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያቸው ማክሰኞ መስከረም 20/2018 ዓ. ም. ወደ ቫቲካን ከመመለሳቸው በፊት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደ ነበር ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ሕንጻ ውጭ የሚጠባበቋቸው ጋዜጠኞች የአሜሪካው ፕሬዚደንት ትራምፕ በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ይሁንታ በጋዛ ሰላምን ለመፍጠር በሚል ጥረት ለዋይት ሃውስ ያቀረቡትን ባለ 20 ነጥብ የሰላም እቅድ በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፥ የሐማስ መሪዎች የሰላም እቅዱን እንደሚቀበሉት ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ “እቅዱ እስካሁን ተጨባጭ ሃሳብ ያለው ይመስላል” ብለዋል። በተኩስ ማቆም እና ታጋቾችን በመልቀቅ አስፈላጊነት ላይ አጽንዖት የሰጡት ቅዱስነታቸው፥ እቅዱ አስደሳች ነገሮች እንዳሉት እና “የሐማስ መሪዎችም በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንደሚቀበሉት ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉም ተናግረዋል።

ለሰዎች ክብር መስጠት

ሰብዓዊ ዕርዳታን ለማቅረብ ወደ ጋዛ እየተቃረበ በሚገኘኝ መርከብ ላይ የቀጠለውን አስቸጋሪ ውጥረት በማስመልከት እንደገለጹት፥ “እውነተኛ ሰብዓዊ ዕርዳታን የመስጠት ፍላጎት አለ” ብለው፥ በዚህ ተግባር መካከል ምንም ዓይነት ሁከት እንደማይፈጠር እና ዕርዳታን በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙት ሰዎችም አክብሮት እንደሚሰጣቸው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ለሰላም አብሮ መሥራት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሰት የኒውክሌር ጦር መሥሪያ አጠቃቀምን ጨምሮ ለጦርነት ከተዘጋጁ ወታደራዊ መሪዎች ጋር የጠሩትን ስብሰባ በማስመልከት ሲናገሩ፥ “ይህ የንግግር መንገድ አሳሳቢ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ፕሬዚደንት ትራምፕ ዲፓርትመንቱን ከመከላከያነት ወደ ጦርነት ለመሰየም ያደረጉት ውሳኔ ‘ንግግር ብቻ ይሆናል’ ብለን ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጸዋል። በማከልም ውሳኔያቸው ኃይልን ተጠቅሞ ጫናን ለመፍጠር የተደረገ የአገዛዝ ዘይቤን የሚያሳይ እንደሆነ ጠቁመው፥ “ያም ሆኖ ጦርነት እንደማይኖር ተስፋ ስለምናደርግ ​​ለሰላም መሥራት አለብን” ብለዋል።

በቫቲካን የፍርድ ሂደት ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት የለም

የቅድስት መንበር የገንዘብ አያያዝን በሚመለከት በቫቲካን እየተካሄደ ስላለው የፍርድ ሂደት የተጠየቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሳይሰጡ ነገር ግን የፍርድ ሂደቱ መቀጠል እንዳለበት እና ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው በመግለጽ ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ ጉዳዩን ለዳኞች እና ለጠበቆች መተዋቸውን ተናግረዋል።

የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን መመልከት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የቺካጎ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች ሕጋዊ ውርጃን ለሚደግፉት ዲሞክራቲክ ሴናተር ዲክ ዱርቢን ሽልማት መስጠታቸውን በማስመልከት አስተያየታቸውን ሲሰጡ፥ ስለ ጉዳዩ ብዙም እንደማያውቁ ገልጸው፥ እርሳቸው እንደሚያስቡት “አንድ ሴናተር በዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት ውስጥ ለ 40 ዓመታት ያገለገለ ከሆነ ያከናወናቸውን አጠቃላይ ሥራዎች መመልከት በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ

ቅዱስነታቸው ችግሮች እና ውጥረቶች መኖራቸውን አምነው ነገር ግን “ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር የተያያዙ ብዙ ጉዳዮችን ማጤን አስፈላጊ ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል። የሞት ቅጣትን እየደገፉ “ፅንስ ማቋረጥን እቃወማለሁ” ማለቱ ሕይወትን መደገፍ እንዳልሆነ ወይም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በስደተኞች ላይ የሚደርሱ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን መደገፍ እንዳልሆነ አስምረውበታል።

“እነዚህ እጅግ የተወሳሰቡ ጉዳዮች ናቸው” ብለው፥ ማንም ሰው በእነዚህ ርዕሦች ላይ ሙሉ እውነት እንዳለው ባላውቅም ነገር ግን በመጀመሪያ ደረጃ መከባበር እንዲኖር፥ “እንደ አሜሪካዊ ዜጋ፣ የኢሊኖይ ግዛት ነዋሪዎች ወይም እንደ ካቶሊኮች አንድ ላይ እነዚህን የሥነ-ምግባር ጉዳዮችን በቅርበት መመልከት እና እንደ ቤተ ክርስቲያን አካሄድ መፍትሄን መፈለግ አለብን” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ከካስቴል ጋንዶልፎ ወደ ቫቲካን ተመልሰዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ወደ ካስቴል ጋንዶልፎ የሄዱት ሰኞ መስከረም 19/2018 ዓ. ም. ሲሆን ማክሰኞ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ተኩል ላይ ወደ ቫቲካን ከተመለሱ በኋላ በነጋታው ረቡዕ 21/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋድያን ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል አቅርበዋል። 

 

 

01 Oct 2025, 16:21