ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በሃይማኖቶች መካከል መተባበር ሊኖር እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለጥቅምት ወር እንዲሆን ያዘጋጁት ወርሃዊ የጸሎት ሃሳብ፥ “በልዩ ልዩ ሃይማኖቶች መካከል ትብብር እንዲኖር” የሚል እንደሆነ ተመልክቷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በዓለም አቀፉ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ በኩል ባስተላለፉት የጥቅምት ወር የቪዲዮ መልዕክት፥ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሃይማኖቶች መካከል መተባበርን ለማሳደግ መጸለይ እንደሚገባት አደራ ብለዋል።
የልዩ ልዩ ሃይማኖት ተከታይ ምዕመናን በኅብረት በሚያቀርቡት ጸሎት ሰላምን፣ ፍትህን እና ሰብዓዊ ወንድማማችነትን ማስፋፋት እንደሚችሉ ተገልጿል።
“ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ!” በማለት የሚጀምረው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የጸሎት ሃሳብ፥ “በልዩነት ውስጥ አንድ ሆነህ እያንዳንዱን ሰው በፍቅር የምትመለከት ጌታችን ሆይ! በኅብረት እንድንኖር፣ እንድንጸልይ፣ እንድንሠራ እና አብረን እንድናልም የተጠራን ወንድሞች እና እህቶች መሆናችንን ለመገንዘብ እርዳን” የሚል እንደሆነ ተነግሯል።
“ዓለማችን በውበት የተሞላች ብትሆንም በጥልቅ መለያየት ምክንያት የቆሰለች ናት” ሲሉ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “አንዳንድ ጊዜ ሃይማኖቶች ሕዝቡን አንድ ከማድረግ ይልቅ የግጭት መንስኤ ሲሆኑ ይታያሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
“ልባችንን የሚያነጻ መንፈስህን ስጠን!” በማለት በጸሎት የጠየቁት ቅዱስነታቸው፥ አንድ የሚያደርገንን ለይተን በማወቅ እና ይህን ሳናጠፋው መደማመጥን እና መተባበርን እንደገና መማር እንደሚገባ ተማጽነዋል።
“በሃይማኖቶች ውስጥ የሚታዩት ተጨባጭ የሰላም፣ የፍትህ እና የወንድማማችነት ምሳሌዎች ከልዩነታችን ባለፈ በጋራ መኖር እና መሥራት እንደሚቻል ማመንን እንዲያበረታታ” በማለት ጸሎት አቅርበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ወርሃዊ የጸሎት ሃሳባቸውን ሲያጠቃልሉ፥ “ሃይማኖቶች የጦር መሣሪያ ወይም የልዩነት ግድግዳ ከመሆን ይልቅ እንደ ድልድይ እና ትንቢት፥ መልካም የጋራ ህልም፣ ሕይወትን በመንከባከብ፣ ተስፋን በማስጠበቅ እና በተበታተነ ዓለም የአንድነት እርሾ ይሆኑ ዘንድ” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወርሃዊ የቪዲዮ መልዕክት
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ ይፋዊ ተነሳሽነት ዓላማ፥ የቅዱስነታቸውን ወርሃዊ የጸሎት ሃሳቦችን በዓለም ዙሪያ የማሰራጨት የጸሎት ሐዋርያነት እንደ ሆነ ይታወቃል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2016 ዓ. ም. ጀምሮ ሲቀርብ የቆየው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳት የቪዲዮ መልዕክት፥ በሁሉም የቫቲካን ማኅበራዊ አውታረ መረቦች ከ 247 ሚሊዮን በላይ ዕይታዎች ያሉትን እና ከ 23 በላይ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በ 114 አገሮች ውስጥ ሽፋን እንደሚያገኝ ታውቋል።
የቪዲዮ መልዕክቱ የሚዘጋጀው፥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቪዲዮ ጸሎት አውታረ-መረብ ቡድን ሲሆን፥ በአንድሬያ ሳሩቢ አስተባባሪነት እና በ “ኮሮኔሽን ሚዲያ” ረዳትነት ተሰርቶ በላ ማኪ ኤጀንሲ እና በቫቲካን ሚዲያ ትብብር የሚሰራጭ መሆኑ ታውቋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት አውታረ-መረብ ጳጳሳዊ ማኅበር ሲሆን፥ ካቶሊካዊ ምዕመናንን በጸሎት እና በተግባር በማሰባሰብ ለሰው ልጅ እና ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምላሽ የመስጠት ተልዕኮ ያለው እንደሆነ ይታወቃል።
