ፈልግ

በሱዳን የምታየው ሰብዓዊ ቀውስ በሱዳን የምታየው ሰብዓዊ ቀውስ   (AFP or licensors)

ር.ሊ.ጳ ሊዮ በሱዳን የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና የሰብአዊ ዕርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ጥሪ አቀረቡ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሱዳን አስቸኳይ የተኩስ አቁም እና የሰብአዊ መተላለፊያ ኮሪደሮች ክፍት እንዲደረጉ ጥሪ አቅርበዋል፣ ዓለም አቀፍ እርምጃ እንዲወሰድ እና ለተጎጂዎች ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በወቅቱ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካደረጉ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ከምርጫ በኋላ በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት የዳረጉትን በታንዛኒያ ሰላም እና ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሁድ ዕለት ጥቅምት 22/2018 ዓ.ም  እንደተናገሩት በጦርነት በተጎዳችው ሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ ገብነት እና የሰብአዊ መተላለፊያዎች እንዲከፈቱ እና የእርዳታ አቅርቦት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

“በታላቅ ሀዘን፣ ከሱዳን የሚመጣውን አሳዛኝ ዜና እየተከታተልኩ ነው፣ በተለይም በሰሜናዊ ዳርፉር ክልል ውስጥ ከምትገኘው ኤል ፋሸር ከተማ” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ተናግረዋል።

“በሴቶችና በህፃናት ላይ የሚደርሰው አድልዎ፣ ጥቃት፣ ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እና ለሰብአዊነት እርምጃ ከባድ እንቅፋቶች” “ለረጅም ወራት ግጭት ተዳክሞ ለነበረው ህዝብ ተቀባይነት የሌለውን ስቃይ እያደረሱ ነው” ሲሉ አውግዘዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሰሜን ዳርፉር ስለሚካሄደው ሁከት የተሰማቸው ስጋት እና በሰሜን ዳርፉር በኤል ፋሸር ከተማ ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት የጠቀሱት ንግግር የመጣው ሚሊሻዎች በሲቪሉ ህዝብ ላይ ከባድ ግፍ እየፈጸሙ እንደሆነ በሚነገርበት ከተማ ላይ ከበባ ከተደረገ በኋላ ነው።

ዳግመኛ ጥሪ

ምእመናን ለተጎጂዎች እንዲጸልዩ ጋብዘዋል፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው አካላት ግጭቶችን እንዲያቆሙ አሳስበዋል።

“ጌታ የሟቾችን ነፍስ እንዲቀበል፣ የሚሰቃዩትን እንዲደግፍ እና ተጠያቂ የሆኑትን ሰዎች ልብ እንዲነካ እንጸልይ” ብለዋል፣ እናም “በግጭቱ የተሳተፉት ወገኖች አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ እና የሰብአዊ ኮሪደሮች በፍጥነት እንዲከፈቱ አስቸኳይ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል።

በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “በቁርጠኝነትና በልግስና ጣልቃ እንዲገባ፣ እርዳታ እንዲሰጥና እርዳታ ለመስጠት ራሳቸውን ለሚያቀርቡት ድጋፍ እንዲሰጥ” ጥሪ አቅርበዋል።

በታንዛኒያ የተከሰተው አለመረጋጋት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ትኩረታቸውን ወደ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ታንዛኒያ ሀገር በማዞር፣ ምርጫን ተከትሎ በአገሪቱ ውስጥ ስለተከሰቱት የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ክስተቶች ጠቅሰዋል። “በቅርቡ የፖለቲካ ምርጫ ከተደረገ በኋላ ብዙ ሰዎችን ተጎጂ ያደረጉ ጥቃቶች እና ግጭቶች በተከሰቱባት ታንዛኒያም ሰላም ይሰፍን ዘንድ እንጸልይ” ብለዋል። ተሳታፊዎቹ ሁሉ “ከሁሉም ዓይነት ዓመፅ እንዲቆጠቡ እና የውይይት መንገድን እንዲከተሉ” ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት በታንዛኒያ የተካሄደው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዋና ተቀናቃኝ እጩዎች ከውድድሩ ከተገለሉ እና ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሁሉ ሀሰን 98 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸናፊ እንደሆኑ ከተገለጸ በኋላ ለሦስት ቀናት የቆየ ኃይለኛ ተቃውሞ አስነስቷል። ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ በተደረጉት ተቃውሞዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። ተቃዋሚዎቹ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

03 Nov 2025, 15:30