ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎትን በመሩበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎትን በመሩበት ወቅት  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሙታንን ማስታወስ ተስፋን እንደሚያመጣ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ እሑድ ጥቅምት 23/2018 ዓ. ም. የተከበረውን የቅዱሳን መታሰቢያ በዓልን በማስመልከት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት በርካታ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን የአገር ጎብኚዎች ቃለ-ምዕዳናቸውን አሰምተዋል። በዕለቱ ከመሩት የእኩለ ቀን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀደም ብሎ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳናቸው፥ ትንሣኤን እና ሙታንን የማስታወስ አስፈላጊነትን አስረድተዋል።

ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ከዚህ ቀጥሎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! በዚህ የኅዳር ወር የመጀመሪያ ቀናት (እ.አ.አ) የተሰቀለው የኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መነሣት ለእያንዳንዳችን መንፈሳዊ ጉዞ ብርሃን ሆኖናል። ምክንያቱም 'የላከኝ የአብ ፈቃድም ይህ ነው፤ ከሰጠኝ ሁሉ አንድም እንኳን እንዳላጠፋ፥ ይልቁንም በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው ነው' ብሎናልና (ዮሐ. 6:39)። ስለዚህ የእግዚአብሔር አሳቢነት ማንም ለዘላለም እንዳይጠፋ፣ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ቦታ እንዲኖረው እና ልዩ ውበቱን እንዲያሳይ ስለሆነ የሚሰጠው ትኩረት ግልጽ ነው።

ቅዳሜ ዕለት ያከበርነው የሁሉ ቅዱሳን በዓል ምስጢርም ይህ ነው። ልዩነቶች የእግዚአብሔርን ሕይወት ለመጋራት የሚፈልጉ ሰዎች ኅብረት የሚያሰፋ ነው። ይህም በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ የተጻፈ፥ እውቅናን፣ ትኩረትን እና ደስታን የመፈለግ ጉጉት ነው። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ እንዳብራሩት፥ 'የዘላለም ሕይወት' የሚለው አገላለጽ ለዚህ ለማይታበል ተስፋ ትርጉምን ይሰጣል።“የዘላለም ሕይወት” የጊዜ ቅደም ተከተል ሳይሆን ነገር ግን ፊት እና ኋላ በሌለው የፍቅር ውቅያኖስ ውስጥ መጠመቅ ነው። ይህ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ያለው የሕይወት እና የደስታ ሙላት በሕይወታችን ተስፋ የምናደርገው እና የምንጠብቀው ነው (“በተስፋ ድነናል” ሐዋርያዊ መልዕክት 'Spe Salvi' ቁ. 12)።

የዛሬው የሙታን መታሰቢያ በዓል ይህ ምስጢር ወደ እኛ የበለጠ ቅርብ እንዲሆን ያደርጋል። በእርግጥ ሞት ድምፅን፣ መልክን ወይም መላውን ዓለም ይዞ የሚሄድ በሚመስልበት በእያንዳንዱ ጊዜ የእግዚአብሔር አሳቢነት ማንም እንዳይጠፋ መሆኑን በልባችን እንረዳለን። እንደ እውነቱ ከሆነ እያንዳንዱ ሰው ሙሉ ዓለም ነው። እንግዲህ ጊዜው እጅግ ውድ ነገር ግን ደካማ የሆነውን የሰው ልጅ የማስታወስ ችሎታን የሚፈታተን ነው። የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት፣ ሞቱን እና ትንሣኤውን የማናስታውስ ከሆነ የዕለት ተዕለት ሕይወት እጅግ ግዙፍ ሃብትን የመረሳት አደጋ ይመጣል። ይሁን እንጂ በኢየሱስ ክርስቶስ አእምሮ ውስጥ ማንም ሰው የማያስታውሳቸው ወይም ታሪክ የረሳቸው የሚመስሉ ማለቂያ በሌለው ክብራቸው ዘወትር ይኖራሉ። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ ኢየሱስ አሁን የማዕዘን ድንጋይ ሆነ (የሐዋ. 4፡11)። የብርሃነ ትንሳኤው መልካም ዜናም ይህ ነው። በዚህ ምክንያት ክርስቲያኖች ሙታንን በእያንዳንዱ የቅዱስ ቁርባን ሥነ-ሥርዓት ላይ ዘወትር ያስታውሷቸዋል። ዛሬም ቢሆን የሚወዷቸውን ሰዎች በቅዱስ ቁርባን ጸሎት እንዲያስታውሷቸው ይጠየቃሉ። ይህ ጸሎት ማንም የማይጠፋ መሆኑን ተስፋ ይሰጠናል።

ጽሞና የሕይወትን ችኮላን ሲያስታግስ የመቃብር ሥፍራን መጎብኘት ሙታንን እንድናስታውስ እና በተስፋ እንድንጠብቅ ይጋብዘናል። በጸሎተ ሃይማኖት ውስጥ፥ 'በሙታን ትንሣኤ እና በሚመጣው ዓለም ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን' የሚለውን እናገኛለን። ባለፈው ነገር ወይም በናፍቆት ስሜት ተሞልተን በእንባ ሳንቆይ ስለ ወደፊቱን እናስብ። በአሁን ጊዜ መቃብር ውስጥ ተዘግተን አንቆይም። የተለመደው የኢየሱስ ክርስቶስ ድምፅ ወደ ሁላችን ዘንድ ይድረስ። ምክንያቱም ከወደፊት የሚመጣው ብቸኛው ድምጽ እርሱ ነውና። በስም ይጥራን፣ ቦታን ያዘጋጅልን፣ በሕይወት እንድንሸነፍ ከሚፈትነን የድህነት ስሜት ነፃ ያውጣን። የሕማማት ቅዳሜ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተስፋ ስለ ማድረግ እንደገና ታስተምረን።"

 

04 Nov 2025, 12:09