ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ሊዮ እኛ የፍጥረት ጠባቂዎች ነን እንጂ ለውድመቷ ተባባሪዎች አይደለንም ማለታቸው ተገለጸ።

COP30 (የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ኮንቬንሽን - UNFCCC - 30ኛው የፓርቲዎች ኮንፈረንስ) ከህዳር 01 እስከ ሕዳር 11/2018 ዓ.ም ደረስ በቤለም፣ ብራዚል እየተክካሄደ ያለ አመታዊ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ ነው።

የዚህ ዝግጅት ዛቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በብራዚል በCOP30 ላይ ለሚሳተፉት የዓለም ደቡብ ጳጳሳት እና ካርዲናሎች የቪዲዮ መልእክት መላካቸው የተገለጸ ሲሆን ትብብር መፍጠር እንደሚገባ አጥብቀው አሳስበዋል እና ከቃላት ይልቅ ተግባርን ከመረጥን ጊዜው እንዳልረፈደ እንገነዘባለን ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ገልጸዋል።

COP30 አብዛኛውን የውይይቱን ጊዜ ለዓለም አቀፉ ደቡብ አሳልፏል፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንም ከዚህ የተለየች አይደለችም፣ እስያ፣ አፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን በየራሳቸው ካርዲናሎች የተወከሉባቸው ስብሰባዎች እና ሲምፖዚየሞች አሏቸው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እንዲሁ ለዓለም አቀፉ ደቡብ ሕዝብ ያላቸውን ቅርበት አሳይተዋል፣ በCOP ውስጥ ለሚሳተፉት ጳጳሳት ሁሉ የቪዲዮ መልእክት ልከዋል።

በሕዳር 08/2018 ዓ.ም የሁለተኛው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጉባኤው ሊጠናቀቅ ሲል፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮም በቪዲዮ ምስል በላኩት መልእክት “የአማዞን ክልል ለአስቸኳይ እንክብካቤ የሚያስፈልገው የፍጥረት ሕያው ምልክት ሆኖ እንደሚኖር ለዓለም ሲናገሩ” ከነበሩት “ትንቢታዊ ድምፅ” ጋር ተቀላቅለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በአማዞን ሙዚየም ለተሰበሰቡት ጳጳሳት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ንግግር ሲያደርጉ “ተስፋንና ተግባርን ከመተው ይልቅ መጠንከር፣ አብሮ የሚሰራ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን መገንባት ይገባል” ብለዋል። በዚህ ረገድ እድገት እንዳለ ቢገነዘቡም፣ “በቂ አይደለም” እና “ተስፋና ቁርጠኝነት በቃላትና በምኞት ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ድርጊቶችም መታደስ አለባቸው” ብለዋል።

“ፍጥረት በጎርፍ፣ በድርቅ፣ በአውሎ ንፋስ እና በማያቋርጥ ሙቀት እየጮኸ ነው” ሲሉ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት የተናገሩት ቅዱስነታቸው “ከሶስት ሰዎች አንዱ በእነዚህ የአየር ንብረት ለውጦች ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ሆኖ ይኖራል” ብለዋል። ለእነሱ የአየር ንብረት ለውጥ የሩቅ ስጋት አይደለም፣ እና እነዚህን ሰዎች ችላ ማለት የጋራ ሰብአዊነታችንን መካድ ነው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የዓለም ሙቀት መጨመርን ከ1.5°ሴ በታች ለማቆየት አሁንም ጊዜ ቢኖርም፣ መስኮቱ እየተዘጋ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን “የእግዚአብሔር ፍጥረት መጋቢዎች እንደመሆናችን መጠን፣ በእምነትና በትንቢት በፍጥነት እንድንሰራ ተጠርተናል፣ እርሱ የሰጠንን ስጦታ ለመጠበቅ የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመቀጠል የፓሪስ ስምምነትም እውነተኛ እድገት እንዳሳየ አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን “ሰዎችንና ፕላኔቷን ለመጠበቅ በጣም ጠንካራ መሳሪያችን ነው” ሲሉ ገልጸውታል። ነገር ግን፣ እውነቱን መናገር አለብን፡- “ስምምነቱ የማይሳካ ሆኖ ያለ ሳይሆን በምንሰጠው በምላሻችን ላይ እየተሳሳትን ነው። የሚከሽፈው በአንዳንዶች የፖለቲካ ፍላጎት ነው። እውነተኛ አመራር ማለት አገልግሎት እና ለውጥ የሚያመጣ ሚዛን ያለው ድጋፍ ማለት ነው። ጠንካራ የአየር ንብረት እርምጃዎች ጠንካራ እና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ስርዓቶችን ይፈጥራሉ። ጠንካራ የአየር ንብረት እርምጃዎች እና ፖሊሲዎች - ሁለቱም ይበልጥ ፍትሃዊ እና የተረጋጋ ዓለም ውስጥ ኢንቨስትመንት ናቸው” ብለዋል።

መልዕክታቸውን ወደ ፍጻሜው በማምጣት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከእኛ ጋር የምንሄድባቸውን የእያንዳንዱ ሀገር እና የሃይማኖት አባቶች፣  ሳይንቲስቶች፣ መሪዎች እና የቤተክርስቲያን አባቶች ስራ አስታውሰዋል። እኛ የፍጥረት ጠባቂዎች ነን እንጂ ለውድመቷ ተባባሪዎች አይደለንም” ብለዋል።

እናም ይህንን በአእምሯቸው ይዘው፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በስብሰባ ላይ የተገኙት ሁሉ “ከፓሪስ ስምምነት ጀርባ እና ከአየር ንብረት ትብብር ጀርባ የማይናወጥ አንድነት” የሚል ግልጽ የሆነ ዓለም አቀፍ መልእክት እንዲልኩ ጠይቀዋል።

በመጨረሻም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ “ይህ የአማዞን ሙዚየም የሰው ልጅ ከመከፋፈል እና ከመካድ ይልቅ ትብብርን የሚመርጥበት ቦታ እንደሆነ ይታወስ” ብለዋል። የቪዲዮ መልእክቱን ተከትሎ፣ በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የዓለም አቀፍ ደቡብ ካርዲናሎች የዓሣ ማጥመጃ መረብ አቅርበዋል። መረቡ እ.አ.አ በ2019 ዓ.ም በፓን-አማዞን ክልል በተካሄደው ሲኖዶስ ወቅት ለቀድሞ ርሊቀ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተሰጠ የዓሳ ማጥመጃ ቅጂ ሲሆን ይህም በአማዞን ውስጥ በበርካታ የአገሬው ተወላጆች ማህበረሰቦች የተሸመነ ሲሆን ይህም የአንድነት እና የሰላም ምልክት ነው።

 

20 Nov 2025, 13:12