ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በኒቂያ ስለ ክርስቲያኖች አንድነት፥ በሊባኖስ ደግሞ ስለ ሰላም መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ሥፍራ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል። ቅዱስነታቸው በቱርክ እና በሊባኖስ የሚደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፥ ወደ እነዚህ አገራት የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በተስፋ እና በሰላም የተሞላ ጉብኝት መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዩክሬን እና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚደረገውን ጦርነትን ለማስቆም ውይይት እንዲደረግ አጥብቀው ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፥ በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለማስቆም የሚደረጉ ጥረቶችን ጨምሮ የሰዎች አስተሳሰብ ለወጣቶች ከሚሰጥ ትምህርት ጀምሮ መለወጥ እንዳለበት አሳስበዋል።

“ሊባኖስን መጎብኘት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በቱርክ እና ሊባኖስ ከመጀመራቸው ከአርባ ስምንት ሰዓታት ቀደም ብሎ በካስቴል ጋንዶልፎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያቸው ተገኝተው በሥፍራው ለነበሩት ጋዜጠኞች እና ምእመናን ሰላምታ ከሰጡ በኋላ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

ቅዱስነታቸው በሁለቱ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የሚያደረጉት የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት የኒቂያ ጉባኤ 1,700ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓልን የሚያካትት መሆኑን ገልጸዋል።

በሁለቱ አገራት ውስጥ የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች በተለይ በዚህ የኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት ተስፋን እና ሰላምን የሚመለከቱ እንደሚሆኑ ገልጸው፥ ለሁለቱም አገሮች ሕዝቦች ሰላምታን ለማቅረብ በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲሊ ተናግረዋል። 

ከቀናት በፊት በእምነት የመተባበር አስፈላጊነትን በትክክል የሚገልጽ ሐዋርያዊ ሠነድ ማሳተማቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ይህ ለመላው ዓለም የሰላም ምንጭ ሊሆን ስለሚችል መመስከር አለብን” ብለዋል። ከቁስጥንጥንያ አብያተ ክርስቲያናት ፓትርያርክ ከብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ጋር ያደረጉትን ስብሰባ በማስታወስ፥ በክርስቲያኖች መካከል አንድነትን ለማስተዋወቅ ልዩ አጋጣሚ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የጦር መሣሪያዎች መልስ ሊሆኑ አይችሉም!

እስራኤል በቤሩት የሄዝቦላ ሠፈሮች ላይ የፈፀመችውን የቦምብ ጥቃት በማስመልከት ሲናገሩ፥ ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረው፥ ሁሉም ሰው ችግሮችን ለመፍታት የጦር መሣሪያዎችን መጠቀምን እንዲተው ጥሪ አቅርበዋል። ሁለቱም እርስ በርስ በመከባበር አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በመወያየት ለችግሮች መፍትሄን ለማግኘት አብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

“ሁሉም ሰው ሰላምን እንዲፈልግ ማበረታታት አለብን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እስራኤልን እና ሄዝቦላህን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ ብዙውን ጊዜ ዓመፅ የሚከሰተው በፍትህ መጓደል ምክንያት በመሆኑ ፍትህን እንዲፈልጉ እና ለበለጠ አንድነት፣ ለሁሉም ሰዎች እና ሃይማኖቶች ክብር ሲባል አብረው መሥራት አለባቸው” ብለዋል።

በዩክሬን ውስጥ ሰዎች አሁንም እየሞቱ ነው

ለሦስት ዓመታት በጦርነት ውስጥ የምትገኘውን ዩክሬን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡት የሰላም እቅድ የሚያመጣውን ውጤት መጠበቅ አለብን” ብለዋል።

ሁለቱ ባላንጣዎች ወደ ስምምነት እየተቃረቡ በመሆናቸው እግዚአብሔርን አመስግነው፥ በውይይቱ ሂደት የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም ነገር ግን ብዙዎች እየሞቱ ስለሆነ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ አደራ ብለው ውይይትን ወደ መፍትሄ የሚያመራ መንገድ አድርገው እንዲቀበሉት አበረታተዋል።

አዲስ አስተሳሰብን ማስረጽ

በዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት ወጣቶችን በማስተማር መጀመር እንዳለበት አሳስበዋል። “እያንዳንዱ ሰው ሊከበር ይገባል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ብዙውን ጊዜ ወጣቶችን የሚጎዳ ዓመፅ እንዲቆም እና አዲስ አስተሳሰብ እንዲፈጠር ጥሪ አቅርበው፥ “ለሁሉም ሰው መልካምን የምንመኝ የሰላም ሰዎች መሆን አለብን” ብለዋል።

ለእግዚአብሔር ምስጋናን ማቅረብ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በማጠቃለያቸው፥ በአሜሪካ ውስጥ የሚከበረውን የምስጋና ቀን በማስመልከት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ “በተለይም በአሜሪካ ውስጥ ባለን በዚህ አስደናቂ በዓል የተለያየ እምነት ያላቸውን ሰዎች ምናልባትም የእምነት ስጦታ የሌላቸውን ሰዎች ጨምሮ ሁሉንም ሰው አንድ የሚያደርግ ከሁሉም በላይ የሕይወት፣ የእምነት እና የአንድነት ስጦታዎችን መቀበላቸውን እንዲገነዘቡ፥ ሰላምን እና ስምምነትን እንዲያሳድጉ፣ ለተሰጣቸው ስጦታዎች በሙሉ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ አበታተዋል።

 

26 Nov 2025, 16:12