ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቱርክ የወንድማማችነት እና የሰላም ድልድዮችን እንገንባ ማለታቸው ተገልጸ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
በመጀመሪያው ቀን ሐዋርያዊ ጉዞአቸው፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአንካራ ለሚገኙ ባለስልጣናት ንግግር በማድረግ፣ ቱርክ በባህሎች፣ በእምነት እና በአህጉራት መካከል እንደ ድልድይ መሆኗን እንድትቀበል እና የዓለም መለያየትን እንድትቃወም እና የውይይት መንገድ እንድትከተል ጥሪ አቅርበዋል።
ጉዞው ከኢስታንቡል ወደ ኢዝኒክ ይወስዳቸዋል፤ ቤተክርስቲያኗ የኒቂያ የመጀመሪያዋ የክርስቲያኖች ሕብረት ጉባኤ የተካሄደበት 1,700ኛ የመታሰቢያ ዓመት ክብረ በዓልን ታከብራለች፤ ከዚያም እሁድ ህዳር 21/2018 ዓ.ም ቅዱስ አባታችን ወደ ሊባኖስ ይጓዛሉ።
በሕዳር 18/2018 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሐዋርያዊ ጉዞዋቸውን በቀጠሉበት ወቅት በቱርክ ፕሬዝዳንት ቤተ መንግሥት እና ከዚያም ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ጉብኝት በማድረግ የጀመሩ ሲሆን የአገሪቷን ባለሥልጣናት፣ የሲቪል ማህበረሰብ እና የዲፕሎማሲ ልዑኮች አባላት የቅዱስነታቸውን ንግግር የመጀመሪያ ቃላትን ለመስማት ተሰብስበው ነበር።
“ሰብአዊነትን ወደ ወንድማማችነት የምትጠራ ምድር”
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን ንግግር ሲያደርጉ፣ ለተደረገላቸው ሞቅ ያለ አቀባበል ምስጋናቸውን ገልጸዋል። ቱርክ “ከክርስትና አመጣጥ ጋር በማይነጣጠል መልኩ የተገናኘች” ምድር እንደሆነች ቅዱስነታቸው በንግግራቸው ወቅት ገልጸዋል፣ እንዲሁም የአብርሃምን ልጆች ሁሉ - ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች እና አይሁዶች - ልዩነትን እንደ መከፋፈል ሳይሆን ወደ ወንድማማችነት ጎዳና የሚወስድ መንገድ መሆኑን እንዲገነዘቡ የመረጣት ምድር እንደሆነች ተናግረዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስለ አገሪቱ የተፈጥሮ ውበት እና የበለፀገ የባህል ልዩነት አፅንኦት ሰጥተው ሲናገሩ የሰው ልጅ ሥልጣኔ ትውልዶች፣ ሀሳቦች እና ወጎች በሚገናኙበት ቦታ እንደሚበቅል የሚያስታውሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንዲህ ዓይነቱ ልዩነት ስጋት ሳይሆን የማኅበራዊ ሕይወት ጥበቃ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩት ቅዱስነታቸው “አንድነት ድህንነት ይሆናል” ድልድዮች - እውነተኛ እና ምሳሌያዊ - እውነተኛ የሲቪል ማህበረሰብን የሚደግፉ ናቸው ብለዋል።
ድልድይ እንደ ቱርኪዬ የሙያ ምልክት
ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ሐዋርያዊ ጉዞ የተመረጠው አርማ በዳርዳኔልስ የባህር ወሽመጥ ላይ ያለውን ድልድይ ያሳያል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳሉት የቱርክ ልዩ ማንነት ምልክት ነው፡ እስያን ከአውሮፓ ጋር በአካል የምታገኛኝ ሀገር፣ ነገር ግን የበለጠ በጥልቀት፣ እራሷን ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከወግ ወደ ዘመናዊነት፣ ከልዩነት ወደ አንድነት የምታገኛኝ ሀገር መሆኗን በንግግራቸው ገልጸዋል።
በሁለት ዋልታዎች (ፖላራይዜሽን) እና በጽንፈኛ አቋም በተጨናነቀ ዓለም ውስጥ፣ ማህበረሰቦች የመበታተን አደጋ ላይ እንደሚወድቁ አስጠንቅቀዋል። ሆኖም በቱርክ የሚኖሩ ክርስቲያኖች፣ በአንድ ወቅት እዚህ ያገለገሉትን እና የካቶሊኮች መገለልን እንዲቃወሙ እና “የመገናኘት ባህልን” እንዲቀበሉ ያሳሰቡትን የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ጥረት በመግለጽ፣ የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ፍቅርን አስታውሰዋል። እነዚህ ቃላት፣ ቅዱስ አባታችን እንዳመለከቱት፣ ዛሬም ድረስ ጠቃሚ ሆነው ቀጥለዋል ብለዋል።
“እግዚአብሔር በሰማይና በምድር መካከል ድልድይ ሠራ”
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የእግዚአብሔርን የወንጌል ምስል እንደ ድልድይ ገንቢ አድርገው የገለጹ ሲሆን እግዚአብሔር ራሱን በመግለጥ፣ ልቦች ርህራሄውን እንዲያንጸባርቁ በሰማይና በምድር መካከል መተላለፊያን የፈጠረ አምላክ ነው ብለዋል።
ፍትህና ምሕረት፣ የበላይነትን አመክንዮ መቃወም አለባቸው፣ ሲሉ አጥብቀው የተናገሩት ቅዱስነታቸው ርህራሄ እና አንድነት - ኃይል ሳይሆን - እውነተኛ የእድገት መለኪያዎች መሆን አለባቸው ብለዋል።
ከሥነ ምግባር የተነጠለ የቴክኖሎጂ እድገት አደጋዎችን እንደምያስከትል አስጠንቅቀዋል፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውልኾት) እንኳን በመጨረሻ የሰውን ምርጫዎች እንደሚያጎላ ለአድማጮቹ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል። “ሂደቶች የማሽኖች ሥራ አይደሉም፣ የሰው ልጅ ራሱ” ሲሉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው መሪዎች “በሰው ልጅ ቤተሰባችን አንድነት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን” አብረው እንዲሠሩ አሳስበዋል።
ቤተሰብ በቱርክ ማህበረሰብ ልብ ውስጥ
በርካታ ቱርኮች ልብ ውስጥ ወደሚገኘው ጭብጥ ሐሳባቸውን በማዞር ቅዱስነታቸው እንደተናገሩት ከሆነ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ስለ ቤተሰብ “የማህበራዊ ህይወት የመጀመሪያ ማዕከል” ሲሉ ተናግረዋል፣ እያንዳንዱ ሰው “ያለሌላኛው፣ እኔ የለሁም” የሚለውን መሠረታዊ እውነት የሚማርበት ቦታ እንደ ሆነ ገልጸዋል።
አገሪቱ የቤተሰብን ሚና ለማጠናከር የምታደርገውን ጥረት አክብረው፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ቤተሰብ ራሱን ካገለለ ወይም የራሱን አባላት ድምጽ ካዳፈነ የሚያጋጥሙትን አደጋዎች አምነዋል።
ደስታ፣ ከግለሰባዊነት ወይም የጋብቻ ትስስርን እና ለሕይወት ክፍትነትን ከማቃለል የመጣ አይደለም ብለዋል።
ብቸኝነትን ወደ ሸቀጥ የሚቀይሩ የሸማቾች ባህሎችን አስጠንቅቀዋል፣ በምትኩ “ፍቅርን እና የግል ግንኙነትን የሚያደንቅ ባህል” - የጋብቻ ፍቅር እና የሴቶች አስፈላጊ አስተዋጽኦ የሚከበርበት ባህል - ይህም ባህል ሴቶች፣ በስኮላርሺፕ፣ በሙያዊ ሕይወት፣ በሕዝብ አገልግሎት እና በባህላዊ አመራር አገሪቱን እያበለፀጉ መሆናቸውን እንዲረጋገጥ ያደርጋል ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።
ቱርክ የሰላም ምንጭ እንድትሆን ጥሪ አቅርቧል
ቅዱስ አባታችን ቱርክ “በሕዝቦች መካከል የመረጋጋትና የመቀራረብ ምንጭ” ሆኗ ማገልገሏን እንደምትቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፤ ይህም የርዕሰ ሊቀ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ፣ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዩሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ እና የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን በማስታወስ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የርሳቸው ጉብኝት፣ የጥንት ክርስቲያኖች የእምነት አንድነትን ለመፈለግ በተገናኙበት ከኒቂያ በዓል ላይ የተሳሰረ ሲሆን፣ ለንግግርና ለመተዋወቅ ዘላለማዊ አስፈላጊነትን ይናገራል።
ዓለም እንደገና በተባባሰ ግጭት በምትታወቅበት ወቅት፣ የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሦስተኛው የዓለም ጦርነት የተካሄደ ይገኛል" ብለው የጠሩትን ነገር አስጠንቅቀዋል።
አገራት ረሃብን በመዋጋት፣ ፍጥረትን በመጠበቅ እና ለሁሉም ትምህርትና ጤናን በማስጠበቅ የጋራ ተግዳሮቶች ላይ ሳይሆን ኃይላቸውን በአጥፊ ተለዋዋጭነት ላይ እያዋሉ ነው ብለዋል።
በእውነትና በወዳጅነት አብረን መጓዝ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ “መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ጥንካሬውን ብቻ” ይዞ አልመጡም፣ ነገር ግን ለእያንዳንዱ ሰው ሁለንተናዊ እድገት ቁርጠኛ ከሆኑ ሁሉም አገራት ጋር አብሮ ለመስራት ጽኑ ፍላጎት አላቸው።
“በእውነትና በወዳጅነት እንጓዝ” ሲሉ ደምድመዋል፣ “በእግዚአብሔር እርዳታ በትህትና እንታመን” ሲሉም አክለው ገልጸዋል።
ሁለቱ መሪዎች በፕሬዚዳንቱ ቢሮ ውስጥ የግል ግንኙነት ካደረጉ በኋላ፣ ከባለስልጣናት፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲያዊ የልዑካን አባላት ጋር ለመገናኘት ወደ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት አመሩ።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ንግግር የተለያዩ ማህበረሰቦችን አንድ ለማድረግ "ድልድይ" በመሆን የቱርክ ሚና፣ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ቤተሰቦች አስፈላጊነት እና "የመገናኘት ባህልን" በመደገፍ "የግዴለሽነት ዓለም አቀፋዊነትን" አለመቀበል አስፈላጊነትን አጉልቶ አሳይቷል።
የጳጳሱ የመጨረሻ ይፋዊ ጉብኝት በቱርክ የሃይማኖት ጉዳዮች ፕሬዝዳንት፣ ዲያኔት ከሆኑት የሱኒ እስልምናን ትምህርት እና ልምምድ የሚያስተዋውቀው የመንግስት ተቋም - ከዲያኔት ፕሬዝዳንት ሳፊ አርፓጉሽ ጋር በግል ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ምንም እንኳን የቱርክ ሪፐብሊክ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥታዊ የሆነ እምነት በይፋ የምትከተል አገር ባትሆንም ከ99% በላይ የሚሆነው ህዝብ የሙስሊም እምነት ተከታይ ነው።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የመጀመሪያውን ቀን በቱርክ በቫቲካን ኤምባሲ ከሚሰሩ ሠራተኞች ጋር ለአጭር ጊዜ ከተገናኙ በኋላ እና መልካም ቆይታ በማሳለፍ አጠናቀዋል፤ ከዚያም ወደ ኢስታንቡል አጭር በረራ ለማድርገ ወደ አየር ማረፊያው መመለሳቸው ተዘግቧል።
የቅዱስ አባታችን ሐዋርያዊ ጉዞ አርብ ዕለት ሕዳር 19/2018 በኢስታንቡል የመንፈስ ቅዱስ ካቴድራል ውስጥ ከሚገኙ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ገድማዊያን/ዊያት እና የሐዋርያዊ አገልግሎት ከሚሰጡ ሰዎች ጋር ለጸሎት ይገናኛሉ፤ ከዚያም በድሆች ታናናሽ እህቶች በሚተዳደረው ለአረጋውያን ልዩ የእንክብካቤ ተቋም ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተዘግቧል።
አርብ ሕዳር 19/2018 ከሰዓት በኋላ የሊቀ ጳጳሳቱ ጉብኝት ዋና ዋና ነገሮች አንዱ ሲሆን ይህም በቤተክርስቲያኗ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውን የቅዱስ አባቶች የሐይማኖት ሕብረት ጉባኤ የነበረውን የኒቂያ ጉባኤ 1,700ኛ የመታሰቢያ ዓመት የምስረታ በዓል ለማክበር በኒቂያ የሚገኘው የቅዱስ አባቶች የጸሎት አገልግሎት ወደ ሚከናወንበት በድሮ መጠሪያዋ ኒቂያ በአሁናዊቷ ዘመናዊቷ ኢዝኒክ - ይሆናል።
