ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን ወጣቶች እምነታቸውን መዘንጋት እንደሌለባቸው አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው ለዓለም አቀፉ የወጣቶች አማካሪ ቡድን (IYAB) አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ወጣቶች መገለልን በማስወገድ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርበው ቤተ ክርስቲያን የተቸገሩትን እና በማኅበረሰቡ የተገፉትን ለመርዳት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ በሲኖዶሳዊነት፣ በወንጌል ተልዕኮ እና በተሳትፎ ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ካለው እና በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ የወጣቶችን አመለካከቶች ወደ ቅድስት መንበር ለማቅረብ ከሚፈልገው ዓለም አቀፍ የወጣቶች አማካሪ ቡድን (IYAB) አባላት ጋር ዓርብ ጥቅምት 21/2018 ዓ. ም. ተገናኝተዋል።
ከማክሰኞ ጥቅምት 18/2018 ዓ. ም. ጀምሮ በሮም የተሰበሰቡት የቡድኑ አባላት ወጣቶችን በሚመለከቱ ሦስት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ማለትም ሲኖዶሳዊነት፣ ተልዕኮ እና ተሳትፎ በሚሉ ጭብጦች ላይ ትኩረት በማድረግ ተወያይተዋል።
የወጣቶች አማካሪ ቡድን አባላት በልዩ ልዩ አገራት ውስጥ የሚገኙ በርካታ እኩዮቻቸውን እንደሚወክሉ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ወጣቶች በአማካሪ ቡድኑ በኩል ለቤተ ክርስቲያን መቆም እንደሚችሉ ድምፃቸው ተሰሚነትን እንዲያገኝ ለማድረግ የሚያደርጉት አስተዋፅዖ በዋጋ ሊተመን የማይችል መሆኑን ተናግረዋል።
“በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን፣ እምነታችሁን አትተውት!”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለወጣቶች አማካሪ ቡድን አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሲኖዳላዊት ቤተ ክርስቲያን በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ እና በዲጂታል ዘመን ወጣቶች እምነታቸውን እንዳይተው ልታበረታታ እንደሚችል አፅንዖት ሰጥተዋል።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ ብዙ ወጣቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ዝግጅቶች እና በታዋቂ የበይነ-መረብ ዝግቶች በኩል በሚሰጡ ክርስቲያናዊ ምስክርነቶች አማካኝነት ወደ እምነቱ መቅረባቸውን የተገነዘቡት ቅዱስነታቸው፥ ሆኖም ግን በበይነ-መረብ አማካይነት የሚገኝ እምነት በግለሰብ ልምዶች ብቻ የተወሰነ በመሆኑ እና ይህም አእምሮን እና ስሜትን ሊያረጋጋ ቢችልም ነገር ግን ወደ ልብ መዝለቅ የማይችል መሆኑን በማስጠንቀቅ፥ ከቤተ ክርስቲያን የአንድነት ሕይወት፣ ከእውነተኛ የእርስ በርስ ግንኙነቶች ወይም አብሮነት ጋር የማይጣጣም መሆኑን አስረድተዋል።
ብዙውን ጊዜ የማኅበራዊ ሚዲያ ስልተ ቀመሮች ለግለሰቦች ጥሩ አጋጣሚዎችን በመፍጠር የግል ፍላጎታቸውን ብቻ እንደሚመልስ ገልጸው፥ ቀልብን በሚስቡ ልዩ ልዩ ሃሳቦች የተሞሉ ቢሆንም ብዙ ሰዎችን ብቻቸውን በማስቀረት የዝንባሌዎቻቸው እስረኞች እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል። ለዚህ አደጋ መፍትሄው እንቅፋቶችን ለማሸነፍ እና ወጣቶች የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተሰብ ውጤታማ አባላት እንዲሆኑ የሚያበረታቱ የሲኖዶሳዊነት ኑሮ ልምዶች ሊሆኑ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
ቤተ ክርስቲያን የአቅመ ደካሞችን እና የድሆችን ድምፅ እንድትሰማ መርዳት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በሲኖዳላዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በእኩዮቻቸው አማካይነት በተለይም አቅመ ደካሞችን፣ ድሆችን፣ ብቸኛ የሆኑ ሰዎችን እና ስደተኞችን ከኅብረተሰቡ ጋር በማዋድ የትምህርት ዕድሎችን ለማግኘት የሚጥሩትን ለማገዝ መጠራታቸውን ጠቁመዋል።
“ሲኖዳላዊት ቤተ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ ለወጣቶች የሚናገረውን ማዳመጥ እና ልዩ የሆኑ ስጦታዎቻቸውን መቀበል” ትፈልጋለች ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል። ሲኖዶሳዊነት በቅድስት ሥላሴ አምሳል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለዘመናት ያህል የቋንቋ እና የትውልድ ሐረግ አንድነት እንዳላት ለማሳየት የሚረዳ መሆኑን ገልጸው፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትም በኅብረት የሚያድጉ እና መንፈሳዊ ስጦታዎቻቸውን የሚጋሩ መሆኑን አክለው አስረድተዋል።
አርቆ በማየት የፈጠራ እና የድፍረት መሪ መሆን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመቀጠልም፥ እውነተኛ ሲኖዶሳዊነት በመንፈስ ቅዱስ እንደሚመራ እና በዚህም ወደ ተልዕኮ እንደሚሰማራ ገልጸዋል። ስኖዶሳዊነት ስብሰባዎች የሚመሩበት ደንብ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስን በማዳመጥ ለእግዚአብሔር ሥራ ቦታ መስጠት መሆኑን በመናገር፥ መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜ እውነት ወደሆነው ወደ ኢየሱስ እንደሚመራ አክለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በዘመናት ሁሉ ወንጌልን ለሁሉ ሰው ማዳረስ የሚቻልበትን መንገድ ለማወቅ ወጣቶች የመንፈስ ቅዱስን አነሳሽነት እና የእያንዳንዱን ሰው ጥልቅ ምኞት ለማዳመጥ ዝግጁ እንዲሆኑ አበረታተዋል።
“ለሕይወት ትርጉም የሚሰጡ እውነተኛ መልሶችን ለማግኘት ነገሮችን በሚገባ መመልከት ያስፈልጋል” ሲሉ አፅንዖት የሰጡት ቅዱስነታቸው፥ “ለእግዚአብሔር ጥሪ ልባቸውን ክፍት ያደረጉ፣ በራስ እቅድ ብቻ የማይጠመዱ እና በሌሎች ላይ ከመፍረዱ በፊት ነገሮችን ለመረዳት እና ለመራራት ፈቃደኛ የሆነ ልብ ሊኖራቸው ይገባል” ብለዋል።
“በቤተ ክርስቲያን ሕይወት የመሳተፍ ፍላጎት የሚመጣው ከመንፈሳዊነት እንጂ ከአይዲዮሎጂ ወይም ከፖለቲካ አቋም አይደለም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የወጣቶች አማካሪ ቡድን አባላትን ለሥራቸው አመስግነው አገልግሎታቸው ለቤተ ክርስቲያን ሚስዮናዊነት አዲስ ጉልበት መሆኑንም አስታውሰዋል።
የወጣቶች አማካሪ ቡድን “IYAB” ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን እና መደበኛ የወጣቶች አገልግሎቶችን የሚያካትት ሰፊ መንፈሳዊ ንቅናቄ አካል መሆኑን ጠቁመው፥ “ይህም ቤተ ክርስቲያንን ሁልጊዜ አዲስ ያደርጋታል” ብለዋል።
የወጣቶች አማካሪ ቡድን ከሁሉም በላይ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ሕይወት እና ሁለንተናዊ ተልዕኮ እንዲሳተፉ ለማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተው፥“እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ተሳትፎ የሚገለጸው ለኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ቅርብ ከመሆን እና የሚጀምረውም ከመንፈሳዊነት እንጂ ከርዕዮተ ዓለም ወይም ከፖለቲካ አይደለም” ሲሉ አስረድተዋል።
የወጣቶች አማካሪ ቡድን አባላት የዘመናችን ወጣቶች ተስፋ፣ ሕልም እና ችግር በኢየሱስ ክርስቶስ ርኅራኄ እንዲመለከቱት እና ቤተ ክርስቲያን በእምነት እነሱን ማግኘት የምትችል መሆኗን እንዲገነዘቡ አሳስበዋል።
ስለ ሌሎች ሲሉ ስቃይን መቀበል
በወንጌል ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ባሻገር ወደ ሌሎችም ይመለከት እንደ ነበር ያሳታወሱት ቅዱስነታቸው፥ የመዳን፣ የእምነት አንድነት እና የጋራ ፍቅር መልዕክቱ ሩቅ ያሉትን እና ወደፊት የሚመጡትን ጨምሮ ለሁሉም ሰዎች ሊደርስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
“እግዚአብሔር ዘወትር ለመላው ዓለም ያስባል፣ የተሳትፎ ምንጭ ይህ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በዚህም ምክንያት ወጣቶች በጸሎት፣ በምስጢራት እና በዕለት ተዕለት ሕይወት የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጆች እንዲሆኑ ጋብዘው፥ ይህ ማለት ለሌሎች ሰዎች ስቃይ፣ ለፍላጎታቸው እና ለምኞታቸው መጨነቅ ማለት እንደሆነ በማስረዳት፥ “የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ተልዕኮ አካል የመሆን ፍላጎት እንዲፈጠር ያደርጋል” ሲሉ ተናግረዋል።
“ተሳትፎ የሰብዓዊነት እና የመንፈሳዊ ብስለት ምልክትም ነው” ሲሉ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ልጆች የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ የሚመለከቱ ቢሆኑም የጎለመሱ ሰዎች የሌሎችን ችግር እንዴት መጋራት እንደሚችሉ ያውቃሉ” ሲሉ ተናግረው፥ የወጣቶች አማካሪ ቡድን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ እንዲሆን አበረታትተዋል።
