ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በመሩበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በመሩበት ወቅት  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “እኛ ከክርስቶስ ጋር እንድንጓዝ የተፈጠርን የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ነን" ሲሉ አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ እሑድ ጥቅምት 30/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት በርካታ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን የአገር ጎብኚዎች ቃለ-ምዕዳን አሰምተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሳምንታዊውን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በመሩበት ወቅት ለምእመናን ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቤተ መቅደስ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ አስገንዝበዋል። “የመዳን ብቸኛው አስታራቂ እና ቤዛ፣ ራሱን ከሰውነታችን ጋር በማዋሃድ፣ በፍቅሩ በመለወጥ እኛን ወደ እግዚአብሔር የሚመራን እና ወደ እርሱ መግቢያ በርን የሚወክል እርሱ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለምዕመናን ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ!  በሮም የሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባሲሊካ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት ክርስቲያኖች የእምነት ጉዞን የምትንከባከብ እናት እንድትሆን ከተጠራችው ከሮም ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን የአንድነት እና የኅብረት ምስጢር እንመለከታለን።

እንደምናውቀው የሮም ሀገረ ስብከት ካቴድራል እና የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ መቀመጫ የሆነው የቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ካቴድራል እጅግ በጣም አስደናቂ ታሪካዊ፣ ጥበባዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች የሚገኝበት ብቻ ሳይሆን ሐዋርያት ጠብቀውት ያቆዩትን እና ለሌሎች ሲያስተላልፉ የቆዩትን እምነት የመመስከር ኃይል ያለው ነው። የዚህ ምስጢር ታላቅነት በባዚሊካው ሕንፃ ጥበባዊ ግርማም ተገልጿል። በባዚሊካው በማዕከላዊ ሥፍራ የቆሙት አሥራ ሁለት ትላልቅ ሐውልቶች የኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ተከታዮች እና የወንጌል ምስክሮችን የሚያሳዩ ናቸው።

ይህ የሚያመለክተው ከውጫዊው ገጽታ ባሻገር የቤተ ክርስቲያን ምስጢር ከአካላዊ ሥፍራነት፣ ከድንጋይ ከተሠራ ሕንፃ የበለጠ መሆኑን እንድንረዳ የሚረዳን መንፈሳዊ እይታን ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ የዮሐ. 2:13-22 ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስን ማነጹን ያስታውሰናል። የእግዚአብሔር እውነተኛ መቅደስ፣ ለእኛ ሲል የሞተው እና ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ ብቸኛው መዳኛችን፣ ብቸኛው ቤዛችን፣ ራሱን ከሰውነታችን ጋር በማዋሃድ እና በፍቅሩ በመለወጥ፣ ለእኛ የተከፈተውን እና ወደ እግዚአብሔር አብ የሚመራንን በር የሚወክል ነው። (ዮሐ. 10:9)

ከእርሱ ጋር በመተባበር እኛም የዚህ መንፈሳዊ ሕንጻ ሕያው ድንጋዮች ነን (1ኛ ጴጥሮስ 2:4-5)። እኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አካል፣ ምህረትን፣ መጽናናትን እና የሰላም ወንጌልን በዓለም ሁሉ ለማሰራጨት የተጠራን የእርሱ አባላት፣ በዚህም መንፈሳዊ አምልኮ ከሁሉም በላይ በሕይወት ምስክርነታችን ውስጥ መብራት አለበት።

ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! ይህን መንፈሳዊ አመለካከት እንዲኖረን ልባችንን ማስተማር አለብን። ብዙውን ጊዜ የክርስቲያኖች ድክመት እና ስህተት ከብዙ የተሳሳቱ ምስሎች እና ጭፍን ጥላቻዎች ጋር ተዳምሮ የቤተ ክርስቲያንን ምስጢራዊ ሃብትን እንዳንረዳ ያደርጉናል። እንደ እውነቱ ከሆነ የቤተ ክርስቲያን ቅድስና በእኛ ብቃት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ነገር ግን ወደ ኋላ በማይመለስ የእግዚአብሔር ስጦታ እና እጆቹ የቆሸሸውን የሰውን ልጅ ለማጽዳት ያሳየው አስደናቂ ፍቅር መምረጥን ቀጥሏል (ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ፥ የክርስትና መግቢያ (ብሬሻ፥ 2005 እ.አ.አ)።

እንግዲህ በእግዚአብሔር የተመረጥ ቅዱስ ሕዝቦች በመሆን በደስታ እንጓዝ። ኢየሱስ ክርስቶስን በልባችን እንድንቀበል የቤተ ክርስቲያን እናት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ እንድትረዳን እንለምናት።”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እሑድ ጥቅምት 30/2018 ዓ. ም. የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ሲመሩ

 

 

10 Nov 2025, 16:39