ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጀመሪያውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረግ ጀመሩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጀመሪያውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረግ ጀመሩ  (@VATICAN MEDIA)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የመጀመሪያውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረግ ጀመሩ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የመጀመሪያውን ሐዋርያዊ ጉዞቸውን ሲጀምሩ ከሮም ፉሚቺኖ የአየር ማረፊያ ተነስተው ወደ ቱርክ እስታቡል ያቀኑ ሲሆን ይህም የአንድነትና የሰላም ምልክት ለማቅረብ ወደ ቱርክ እና ሊባኖስ ይወስዳቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ቱርክ የምያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ዛሬ ጀመረዋል። ቅዱስነታቸው ከሕዳር 18 እስከ ሕዳር 21/2018 ዓ.ም በቱርክ ለምያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተመረጠው አርማ "አንድ ጌታ፥ አንድ እምነት፥ አንድ ጥምቀት" (ኤፌሶን 4፡5) የተሰኘ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የተካተተበት ሲሆን የቅድስት መንበር የፕሬስ ጽ/ቤት እንዳስታወቀው፣ በዐርማው ላይ የድልድይ ምስል ይታያል፣ በድልድዩ ስር የጥምቀት ውሃዎችን እንዲሁም የኢዝኒክ ሐይቅን ለመግለጽ የተጠቀሙበት ሞገዶች ይታያሉ። በአርማው በስተቀኝ እ.አ.አ የ2025 ዓ.ም የኢዮቤልዩ መስቀል አለ፣ ከላይ በግራ በኩል ደግሞ ሦስት የተጠላለፉ ቀለበቶች ቅድስት ሥላሴን የሚወክሉ ምስሎች ተቀምጠዋል። ዐርማው በክብ ምስል የተሰራ ነው፣ ክቡ የእግዚአብሔርን አንድነት ያመለክታል፤ ድልድዩን፣ ሕዝቦችን አንድ የሚያደርግ አንድ እምነት፤ እንዲሁም ማዕበሎቹ፣ ለእግዚአብሔር ልጆች አዲስ ሕይወት የሚሰጥ ጥምቀት ይገልጻል” ሲል የቅድስት መንበር የፕሬስ ጽሕፈት ቤት ተናግሯል። “ይህም በምስራቅና በምዕራብ አገራት መካከል ወንድማማችነትንና ውይይትን እንድንገነባ ይጋብዘናል” ሲል መግለጫው አክሎ ገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን የያዘው አውሮፕላን ሐሙስ ዕለት ሕዳር 18/2018 ዓ.ም በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ረፋዱ ላይ  3፡58 አከባቢ ከሮም ፉሚችኖ አየር ማረፊያ ተነስቶ ወደ አንካራ፣ ቱርክ እያመራ ይገኛል።

ይህ የጣሊያን አየር መንገድ ንብረት የሆነው ኤርባስ ኤ320ኒዮ ክፍሎች ውስጥ የመልካም ምክር እናታችን የሆነችው የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ምስል፣ በኦገስቲናውያን ማሕበር አባላት ዘንድ የተከበረች የቅድስት ድንግል ማርያም ማዕረግ ምስል ተሰቅሎ ይገኛል።

በማዕረጉ ስር ለእመቤታችን የሚደረግ አምልኮ ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አውጉስቲናውያን ያገለገሉበት ጣሊያን ውስጥ በሚገኘው የጌናዛኖ ኮረብታማ ከተማ ቤተክርስቲያን ጋር የተሳሰረ ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ሆነው ከተመረጡ ከሁለት ቀናት በኋላ በጌናዛኖ የሚገኘውን ቤተክርስቲያን ጎብኝተው እንደ ነበረ ይታወሳል። በዚያ ጉብኝት፣ ከሽኮደር፣ አልባኒያ የመጣውን የመልካም ምክር እናታችን ጥንታዊ ምስል ግርጌ ጸልየው እንደ ነበረ ይታወሳል።

የመጀመሪያው ቀን በቱርክ

የርዕሰ ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ ወደ ቱርክ እና ሊባኖስ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በአንካራ ይጀምራል፣ የመጀመሪያ ማረፊያቸውም የቱርኪክ ሪፐብሊክ አባት በሆኑት በሙስጠፋ ከማል አታቱርክ መካነ መቃብር በሚገኝበት ሥፍራ አከባቢ ይሆናል።

ከዚያም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከፕሬዚዳንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር ለመገናኘት እና ለሲቪል ባለስልጣናት እና ለዲፕሎማሲ አካላት ንግግር ለማድረግ ወደ ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት እንደምያቀኑ ይጠበቃል። ከዚያም ጳጳሱ እንደገና ወደ ኢስታንቡል ይጓዛሉ፣ እዚያም በቱርክ ጉብኝታቸው ቀሪ ጊዜ በቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ልዑክ መኖሪያ እንደሚሆን ተገልጿል።

27 Nov 2025, 13:04