ር.ሊ.ጳ ሊዮ በኒቂያ ጉባኤ መታሰቢያ ላይ 'በእምነት አንድነት' የሚል ሐዋርያዊ መልእክት ይፋ አደረጉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ከሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ጉዞ በፊት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እ.አ.አ በ325 ዓ.ም በኒቂያ ጉባኤ የተካሄደበትን 1700ኛ ዓመት የመታሰቢያ በዓል ምክንያት በማድረግ 'በእምነት አንድነት' በሚል ርዕስ ሐዋርያዊ መልእክት ይፋ ያደረጉ ሲሆን ሐዋርያዊ መልእክቱ በ12 ነጥቦች የተከፈለ ነው፣ "ቤተ ክርስቲያን በሙሉ ለእምነት መግለጫ (ጸሎተ ሐይማኖት) ያላትን ጉጉት እንድታድስ ለማበረታታት" ተስፋ በማድረግ ይፋ ያደረጉት መልእክት ነው።
ወደ ቱርክ ከሚደረገው ሐዋርያዊ ጉዞ በፊት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሁድ ህዳር 14/2018 ዓ.ም የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘነድ በተከበረው የክርስቶስ ንጉሥ ዓመታዊ በዓል ላይ 'በእምነት አንድነት' በሚል አርዕስት ሐዋርያዊ መልእክት ይፋ አድርገዋል።
"ቤተ ክርስቲያን በሙሉ ለእምነት መግለጫ ያላትን ጉጉት እንድታድስ ለማበረታታት" ያሰበ ተስፋ ያለው ሙሉ ሐዋርያዊ መልእክት ሲሆን በአስራ ሁለት ነጥቦች የተከፈለ ነው።
እ.ኤ.አ. በ2025 ዓ.ም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የኒቂያ የመጀመሪያ ጉባኤ 1,700ኛ ዓመት መታሰቢያን እያከበረች ሲሆን ይህም እ.አ.አ በ325 ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ቀዳማዊ በኒቂያ ከተማ የተጠራ ጉባኤ እንደ ነበረ ይታወሳል፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከጣሊያን ውጪ ወደ ቱርክ የሚደረጉት የመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጉብኝት ወደ አንካራ፣ ኢስታንቡል እና ኢዝኒክ፣ በአንድ ወቅት ኒቂያ በመባል ይታወቅ ነበር ስፍራ እንደሚከናወን የተገለጸ ሲሆን በእዚያም የመጀመሪያው የኒቂያ ጉባኤ የተካሄደበትን 1700ኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
የኒቂያ ጉባኤው ሥነ-መለኮታዊ አለመግባባቶችን ለመፍታት እና አንድ ወጥ የሆነ የክርስትና አስተምህሮ ለመመስረት ያለመ የመጀመርያው ጉባኤ ሲሆን ውጤቶቹም የክርስቶስን መለኮታዊ ባሕሪይ ማረጋገጥ እና የኒቂያ የሃይማኖት መግለጫን (ጸሎተ ሐይማኖት) ማዘጋጀትን ያካተተ ነበር።
ይህንን ከግምት ባስገባ መልኩ የርዕሰ ሊቀ ጳጳሳት ሊዮ ሐዋርያዊ መልእክት፣ ከሁሉም በላይ ለአንድነት የቀረበ ጥሪ ነው። "ከቤተ ክርስቲያን መጀመሪያ ጀምሮ በታወጀው የእምነት አንድነት" ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጽሑፉን ይጀምራሉ፣ "ክርስቲያኖች በፍቅርና በደስታ የተቀበሉትን ስጦታ እንዲጠብቁና እንዲያስተላልፉ ተጠርተዋል" በማለት በማስታወስ፣ "ይህም በሃይማኖት መግለጫው (ጸሎተ ሐይማኖት) ውስጥ የተገለጸው "በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ፣ በእግዚአብሔር አንድያ ልጅ አምናለሁ… ለመዳናችን ከሰማይ በወረደው በእርሱ አምናለሁ" የተሰኙት የእምነት መግለጫዎችን አቅፎ የያዘ እንደ ሆነ ተገልጿል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህ እውነት ከ1700 ዓመታት በፊት በክርስትና ታሪክ የመጀመሪያው የኅብረት ጉባኤ በሆነው በኒቂያ ጉባኤ እንዴት ውጤታማ በሆነ መንገድ እንደተቀረፀ አስታውሰዋል።
'የሃይማኖት መግለጫው (ጸሎተ ሐይማኖት) ተስፋ ይሰጠናል'
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከሐዋርያዊ ጉዞአቸው በፊት የቤተክርስቲያኑኗን ትኩረት ወደ እምነት መግለጫ ለመሳብ እንደሚፈልጉ አጉልተው ገልጸዋል።
"ለዘመናት ይህ ዘላቂ የእምነት መገለጫ የክርስቲያኖች የጋራ ቅርስ ሲሆን፣ በአዲስ እና ተዛማጅ መንገዶች መገለጽ እና መረዳት ይገባዋል" ሲሉ በሐዋርያዊ መልእክታቸው ገልጸዋል።
"ለዘመናት፣ ዘላቂ የእምነት መግለጫ የክርስቲያኖች የጋራ ቅርስ ሆኖ ቆይቷል፣ እናም በአዲስ እና ተዛማጅ መንገዶች መገለጽ እና መረዳት ይገባዋል" በማለት በሐዋርያዊ መልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው በዚህ ቅዱስ ዓመት፣ ተስፋችን ለሆነው ለክርስቶስ በተሰጠው ልዩ የኢዩቤሊዩ አመት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ "የኒቂያ የመጀመሪያ የክርስቲያኖች ሕብረት ጉባኤ (ኢኩሜኒካል)1700ኛ መታሰቢያ ዓመትን እያከበርን መሆናችን" የምያስደስት ነው ሲሉ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ገልጸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እ.አ.አ በ325 ዓ.ም. የኒቂያ ጉባኤ አዋጅ በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የታወጀው የእምነት መግለጫ "የክርስትና እምነት ልብ ነው" ብለዋል። "ዛሬም ቢሆን፣ በእያንዳንዱ ዕለተ ሰንበት በሚከናወነው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ፣ ሁሉንም ክርስቲያኖች አንድ የሚያደርገውን የኒቂያ-ቆስጢንጢኒያ የሃይማኖት መግለጫን እንደግማለን" ሲሉ አስታውሰዋል።
ከዚህም በላይ፣ "በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ በብዙ ስጋቶችና ፍርሃቶች፣ በጦርነትና በዓመፅ ዛቻዎች፣ በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በከባድ ኢፍትሃዊነትና አለመመጣጠን መካከል እየኖርን ነው" ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሐዋርያዊ መልእክታቸው የገለጹ ሲሆን "ይህ የሃይማኖት መግለጫ ተስፋ ይሰጠናል" ሲሉ በሐዋርያዊ መልእክታቸው አመላክተዋል።
ከሚለያየን ነገር የበለጠ የሚያዋህደን ነገር ይበዛል
በመጨረሻም፣ የኒቂያ ጉባኤ ዛሬ ጠቃሚ የሆነው በታላቁ የክርስቲያን ሕብረት አውድ ጠቀሜታ ምክንያት ነው። በእርግጥም በሁሉም ክርስቲያኖች መካከል አንድነትን ማሳካት የመጀመርያው የኒቂያ ጉባኤ የመጨረሻው ግብ ሲሆን ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ዋና ዓላማዎች አንዱ ነበር። ልክ ከሰላሳ ዓመታት በፊት፣ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ይህንን የማስታረቅ መልእክት በላቲን ቋንቋ "Ut Unum Sint" (ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ) በተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክት (እ.አ.አ ግንቦት 25፣ 1995 ዓ.ም) ላይ አበረታተዋል።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይግባውና፣ የክርስቲያኖች ሕብረት ንቅናቄ ባለፉት ስልሳ ዓመታት ውስጥ ብዙ ውጤት አስመዝግቧል። "ከኦርቶዶክስና ከምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እና ከተሃድሶው ከተወለዱት የቤተክርስቲያን ማህበረሰቦች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚታይ አንድነት እስካሁን አለመደረሱ እውነት ነው" ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አምነዋል።
“ይሁን እንጂ፣ በአንድ ጥምቀት እና በኒቂያ-ቆስጠንጢያ የሃይማኖት መግለጫ (ጸሎተ ሐይማኖት) ላይ የተመሠረተው የክርስቲያኖች ሕብረት "ኢኩሜኒካል" ውይይት” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስታውሰዋል፥ “የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና የቤተክርስቲያን ማህበረሰቦች አባላትን በኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን አድርገን እንድናውቅ እና በዓለም ዙሪያ ያሉትን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አንድ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንደገና እንድናገኝ አድርጎናል” ሲሉ ጽፈዋል።
ክርስቲያኖች “በአንድ እና ብቸኛ አምላክ፣ የሁሉም ሰዎች አባት፣ አንድ ጌታ እና እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እና አንድ መንፈስ ቅዱስ፣ አንድ ላይ እንመሰክራለን፣ እሱም ወደ ሙሉ አንድነት እና ወደ ወንጌል የጋራ ምስክርነት ይመራናል” ሲሉ አጉልተው በሐዋርያዊ መልእክታቸው ገልጸዋል፣ “በእውነት፣ አንድ የሚያደርገን ነገር ከሚለየን እጅግ የላቀ ነው!” ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
"በብዙ ግጭቶች በተከፋፈለና በተበታተነ ዓለም ውስጥ" ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እንዲህ ሲሉ በድጋሚ አረጋግጠዋል፣ "አንድ ዓለም አቀፋዊ የክርስቲያን ማህበረሰብ የሰላም ምልክት እና የእርቅ መሳሪያ ሊሆን ይችላል፣ በአለም አቀፍ የሰላም ቁርጠኝነት ወሳኝ ሚና ይጫወታል" ሲሉ በሐዋራያዊ መልእክታቸው ገልጸዋል።
"በብዙ ግጭቶች በተከፋፈለና በተበታተነ ዓለም ውስጥ፣ አንድ ዓለም አቀፋዊ የክርስቲያን ማህበረሰብ የሰላም ምልክት እና የእርቅ መሳሪያ ሊሆን ይችላል፣ በአለም አቀፍ የሰላም ቁርጠኝነት ወሳኝ ሚና ይጫወታል"።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ "በተለይ ከሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እና ከቤተክርስቲያን ማህበረሰቦች የተውጣጡ በርካታ ክርስቲያን ሰማዕታት ምስክርነትን እንዳስታወሱን" በመግለጽ "ትዝታቸው እንዴት እንደሚያስተሳስረን እና በዓለም ላይ ምስክሮች እና የሰላም ፈጣሪዎች እንድንሆን እንደሚያነሳሳን" በድጋሚ ተናግረዋል።
የኒቂያ የሃይማኖት መግለጫ በጉዟችን ውስጥ የማጣቀሻ ነጥብ ሊሆን ይችላል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህንን አገልግሎት በአስተማማኝ ሁኔታ ማከናወን ያለውን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው ሲናገሩ "በሁሉም ክርስቲያኖች መካከል አንድነት እና እርቅ ለመድረስ አንድ ላይ መጓዝ" እንደሚያስፈልግ "የኒቂያ የሃይማኖት መግለጫ (ጸሎተ ሐይማኖት) ለዚህ ጉዞ መሠረት እና ማጣቀሻ ነጥብ ሊሆን ይችላል" ብለዋል፣ "በሕጋዊ ልዩነት ውስጥ የእውነተኛ አንድነት ሞዴል ይሰጠናል" ብለዋል፣ "ስለዚህ፣ የጋራ ግንዛቤን ለማዳበር እና ከዚያም በላይ የሆነውን የጋራ ጸሎት ለማዳበር ይቻል ዘንድ የነገረ መለኮት ክርክሮችን (የቲዎሎጂ) ለመንፈስ ቅዱስ በመተው አንድ የምያደርገን የጋራ ጸሎት ያስፈልገናል" ሲሉ ተናግረዋል።
ሆኖም "ይህ ከክፍፍሎቹ በፊት ወደ ነበርንበት ወደ ቀድሞ ሕይወት ለመመለስ የሚሞክር የክርስቲያን ሕብረትን "ኢኩሜኒዝምን" አያመለክትም፣ እንዲሁም የአብያተ ክርስቲያናት እና የቤተ ክርስቲያን ማህበረሰቦች ልዩነት አሁን ያለውን ሁኔታ የጋራ እውቅና መስጠት አይደለም" ሲሉ ግልጽ አድርገዋል፣ ነገር ግን "ይልቁንስ ወደ ፊት የሚመለከት የክርስቲያን ሕብርተ "ኢኩሜኒዝም" ነው፣ ስጦታዎቻችንን እና መንፈሳዊ ቅርሳችንን ስንጋራ በውይይት እርቅን የሚፈልግ የክርስቲያን ሕብረት "ኢኩሜኒዝም" ነው የምያስፈልገን ሲሉ አክለው በሐዋርያዊ መልእክታቸው ገልጸዋል።
በክርስቲያኖች መካከል የነበረውን አንድነት መመለስ፣ ቅዱስ አባታችን እንዳሉት፣ "ድሆች አያደርገንም፤ በተቃራኒው ያበለጽገናል" ሲሉ ጠቀሜታውን አጽኖት ሰጥተው ገልጸዋል።
በመጨረሻም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ መልእክታቸውን የደመደሙት "መንፈስ ቅዱስ በዚህ ሥራ አብሮን እንዲመራን እና እንዲያንጸን" በመማጸን አብረን እንድንጸልይ በቀረበ ግብዣ ነው።
"In unitate fidei" የሚለው የላቲን አገላለጽ ወደ አማርኛ ቋንቋ "በእምነት አንድነት" ተብሎ ይተረጎማል። በተለይም በካቶሊክ እምነት ውስጥ በክርስቲያኖች መካከል ያለውን አንድነት አስፈላጊነት ለማጉላት በቤተክርስቲያን እና በሥነ-መለኮት አውዶች ውስጥ የተለመደ አገላለጽ ነው።
በቅርቡ አገላለጹ በሕዳር 14/2018 ዓ.ም የኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት ክብረ በዓል ለመዘከር ታስቦ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የተጻፈው አስፈላጊ ሐዋርያዊ መልእክት ርዕስ ሆኖ ልዩ ጠቀሜታ አግኝቷል።
በሐዋርያዊ መልእክቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ክርስቲያኖች የኒቂያን የሃይማኖት መግለጫ (ጸሎተ ሐይማኖት) እንደ የጋራ የእምነት፣ የተስፋ እና የአንድነት መሠረት እንደገና እንዲያገኙ ይጋብዛሉ፣ በስምምነት እንዲኖሩ እና ለዓለም የሰላም ምልክት እንዲሆኑ ያሳስባሉ።
