ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 'የአንድነትና የሰላም መልእክት' ይዘው ወደ ቱርክ እየተጓዙ መሆኑን ገለጹ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ቱርክ የምያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ዛሬ መጀመራቸውን ቀደም ሲል መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው ከሕዳር 18 እስከ ሕዳር 21/2018 ዓ.ም በቱርክ እና በሊባኖስ ለምያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተመረጠው አርማ "አንድ ጌታ፥ አንድ እምነት፥ አንድ ጥምቀት" (ኤፌሶን 4፡5) የተሰኘ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የተካተተበት ነው፣ የቅድስት መንበር የፕሬስ ጽ/ቤት እንዳስታወቀው፣ በዐርማው ላይ የድልድይ ምስል ይታያል፣ በድልድዩ ስር የጥምቀት ውሃዎችን እንዲሁም የኢዝኒክ ሐይቅን ለመግለጽ የተጠቀሙበት ሞገዶች ይታያሉ። በአርማው በስተቀኝ እ.አ.አ የ2025 ዓ.ም የኢዮቤልዩ መስቀል አለ፣ ከላይ በግራ በኩል ደግሞ ሦስት የተጠላለፉ ቀለበቶች ቅድስት ሥላሴን የሚወክሉ ምስሎች ተቀምጠዋል። ዐርማው በክብ ምስል የተሰራ ነው፣ ክቡ የእግዚአብሔርን አንድነት ያመለክታል፤ ድልድዩን፣ ሕዝቦችን አንድ የሚያደርግ አንድ እምነት፤ እንዲሁም ማዕበሎቹ፣ ለእግዚአብሔር ልጆች አዲስ ሕይወት የሚሰጥ ጥምቀት ይገልጻል” ሲል የቅድስት መንበር የፕሬስ ጽሕፈት ቤት ተናግሯል። “ይህም በምስራቅና በምዕራብ አገራት መካከል ወንድማማችነትንና ውይይትን እንድንገነባ ይጋብዘናል” ሲል መግለጫው አክሎ ገልጿል።
ወደ አንካራ በሚወስደው የጳጳስ አውሮፕላን ውስጥ የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከ80 በላይ ጋዜጠኞች ከእርሳቸው ጋር መጓዛቸው የተገለጸ ሲሆን ጋዜጠኞቹ ለቅዱስነታቸው ሞቅ ያለ አቀባበል በአውሮፕላን ውስጥ ካደረጉላቸው በኋላ እንደ የቤዝቦል መጫወቻ ባት ወይም ወፍራም ዱላ፣ በሚስዮናዊነት ያሳለፉትን ጊዜ የሚያሳዩ ፎቶዎችን እና የዱባ ኬክ ያሉ በርካታ ስጦታዎችን አበርክተዋል፤ እንዲሁም ወደ ቱርክ እና ሊባኖስ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ ሰላምንና አንድነትን ለማስፈን ያለመ እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።
በእለቱ ማለትም እ.አ.አ በሕዳር 27/2025 ዓ.ም በዩናይትድ ስቴትስ የምስጋና በዓል እየተከበረ መሆኑን በማስታወስ ቅዱስነታቸው "እዚህ ላሉት አሜሪካውያን፡ መልካም የምስጋና በዓል!" (እ.አ.አ በሕዳር 27/2025 ዓ.ም በዩናይትድ ስቴትስ የምስጋና በዓል እየተከበረ ይገኛል፣ ይህ በዓል ምስጋናን ለመግለጽ፣ ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር ለመሰብሰብ እና የበዓል ምግብ በመጋራት የሚከበር ቀን ነው) ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መልካም ምኞታቸውን የገለጹ ሲሆን ከሮም አለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ከተነሱ ከ20 ደቂቃዎች በኋላ ቅዱስነታቸው በአውሮፕላን ውስጥ ለሚገኙ ጋዜጤኞች ሰላምታ ማቅረባቸው ተገልጿል።
“ይህንን ቀን ማክበር አስደናቂ ነገር ነው፣ እናም ለቫቲካን፣ ለቅድስት መንበር እና ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለምም ላደረጋችሁት አገልግሎት እያንዳንዳችሁን በማመስገን መጀመር እፈልጋለሁ” ሲሉ ወደ አንካራ በበረራ ላይ ለነበሩት ከ80 በላይ ለሆኑ ጋዜጠኞች ተናግረዋል። ይህም የመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጉዞ የመጀመሪያ ኦፊሴላዊ ንግግራቸው ሲሆን ከህዳር 18 እስከ ሕዳር 23/2018 ዓ.ም ድረስ ወደ ቱርክ እና ሊባኖስ የምያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አካል ነው።
“ዛሬ መልእክቱ ዓለም የሚያስፈልገውን እውነት እና ስምምነት በእውነት በሚገልጽ መንገድ መተላለፉ በጣም አስፈላጊ ነው” ሲሉ ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “በተለይም ወደ ቱርክ እና ወደ ሊባኖስ የሚደረገው ይህ ልዩ ጉዞ በመጀመሪያ ደረጃ የአንድነት ትርጉም አለው፣ ከኒቂያ ጉባኤ በኋላ ያሉትን 1,700 ዓመታትን ያከብራል” ብለዋል።
እንደ ቅዱስ አጎስጢኖስ ማሕበር አባል ካህን ሆነው ወደ ብዙ አገሮች ቢጓዙም፣ ይህ በሁለቱም አገሮች ማለትም በቱርክ እና በሊባኖስ የምያደርጉት ጉዞ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ይሆናል፣ ከዚህ ቀደም ቅዱስነታቸው ከሲመተ ጵጵስናቸው በፊት በሁለቱ አገራት ጉብኝት አድርገው አያውቁም ነበር። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህንን ጉብኝት በጉጉት ይጠብቁ እንደ ነበረ ተናግረዋል፣ ምክንያቱም ለክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለምም ሰላምን በማስፈን ረገድ ምን ማለት እንደሆነ የሚመስከር ሐዋርያዊ ጉብኝት በመሆኑ የተነሳ ነው።
“በልዩ መንገድ፣ የቤተክርስቲያን፣ በቱርክም ሆነ በሊባኖስ የሚገኙ አማኞች መገኘት፣ ሰላም በዓለም ዙሪያ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማሳወቅ፣ ለማስተላለፍ እና ለማወጅ እንዲሁም ሁሉም ሰዎች የበለጠ አንድነት እና የተሻለ ስምምነት ለመፈለግ እንዲሰባሰቡ እና ሁሉም ወንዶችና ሴቶች በእውነት ወንድማማቾች እና እህቶች ሊሆኑ የሚችሉባቸውን መንገዶች ለመፈለግ እንዲመጡ ለመጋበዝ ተስፋ እናደርጋለን፣ ልዩነቶች ቢኖሩም፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች ቢኖሩም፣ የተለያዩ እምነቶች ቢኖሩም” ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።
ሁሉም ሰው “በዓለም ዙሪያ ሰላምን እና አንድነትን በማበረታታት ረገድ አንድ አካል መሆን” እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጿል፣ እናም የፕሬስ ጓዶቹን ወይም ጋዜጠኞቹን ለአገልግሎታቸው እና “የዚህ ታሪካዊ ወቅት አካል በመሆናቸው” በድጋሚ አመስግነዋል።
ሳቅ፣ ስጦታዎች እና ቀልዶች
ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ የሚዲያ ተቋማትን የሚወክሉ ጋዜጠኞች ደስታቸውን በግልጽ አሳይተዋል። ጋዜጠኞች፣ የቪዲዮ ጋዜጠኞች እና ፎቶግራፍ አንሺዎች ቆመው ለቅዱስነታቸው አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ከዚያም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋዜጠኞችን አንድ በአንድ በአውሮፕላኑ ጠባብ መንገድ ውስጥ እየተዘዋወሩ ሰላምታ ሰጥተዋቸዋል፣ እጅ ለእጅ መጨባበጡ፣ ሳቅ፣ ቀልዶችን እና ፎቶግራፍ ማንሳት የግንኙነት አንድ አካል ነበር። ብዙ ጋዜጠኞች እንደ የምስጋና በዓልን ለማክበር የዱባ ኬክ እና የርዕሰ ሊቀ ጳጳሳቱን ተወዳጅ የቤዝቦል ቡድን የሆነውን የቺካጎ ዋይት ሶክስን ጫማዎች እና ካልሲዎች የያዘ ኪት ያሉ ስጦታዎችን ለቅዱስነታቸው አበርክተዋል።
ወደ ቱርክ ሲደርሱ
አጭር በረራ ካደረጉ በኋላ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከሰዓት በኋላ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር 12፡22 የሐዋርያዊ ጉዟቸው የመጀመሪያ መዳረሻ በሆነችው ከተማ በአንካራ፣ ቱርክ አረፉ።
በአንካራ ቅዱስነታቸው በደረሱበት ወቅት በቱርክ የቅድስት መንበር ልዑክ እና የአገሪቱ የፕሮቶኮል ዋና ኃላፊ ቅዱስ አባታችንን ከአውሮፕላኑ ውስጥ ከወጡ በኋላ በኤሰንቦጋ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በይፋዊ ሥነ ሥርዓት ተቀብለዋል።
ቅዱስ አባታችን ወደ ዋና ከተማዋ አንካራ ሲደርሱ የቱርክ ሪፐብሊክ መስራች እና የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ የመጨረሻ የማረፊያ ቦታ ላይ የሚገኘውን የመታሰቢያ መካነ መቃብር ጎብኝተዋል።
ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር ተገናኝተዋል፣ ከቱርክ ባለስልጣናት፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲያዊ ጓዶች አባላት ጋር ተገናኝተው ንግግር አድርገዋል። በቀኑ መጨረሻ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከአንካራ በአውሮፕላን ወደ ኢስታንቡል የቱርክ ትልቁ ከተማ ይጓዛሉ።
ወደ ቱርክ የተደርገው ሐዋርያዊ ጉዞ መሪ ቃል "አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት" የሚል ሲሆን በምስራቅ እና በምዕራብ መካከል ወንድማማችነትን እና ውይይትን በመገንባት ላይ ያተኩራል።
