ፈልግ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት በሊባኖስ መዲና ቤይሩት ውስጥ ከተደረጉት ዝግጅቶች መካከል  የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት በሊባኖስ መዲና ቤይሩት ውስጥ ከተደረጉት ዝግጅቶች መካከል  

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በቱርክ እና ሊባኖስ የሚያደርጉት ጉብኝት የሰላም እና የተስፋ ምልክት መሆኑ ተነገረ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ቱርክ እና ሊባኖስ የሚያደረጉትን የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉዞ በማስመልከት የቅድስት መንበር መግለጫ ጽ/ቤት ዳይሬክተር ማቴዎ ብሩኒ ማብራሪያ ሰጥተዋል። አቶ ማቴዎ ብሩኒ በመግለጫው፥ ቅዱስነታቸው በአገራቱ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የክርስቲያኖችን ኅብረት እና በሃይማኖቶች መካከል የሚደረገውን የጋራ ውይይት የሚያበረታታ እንዲሁም ለአገራቱ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ድጋፍ እንደሚሆን አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር መግለጫ ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ በማብራሪያቸው ታሪካዊ የእርስ በርስ ግንኙነት ምሳሌ በሆነው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ቅዱስነታቸው ከሲቪል እና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር እንደሚሰበሰቡ እና ክልላዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያለመ የመተጋገዝ ምልክትን ያለበት እንደ ሆነ ገልጸው፥ ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ጉብኝት በኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ መገኘትን ጨምሮ አንካራን፣ ኢስታንቡልን እና ቤሩትን የሚጎበኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ጠንካራ የክርስቲያኖች ኅብረት ባህሪ ያለው እና በሃይማኖቶች መካከል የሚደረገውን የጋራ ውይይት ማዕከል ያደረገ እንዲሁም በክልሉ ውስጥ ካሉ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች እና የአካባቢው ሕዝቦች ጋር የጠበቀ ግንኙነት የሚመሠርቱበት ጊዜ እንደሚሆን እና ይህን ዓላማ ፍሬያማ ለማድረግ አስፈላጊው የደህንነት እርምጃዎች ሁሉ መወሰዳቸውን አቶ ማቴዎ ብሩኒ አክለው አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቱርክ እና ሊባኖስ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉት ከሐሙስ ኅዳር 18 እስከ ማክሰኞ ኅዳር 23/2018 ዓ. ም. ድረስ እንደሆነ ታውቋል።

በሁለት ቁልፍ አገራት ውስጥ የሚደረግ ሐዋርያዊ ጉብኝት

አቶ ማቴዎ ብሩኒ በመግለጫቸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በእነዚህ ሁለት ቁልፍ አገራት ውስጥ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አድካሚ በመሆኑ ብርታትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።  ቱርክ የቅዱስ ጳውሎስ የትውልድ አገር እና ጥንታዊት የክርስትና እምነት አገር እንደሆነች እና ሊባኖስ፣ በኢኮኖሚ ቀውስ፣ በወደብ ፍንዳታ እና በቅርቡ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል በተከሰቱት ሁከቶች ክፉኛ የተጎዳች ብትሆንም አብሮ የመኖር ምልክት እንደሆነች አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በክልሉ በሚያደርጉት የአንድ ሳምንት ያህል ቆይታ ከሲቪል እና ከሃይማኖት ባለሥልጣናት ጋር እንደሚገናኙ፣ መስጊዶችን እና ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትን እንደሚጎበኙ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2020 ዓ. ም. በተከሰተው ፍንዳታ የተጎዱትን  ለማስታወስ በቤሩት ወደብ ተገኝተው ጸሎት እንደሚያቀርቡ እና ከሁለቱ አገራት ፕሬዚዳንቶች፥ ከፕሬዝደንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን እና ከፕሬዝደንት ጆሴፍ አውን ጋር በግል እንደሚገናኙ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቀደሙት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ማለትም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ እና በኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ ለመገኘት ተስፋ አድርገው የነበሩ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ፈለግ እንደሚከተሉ አቶ ማቴዎ ማቴዎ ብሩኒ ገልጸዋል።

ለክርስቲያኖች ኅብረት ትኩረት መስጠት እና ወጣቶችን መደገፍ

“የክርስቲያኖች የኅብረት አቅጣጫ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና አካል ነው” ያሉት አቶ ማቴዎ ብሩኒ፥ የብዙ ባሕሎች ባለቤት የሆኑ ክርስቲያኖች የኒቂያን ጉባኤ የጋራ እምነት መሠረት አድርገው እንደሚቀበሉት አስታውሰው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በውጭ አገር የሚኖሩትን በርካታ የሊባኖስ ክርስቲያኖችን ጨምሮ ስደት እና አለመረጋጋት የሚገጥማቸውን በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ካቶሊካዊ ማኅበረሰቦችን እንደሚደግፏቸው አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በማሮናዊት ቤተ ክርስቲያን ከሊባኖስ ወጣቶች ጋር የሚያደርጉት ስብሰባ እጅግ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ይህ ስብሰባ በኢዮቤልዩ ዓመት ጠንካራ የተስፋ መልዕክቶችን ይይዛል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን የቅድስት መንበር መግለጫ ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ በመግለጫቸው ተናግረዋል።

 

26 Nov 2025, 16:07