ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ሊዮ 14ኛ፥ ቅዱሳት መጽሐፍት ወጣቶችን በቀላሉ ሊደርሳቸው እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰኞ ዕለት ከካቶሊክ የመጽሐፍ ቅዱስ ፌዴሬሽን አባላት ጋር ተገናኝተው የእግዚአብሔር ቃል ወደ ሰዎች ዘንድ እንዲደርስ ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “Dei Verbum” ወይም የእግዚአብሔር ቃል የተሰኘ የመለኮታዊ ራዕይ ሕገ-ቀኖናዊ ድንጋጌ 60ኛ ዓመት መታሰቢያ እና ቅዱሳት መጽሐፍት ወደ የትኛውም ቦታ በቀላሉ እንዲደርስ እና ክብር እንዲሰጠው በማለት ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ባቀረበው ጥሪ ላይ በማሰላሰል፥ ሠነዱ ጠንካራ ፍላጎትን፣ ጽኑ እምነትን እና የእረኝነት ዘዴን የሚያስተዋውቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
“የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት የማያሻማ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “የእግዚአብሔርን ቃል በአክብሮት ለማዳመጥ እና በእምነት ለመመስከር የተጠራን በመሆናችን ክርስቲያኖችን በሙሉ በቀላሉ ሊደርሳቸው ይገባል” ብለዋል።
የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ፌዴሬሽንም ተመሳሳይ ግብ እንዳለው ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ፌዴሬሽኑ የእግዚአብሔርን ቃል ወደ ሕዝቦች ማዳረስን የአገልግሎቱ ዋና አካል ለማድረግ እና ለቤተ ክርስቲያንም የመነሳሳት ምንጭ ለማድረግ እየጣረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሮም የተሰበሰቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ለተልዕኮአቸው ታማኝነት የገቡትን ቃል እንዲያድሱ ጋብዘው፥ ይህም “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ምስጢር ከሆነው የወንጌል አዋጅ “kerygma” የተለየ አይደለም” ብለው፥ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር ኢየሱስ ክርስቶስን በትኩረት በማዳመጥ ሕይወትን ከወንጌሉ ታገኛለች ብለዋል።
“ቤተ ክርስቲያን የጉዞ አቅጣጫዋን ሳታቋርጥ የምታገኘው መንፈስ ቅዱስ በመሪነቱ ሁሉንም ነገር ከሚያስተምረው፣ ከሚያስታውሰው እና ወልድ ከተናገረው ወንጌል ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ቅዱስነታቸው በዘመናችን ውስጥ “የእግዚአብሔር ቃል ሰዎችን በቀላሉ እንዲደርስ” በሚለው ላይ በማሰላሰል ሲናገሩ፥ ምዕመናን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ መበረታታት እንዳለባቸው ጠቁመው፥ “ይህም በሰው ቃል የተገለጸውን የእግዚአብሔርን ፍቅር በግል እንዲያገኙ ማድረግ ነው” ብለዋል።
“ዛሬ አዳዲስ ትውልዶች የእግዚአብሔር ቃል በቀላሉ በሚደበቁባቸው አዳዲስ የዲጂታል መሣሪያዎች ዘመን ውስጥ ይኖራሉ” ብለው፥ አዳዲስ ማኅበረሰቦች ብዙውን ጊዜ ወንጌል በማይታወቅባቸው ወይም በተዛባባቸው ባሕሎች ውስጥ ይገኛሉ” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለካቶሊክ የመጽሐፍ ቅዱስ ፌዴሬሽን አባላት ባደረጉት ንግግር፥ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የማያውቁ ሰዎችን እንዴት በተሻለ መንገድ መርዳት እንደምትችል ራሳቸውን እንዲጠይቁ ጋብዘዋል።
“እነዚህ ጥያቄዎች ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚወስዱ መንገዶችን እንደሚያሳዩ እና አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተደራሽነት ዓይነቶችን ለማወቅ እንደሚያነሳሱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ይህም የእግዚአብሔር ቃል በሰዎች ልብ ውስጥ ሥር እንዲሰድድ እና ሁሉም በጸጋው እንዲኖሩ ይመራቸዋል” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ሁሉም ክርስቲያኖች “በቀለም ሳይሆን በሕያው እግዚአብሔር የተጻፉ ሕያው ፊደላት” እንዲሆኑ ጋብዘው፥ ይህን በማድረጋቸው ዓለማችንን ከሞሉት ብዙ ድምጾች በላይ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚበልጥ ይመሰክራሉ” ብለዋል።
“ቃል ሥጋ በሆነበት ማኅጸኗ የተባረከች የእግዚአብሔር እናት ቅድስት ድንግል ማርያም የማዳመጥ ጥበብን እንድትሰጥን፣ ለቃሉ ታዛዦች ለመሆን እንድታበረታን እና እግዚአብሔርን ወደምንመሰክርበት መንገድ ትምራን” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።
