ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በማቅረብ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በማቅረብ ላይ  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጅ የጨለማ ታሪክ ተስፋን ያመጣል” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋችን ነው!” የሚለውን የኢዮቤልዩ ዓመት መሪ ሃሳብ መሠረት በማድረግ ያዘጋጁትን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል አቅርበዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ረቡዕ ጥቅምት 26/2018 ዓ. ም. ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ባቀረቡት አስተምህሮ፥ “የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጅ የጨለማ ታሪክ ተስፋን ያመጣል” ሲሉ ተናግረዋል።

ክቡራት ክቡራን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን የዕለቱን አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን፥ አስተንትኖ ያደረጉበትን የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ እናነብላችኋለን፥

“ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ አላቸው። ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። ስለዚህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ. 28:18-20)።

ክቡራት እና ክቡራን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ! የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ከረጅም ጊዜ በፊት የተገኘ ክስተት ሳይሆን ልክ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንደ ነበሩት ሌሎች ክስተቶች ሁሉ ዛሬ የተለመደ ሆኗል። በዚህ ጊዜ ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ የተስፋ ቃል ሙሉ በሙሉ እውን ስለሚሆን ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ በብርሃነ ትንሳኤው እሁድ እና በየቀኑ በሚቀርበው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የምናከብረው ቅዱስ ቁርባን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ሕያው መታሰቢያ እንድናደርግ ታስተምረናለች። ‘እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ’ (ማቴ. 28:20)።

በዚህም ምክንያት የብርሃነ ትንሳኤው ምስጢር የክርስትና ሕይወት መሠረት ሲሆን፥ ሌሎች ክስተቶች በሙሉ ተጨማሪዎች ናቸው። እንግዲህ እያንዳንዱ ቀን ‘ብርሃነ ትንሳኤ ነው’ ማለት እንችላለን። ነገር ግን ይህ በምን መንገድ ሊሆን ይችላል?

በየሰዓቱ የሚያጋጥሙን በርካታ ልዩ ልዩ ልምዶች አሉን። ህመም፣ ስቃይ፣ ሐዘን፣ ከደስታ ጋር የተገናኙ አስደናቂ እና አስገራሚ ሁኔታዎች አሉ። ነገር ግን በእያንዳንዱ ሁኔታ ውስጥ የሰው ልጅ ልብ ሙሉነትን እና ጥልቅ ደስታን ይናፍቃል። የሰውን ልጅ ምስጢራዊነት በጥልቀት የመረመረችው ታላቅ የሃያኛው ክፍለ ዘመን ፈላስፋ እና የቅዱስ መስቀል ወዳጅ ቅድስት ተሬዛ ቤኔዲክታ ወይም ኤዲት ስታይን ይህን የማያቋርጥ የልብ ሙላት ፍለጋን እንዲህ በማለት ታስታውሰናለች። ‘የሰው ልጅ ሁልጊዜ አዲስ ሆኖ መቅረብን ይናፍቃል፤ ጊዜው የሚሰጠውን ነገር የሚጠቀም ሲሆን፥ ያንን ያገኘውን ነገር ጊዜው መልሶ ይወስድበታል’ ስትል ጽፋለች። (ፍጹም እና ዘላለማዊ ፍጡር፤ ቁ. 387፣ ሮም 1998 እ.አ.አ) እኛ ውስኖች ብንሆንም ከዚህ ለመላቀቅ እንጥራለን።

የብርሃነ ትንሳኤው መልካም ዜና በታሪክ ከተሰሙት እጅግ ውብ፣ አስደሳች እና አስደናቂ ዜናዎች መካከል አንዱ ነው። ፍቅር በኃጢአት ላይ ድልን መቀዳጀቱ እና በሞት ላይ ሕይወትን መዝራቱን ማረጋግጥ እጅግ ጠቃሚ መልካም ዜና ነው። አእምሯችንን እና ልባችንን የሚያስቸግር የትርጉም ፍላጎት ማርካት የሚችል ብቸኛ መንገድ የሆነው ለዚህም ነው። የሰው ልጅ በውስጣዊ ነገር ቢመሰጥም በውጫዊው ነገር ያለማቋረጥ ይሳባል። ተጨባጭ እውነታ ምንም ቢሆን አያረካንም። ማለቂያ ወደሌለው እና ወደ ዘላለማዊው እናዘነብላለን። ይህም የሞት ተሞክሮ የሆነውን መከራን፣ ጥፋትን እና ውድቀትን ይቃረናል። ቅዱስ ፍራንችስኮስ ስለ ፀሐይ በዘመረው መዝሙሩ፥ ‘ከሞት ማምለጥ የሚችል ማንም የለም’ ብሏል።

የኢየሱስ ክርስቶስን አስክሬን ሽቶ ለመቀባት በጠዋት ወደ መቃብሩ የሄዱ ሴቶች መቃብሩ ባዶ ሆኖ ባገኙት ጊዜ ሁሉም ነገር ተለውጧል። ኮከቡን በምሥራቅ አይተውት ሊሰግዱለት ወደ ኢየሩሳሌም የመጡት ሰብዓ ሰገል፥ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ሲሉ ጠየቁ። (ማቴ 2:2)፣ ትክክለኛውን መልስ ያገኙት በብርሃነ ትንሳኤው ንጋት ነጭ ለብሶ ለሴቶቹ ከተናገረው ሚስጥራዊ ወጣት ነበር። ‘የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፤ እዚህ የለም’ አላቸው(ማር 16፡6)።

ከዚያ ንጋት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በየቀኑ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያውነት ማዕረግ አለው። ራሱን በራዕይ ላይ ማቅረብ ችሏል። ‘አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ’ (ራዕይ 1፡17-18)። በእርሱም አማካይነት ሁከት የሞላበት የሚመስለውን ሕይወታችንን የምንመራበት ኮከብ ሁልጊዜ ማግኘት እንደምንችል እርግጠኞች ነን። ብዙውን ጊዜ ግራ የሚያጋቡ፣ ተቀባይነት የሌላቸው፣ መረዳት የማንችላቸው በሚመስሉ ክስተቶች የተገለጹ፥ እያንዳንዳችንን የሚነኩ፥ በብዙ መልኩ ክፋት፣ መከራ እና ሞት ያሉባቸው ክስተቶች ያጋጥሙናል። ነገር ግን የትንሣኤውን ምስጢር በማሰላሰል ትርጉማቸውን ለማግኘት ባለን ጥማት መልስ እናገኝላቸዋለን።

ከደካማው ስብዕናችን ጋር ስንጋፈጥ የብርሃነ ትንሳኤው መልካም ዜና እንክብካቤ እና ፈውስ ይሆነናል። ሕይወት በየቀኑ በግል እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያቀርብልን አስፈሪ ፈተናዎች ፊት ለፊት ያለን ተስፋ ገንቢ ይሆነናል። በብርሃነ ትንሳኤው እይታ የመስቀል መንገድ ወደ ብርሃን መንገድነት ይለወጣል። ከስቃይ በኋላ ያለውን ደስታ ማጣጣም እና ማሰላሰል፣ ከትንሣኤ በፊት ያሳለፍናቸውን ደረጃዎች በሙሉ ወደ አዲስ ብርሃን መመለስ አለብን።

ብርሃነ ትንሳኤው መስቀልን ወይም መከራን ከእኛ አያስወግደውም። ነገር ግን የሰውን ልጅ ታሪክ የለወጠውን ተአምራዊ ፍልሚያን ያሸንፋል። በብዙ መስቀሎች የተመሰለው ጊዜያችን የብርሃነ ትንሳኤውን ተስፋ ይፈልጋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ሐሳብ ሳይሆን የእምነታችን መሠረት ነው። ከሞት የተነሣው እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ይህን ማስታወሱን ቀጥሏል። ስለዚህም የሰው ልጅ ታሪክ አድማስ ላይ ያለውን ብርሃን ማየት ባይችልም ምስክሮቹ እንድንሆን ይጋብዘናል። የብርሃነ ትንሳኤው ተስፋ ምንም ቢሆን አያሳፍርም። በዕለት ተዕለት ጉዟችን ብርሃነ ትንሳኤውን በእውነት ማመን ማለት ሕይወታችንን በመለወጥ መላውን ዓለም በክርስቲያናዊ ተስፋ እና ደፋር ኃይል መለወጥ ማለት ነው።”

 

05 Nov 2025, 16:21