ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “መዘምራን የቤተ ክርስቲያን የአንድነት ምልክት ለመሆን ተጠርተዋል” ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የመዘምራን ኢዮቤልዩ በዓልን ምክንያት በማድረግ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እሑድ ኅዳር 14/2018 ዓ. ም. የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት መርተዋል። ቅዱስነታቸው በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት ምዕመናን ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ መዘምራን አገልግሎታቸውን የቤተ ክርስቲያን የአንድነት ምልክት እንዲያደርጉት፣ በእምነት አብረው እንደሚጓዙ እና እንደ አንድ ሕዝብ በኅብረት እንዲዘምሩ በማሳሰብ፥ የአምልኮ ዝማሬ ኅብረትን ማበረታታት እንዳለበት እና መላው ቤተ ክርስቲያን ወደፊት እንዲጓዝ መርዳት እንዳለበት አደራ ብለዋል።

ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለምዕመናን ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማቅረባችን በፊት በዚህ የኢዮቤልዩ በዓል ላይ ለተሳተፋችሁ በሙሉ በተለይም ከመላው ዓለም ለመጣችሁ የመዘምራን ቡድኖች ሰላምታዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ። በበዓሉ ላይ ስለተገኛችሁ አመሰግናችኋለሁ፤ እግዚአብሔር አገልግሎታችሁን ይባርክ።

ለሌሎች ምዕመናንም በተለይም በጣሊያን ከቴራሞ-አትሪ ሀገረ ስብከት ለመጣችሁ እና ከዩክሬን የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች የመጣችሁ ምዕመናን በዚህ አደባባይ ያቀረብነውን ጸሎት ወደመጣችሁበት ቦታ ሁል አድርሱ።

በናይጄሪያ እና በካሜሩን የሚገኙ ካህናት፣ ምዕመናን እና ተማሪዎች መታፈን ስሰማ በጣም አዝኛለሁ። ከሁሉም በላይ ለታገቱት በርካታ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች እንዲሁም ችግር ውስጥ የወደቁ ቤተሰቦቻቸውን ሳስብ ከፍተኛ ህመም ይሰማኛል። ታጋቾቹ ወዲያውኑ እንዲፈቱ ጥሪ አቀርባለሁ።

የታገቱትን ለማስፈታት ሃላፊነት ያለባቸው የመንግሥት ባለስልጣናት ተገቢ እና ወቅታዊ ውሳኔዎችን እንዲወስዱ አሳስባለሁ። ለእነዚህ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንዲሁም ቤተ ክርስቲያናት እና ትምህርት ቤቶች ዘወትር እና በየትኛውም ቦታ የደኅንነት እና የተስፋ ቦታዎች ሆነው እንዲቀጥሉ እንጸልይ።

ዛሬ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን እያከበሩ ይገኛሉ። በልዩ ልዩ በዓላት እና ተነሳሽነቶች ውስጥ ከሚሳተፉት ጋር በመንፈስ በመተባበር እባርካቸዋለሁ። በክርስቶስ ንጉሡ በዓል ወጣቶች በሙሉ ኢየሱስን በመከተል እራሳቸውን ለፍቅር፣ ለፍትህ እና ለሰላም መንግሥት በማስገዛት የሚገኘውን ውበት እና ደስታ እንዲቀበሉ እጸልያለሁ።

ወደ ቱርክ እና ሊባኖስ የማደርገው የሐዋርያዊ ጉብኝት ጊዜ ተቃርቧል። በቱርክዬ የኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት መታሰቢያ ይከበራል። በዚህም ምክንያት ይህንን ታሪካዊ ክስተት የሚያስታውስ ‘In Unitate Fidei’ ወይም ‘በእምነት አንድ መሆን’ የተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክት ዛሬ ይታተማል።

አሁን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመመለስ ለእነዚህ ሃሳቦቻችን እና የሰላም ጸሎታችን የእናታችንን አማላጅነት እንለምን።”

24 Nov 2025, 14:48