ፈልግ

ከሀገረ ስብከቶች እና ከቁምስናዎች የተወጣጡ የአምልኮ ሥርዓት ትምህርት ተሳታፊዎች ከሀገረ ስብከቶች እና ከቁምስናዎች የተወጣጡ የአምልኮ ሥርዓት ትምህርት ተሳታፊዎች   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፥ የአምልኮ ሥርዓት ስልጠና በአዲስ መንገድ እና ዘዴ መታደስ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የምእመናንን የአምልኮ ሥርዓት እና የክርስቲያናዊ አምልኮ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖር የሚያግዙ አገልጋዮችን ለማዘጋጀት የሚደረገው ጥረት እንዲያበራታታ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም በሚገኘው የቅዱስ አንሴልሞ ጳጳሳዊ የሥርዓተ አምልኮ ተቋም የተዘጋጀውን የሥርዓተ አምልኮ ሐዋርያዊ አገልግሎት የሚሰጥ የሥልጠና ኮርስ የተሳተፉ የሀገረ ስብከት ኃላፊዎችን ሰኞ ኅዳር 9/2018 ዓ. ም. በቫቲካን የተቀበሉት ቅዱስነታቸው፥ በሀገረ ስብከቶች እና በቁምስናዎች የአምልኮ ሥርዓት ትምህርት እንዲጠናከር እና ሰልጣኞቹ መንፈስዊ አምልኮን በጥልቀት እንዲያውቁ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ስልጠናቸውን ከመጀመራቸው በፊት ቡድኑን በቫቲካን የተቀበሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ስልጠናው የሥርዓተ አምልኮ ባሕልን እና ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ የሚፈልገውን ተሃድሶ የሚያመቻች የቅዱስ አንሴልሞ ተቋም ተልዕኮን የሚያንፀባርቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “Desiderio desideravi” ወይም “እጅግ እመኝ ነበር” (ሉቃ. 22:15) በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳናቸው አማካይነት የሥርዓተ አምልኮ ጥናትን ለማሳደግ ያቀረቡትን መልዕክት የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ይህንን እውቀት ከሥነ-ምርምር ዘርፍ ውጭ በቀላሉ ተደራሽ በሆነ መንገድ ማሰራጨት አስፈላጊ እንደሆነ እና በዚህም እያንዳንዱ ምዕመን የሥርዓተ አምልኮን ሥነ-መለኮታዊ ትርጉም መረዳት እንዲችል” በማለት ያቀረቡትን ምክረ ሃሳብ አስታውሰዋል።

የሥርዓተ አምልኮ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ስልጠና ማጠናከር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአካባቢ ደረጃ የሚደረጉ አዲስ የስልጠና ጥረቶች አስፈላጊነትን በማጉላት በሀገረ ስብከቶች እና በቁምስናዎች ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ አደረጃጀት ለስልጠና አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው፥ በቅዱሳት መጻሕፍት እና በሥርዓተ አምልኮ ትምህርቶች ላይ መጀመር እንደሚገባ አክለዋል።

የቅዱስ አንሴልሞ ጳጳሳዊ የሥርዓተ አምልኮ ተቋም፣ ቤተ ክርስቲያናት የሳምንቱን ቀናት እና የእሁድ ዕለት የአምልኮ ሥነ-ሥርዓትን እንዲያብራሩ እና የምእመናንን ቀጣይነት ያለው የክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ ጅምር በመደገፍ እንዲረዳቸው ሐሳብ አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሀገረ ስብከት የሥርዓተ አምልኮ ጽሕፈት ቤቶች መሪዎች ቃለ እግዚአብሔርን ለሚያሰሙ ሰዎች ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ በማሳሰብ ጥልቅ ዝግጅት፣ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት፣ ግልጽ መዝገበ ቃላት እና የምእመናንን ጸሎት የመጻፍ ችሎታን ማካተት እንዳለበት አደራ ብለዋል።

ሥርዓተ አምልኮ ማሻሻልን ተግባራዊ ማድረግ መቀጠል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በኋላ ባለው ጊዜ ላይ በማሰላሰል የሥርዓተ አምልኮ ሥነ-ሥርዓትን በማበረታታት ረገድ ብዙ ዕድገት መታየቱን ቢያምኑም ወደፊት ረጅም መንገድ መኖሩን ተገንዝበዋል።

“በዚህ ጉዞ ድካም ሊሰማን አይገባም” ያሉት ቅዱስነታቸው እንደገና በአዲስ ጉልበት፣ በተሃድሶ እና በመልካም ተነሳሽነቶች መጀመር እንደሚገባ እና እንደዚሁም አዳዲስ መንገዶችን እና ዘዴዎችን መፈለግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሀገረ ስብከት የአምልኮ ሥርዓት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ሃላፊነቶች ለካኅናት እና ለምእመናን ቀጣይነት ያለውን ስልጠና በማዘጋጀት እንዲሁም የቁምስናው የአምልኮ ሥርዓት ቡድኖችን፣ መዘምራንን፣ ንባባት አቅራቢዎችን እና የመንበረ ታቦት ላይ አገልጋዮችን ማስተባበርን የሚያካትት መሆኑን ገልጸዋል።

ተግባራቸው የእግዚአብሔር ሕዝብ በአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ላይ ፍሬያማ ተሳትፎን እንዲያሳይ ማበረታታ እና ለልዩ ልዩ ስሜቶች ትኩረትን በመስጠት ንቁ የአምልኮ ሥርዓትን ማበረታታት እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በቁምስና ውስጥ የሚገኙ የሥርዓተ አምልኮ ቡድኖችን ማነቃቃት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ውስጥ የሥርዓተ አምልኮ ቡድኖች እየቀነሱ ወይም እየጠፉ መምጣታቸው እንዳሰጋቸው ገልጸው፥ የቁምስና መሪዎች ቁምስናዎችን እንደገና በመገንባት ረገድ እንዲደግፉ በማበረታታት፥ “ይህም የቤተ ክርስቲያን ሕይወት እንደገና ማራኪ እንዲሆን ለማድረግ፣ ብቁ ወይም ቢያንስ ለዚህ ዓይነት አገልግሎት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ለማሳተፍ የሚያስችል እንዲሆን ለመሥራት አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ ከቁምስና መሪ ካኅናት ጋር በመተባበር መንፈሳዊ በዓላትን የሚያዘጋጁ፣ በመዝሙር የሚያገለግሉ፣ ቅዱሳት ንባባትን የሚያሰሙ እና መንበረ ታቦትን የመሳሰሉ ቅዱሳት ቦታዎችን የሚያስውቡ ቡድኖችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

19 Nov 2025, 16:25