ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት ለምዕመናን ሰላምታ ሲያቀርቡ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት ለምዕመናን ሰላምታ ሲያቀርቡ  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በጤና ዘርፍ የሚሰጠውን ጥቅም ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በጤናው ዘርፍ የእንክብካቤ እና የግንኙነት ጥራትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበው፥ ግለሰባዊ ግንኙነቶችን የማይተካ መሆኑን ለማረጋገጥ ቫቲካን ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ የተሳተፉትን አበረታተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን የሥነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ “የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የሕክምና ፈተና በሰብዓዊ ክብር ላይ” በሚል ርዕሥ ከኅዳር 1-3/2018 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ጉባኤ አዘጋጅቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጉባኤው መጀመሪያ ሰኞ ኅዳር 1/2018 ዓ. ም. ለተሳታፊዎች በላኩት መልዕክት፥ በጤና አጠባበቅ ዘርፍ ስለ ሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ለሚደረገው ውይይት በጸሎት የታገዘ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመልዕክታቸው፥ የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሌሎች የቴክኖሎጂ እድገቶች በሰው ልጅ ላይ ያላቸውን ሰፊ ​​ተጽዕኖ አስታውሰው፥ “ይህም በአስተሳሰባችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ከማሳደሩ በላይ ራሳችንን እና ሌሎችን የምናይበት መንገድ ይለውጣል” ብለዋል።

“በአሁኑ ጊዜ ዘመናዊ መሣሪያዎችን እንደ አስተርጓሚዎች ስለምንጠቀማቸው የእነርሱ አስፋፊዎች በመሆን በዙሪያችን ካሉት ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ማጣት ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ መለየትን እና ማክበርን የመዘንጋት አደጋም ያጋጥመናል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቴክኖሎጂ ዕድገቶች በሕክምና እና በጤና ዘርፎች ያመጡትን ጥቅሞች የገለጹ ቢሆንም፥ ነገር ግን “እውነተኛ ዕድገት የግለሰቦችን እና የሕዝብን ሰብዓዊ ክብር እና የጋራ ጥቅምን እንዲጠብቅ ይጠይቃል” ብለዋል።

“ምንም እንኳን የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች በተንኮል ጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜ በሰው ልጅ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ሊያገለግሉ ቢችሉም እነዚያ ቴክኖሎጂዎች ለሰው ልጅ እውነተኛ አገልግሎትን ከሰጡ ለውጥ አምጪ እና ጠቃሚ የመሆን አቅም አላቸው ሲሉ” ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች የሰው ልጅ ሕይወት ጠባቂ እና አገልጋይ የመሆን ጥሪያቸውን እንዲያሟሉ እና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ በዘርፉ መሥራትን እንዲቀጥሩ አደራ ብለዋል።

ብዙውን ጊዜ የሰው ልጅ ደካማነት በሕክምናው ዘርፍ እንደሚታይ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን “በእግዚአብሔር ፈቃድ ስለተፈጠረ እና ስለተወደደ ብቻ የሚገባውን እውነተኛ ክብር ፈጽሞ መረሳት የለበትም” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለግለሰቦች እንክብካቤ በመስጠት ረገድ በሰዎች መካከል ባለው ሊተካ በማይችል ባህሪ ላይ በማትኮር፥ “የህክምና ባለሙያዎች እንክብካቤ ለመስጠት እና ከታካሚዎቻቸው ጋር ያላቸውን ቅርበት በመግለጽ ውጤታማ በሆነ መንገድ የመግባባት ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል” ብለዋል።

የጤና አጠባበቅ ችግርን ለመፍታት ብቻ ሊቆም አይችልም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች በታካሚው እና በተንከባካቢው መካከል ያለውን ግንኙነት ፈጽሞ ሊነጥቁ እንደማይገባ አክለዋል።

“የሰው ልጅን የሚያካትት የአዕምሮ ጤና አጠባበቅ ሥርዓት የሰው ልጅ ክብርን እና ውጤታማ የጤና አጠባበቅ አቅርቦትን የሚያገልገል ከሆነ፥ ግለሰባዊ ግንኙነቶችን እና የሚሰጠውን እንክብካቤ በእውነት የሚያሳድግ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ በሕክምና እና በቴክኖሎጂ መስኮች በቀጣይነት ለቁጥጥር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ብዙውን ጊዜ አደጋ ላይ የሚጥሉትን ሰፊ የኢኮኖሚ ጥቅሞች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

በዚህ መካከል ያሉ ፍላጎቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ጉባኤውን በተሳተፉ የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች እና በፖለቲካው መካከል ሰፊ ትብብር እንዲኖር ጠይቀው፥ ይህም ከአገር አቀፍ ድንበሮች በላይ በሚዘልቅ በሰው ሠራሽ አስተውሎት መስክ ሊሆን እንደሚገባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ አሳስበዋል።

11 Nov 2025, 16:42