ፈልግ

2025.06.15 Giubileo dello Sport - Santa Messa

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፣ የክህነት ኃላፊነት 'ሙሉ ስጦታ' ነው ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአንድ ወቅት መምህር ሆነው ባገለገሉበት በፔሩ ወደሚገኘው የዐብይ ዘርዓ ክህነት ተማሪዎች መልእክት መላካቸው የተገለጸ ሲሆን እነዚህ የምስጢረ ክህነት እጩዎች "የታማኝነት እና የፍቅር ቀጣይነት ያለው ምስክርነት እንዲሰጡ" ማበረታታታቸው ተዘግቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ረቡዕ ዕለት ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም በፔሩ በትሩጂሎ ወደሚገኘው ዋና የሊቀ ጳጳስ ሴሚናሪ መልእክት መላካቸው ተገልጿል፣  እዚያም በአንድ ወቅት ቅዱስነታቸው መምህር እና የጥናት ዳይሬክተር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ለተቋሙ "ለአራት ምዕተ ዓመታት ታሪክ" ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመልእክታቸው የሚማሩ ሰዎች አስፈላጊ ተግባር ሁልጊዜም ተመሳሳይ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን "ከጌታ ጋር በመሆን፣ እንዲቀርጻቸው መፍቀድ፣ እሱን ማወቅ እና መውደድ፣ እሱንም መምሰል" ይኖርባችኋል ሲሉ ቅዱስነታቸው በአጽኖ ገልጸዋል።

የክህነት ኃላፊነት ራስን 'ሙሉ ስጦታ' አድርጎ ማቅረብ ነው

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የዐብይ ዘርዓ ክህነት ተማሪዎችን ጥልቅ ተነሳሽነታቸውን እንዲመረምሩ ጋብዘዋል፣ ክህነት እንደ የግል ምኞት ብቻ ሊተረጎም እንደማይችል አጥብቀው ተናግረዋል።

"ክህነት ውጫዊ ግብ ወይም ከግል ችግሮች ለመውጣት ቀላል መንገድ እንደሆነ 'መደምደሚያ ላይ' መድረስ አይቻልም" ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጽፈዋል። “አንድ ሰው ሊጋፈጠው የማይፈልገውን ነገር መሸሽ ወይም ከስሜታዊነት፣ ከቤተሰብ ወይም ከማህበራዊ ችግሮች መሸሸጊያ አይደለም። ሹመት ሆነ ሥልጣን አይደለም፣ ነገር ግን የአንድ ሰው ህልውና ሙሉ ስጦታ ነው” ሲሉ ቅዱነታቸው ተናግረዋል።

ከዚያም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የክህነትን ምስጢር “ብቻ ሥልጣን ወይም ቢሮክራሲያዊ ተግባር” አድርገው እንዳይመለከቱ አስጠንቅቀዋል፣ “ጥቃቅን ዓላማዎችን ተጠቅሞ ክህነትን የሚፈልግ ሁሉ በመሠረታቸው ላይ ይሳሳታሉ እና መሰረቶቻቸው በአሸዋ ላይ ይገነባል” በማለት አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ጸሎት፣ ጥናት እና ቀጣይነት ያለው ማስተዋል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዐብይ ዘርዓ ክህነት ትምህርት መስጫ ተቋም ውስጥ ያለው ሕይወት “የውስጥ ተሃድሶ መንገድ” እንደሆነ አብራርተዋል፣ በዚህ ውስጥ ነጸብራቅ እና ቅንነት ለብስለት እና ለነፃነት እድገት አስፈላጊ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

የዐብይ ዘርዓ ክህነት ተማሪዎች በጸሎት እና ቃሉን በማዳመጥ ከኢየሱስ ጋር የግል ግንኙነት እንዲፈጥሩ አሳስበዋል፡- “ከእግዚአብሔር ጋር ትንሽ ነገር የሚነጋገር ሰው ስለ እግዚአብሔር መልካምነት ብዙ መናገር አይችልም!” ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ቤተ ክርስቲያን ከጌታ ጋር መገናኘት በአእምሮ ውስጥ ሥር መስደድ እንዳለበት ሁልጊዜ ስለተገነዘበች” የነገረ መለኮት ወይም የቲዎሎጂ ጥናትን ዋጋ አጉልተው ገልጸዋል”፥ ጥናት እና ትምህርት “አስፈላጊ” ነገሮች ናቸው ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ እምነት “ጠንካራ፣ ምክንያታዊ እና ለሌሎች የማብራራት ችሎታ” እንዲሆን ስለሚያስችል ጥናት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

‘ከመካከለኛነት ሽሹ’ እና በኅብረት ኑሩ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አክለው በመልእክታቸው እንደ ገለጹት ከሆነ የዐብይ ዘርዓ ክህነት ተማሪዎችን “ከመካከለኛነት እንዲሸሹ” እና በዓለማዊነት፣ በአክቲቪዝም፣ በአልጎሪዝም (ስልተቀመር) ወይም በርዕዮተ ዓለም እንዳይጠመዱ አሳስበዋል።

በተጨማሪም የካህናት የብቸኝነት አደጋን በተመለከተ ሐሳብ አንስተው አስጠንቅቀዋል፡- “የብቸኝነት መንፈስ ያለበት ካህን ተጋላጭ ነው… ቤተክርስቲያን ራሳቸውን ለሌሎች የሚሰጡ ቅዱሳን ካህናት ያስፈልጓታል፣ ብቸኛ አገልጋዮች አይደሉም፣ ተባብረው መሥራት ይኖርባቸዋል” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

በመልእክቱ መደምደሚያ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለዐብይ ዘርዓ ክህነት ተማሪዎች (ሴሚናሪዎች) ያላቸውን ቅርበት እና ጸሎት እንዲህ በማለት ገልጸዋል፣ “በጴጥሮስ ተተኪ ልብ ውስጥ ቦታ አላችሁ። የዐብይ ዘርዓ ክህነት ተቋሙ እጅግ በጣም ግዙፍ እና አድካሚ ስጦታ ነው፣ ​​ነገር ግን በዚህ ጉዞ ላይ በጭራሽ ብቻችሁን አይደላችሁም” በማለት ቅዱስነታቸው ከእነርሱ ጋር በጸሎት እንደሚሆኑ በመግለጽ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

06 Nov 2025, 13:40